
ከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራት በሚልኳቸው ሸቀጦች ላይ የጣሉት ታሪፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያመጣ ይጠበቃል። ከወዲሁ የፕሬዚዳንቱን እርምጃ የአውሮፓ ህብረት እና ቁልፍ አጋሮቻቸው አውግዘውታል።
ነገር ግን ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የጣሉት ታሪፍ ከቻይና በኩል ለየት ያለ ምላሽ ሊኖር ይችላል ተብሏል። የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ታሪፉን እንደ ስጦታ ሊያዪት ይችላሉ።
በዓለማችን ያሉ አምስት ባለ ታላላቅ ምጣኔ ኃብቶች ይህንን ታሪፍ እንዴት እንዳዩት የቢቢሲ ዘጋቢዎች ተመልክተውታል።
አውሮፓ አሜሪካን ልትጎዳ ብትችልም፤ ማጋጋል አትፈልግም
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ታሪፉ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች
የከፋ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ነው የአውሮፓ አገራትን ወክለው ባደረጉት ንግግር አጽንኦት የሰጡት።
ታሪፉ በዓለም ላይ ሊያስከትለው የሚችለው “ቀውስ እና ውስብስብነት ግልጽ ያለ መንገድ የለም” ብለዋል። ሆኖም ኮሚሽኑ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራትን ንግዶችን ለመጠበቅ ቃል ገብቷል።
እንደ ጀርመን የመኪና ኢንዱስትሪ፣ የጣሊያን የቅንጦት ቁሶች እና የፈረንሳይ ሻምፓኝ እና ወይን ከሌሎቹ በበለጠ በታሪፉ ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከአገራቸው የንግድ መሪዎች ጋር ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ለሐሙስ ጠርተዋል።
የአውሮፓ ህብረት የአሜሪካ ምርቶች እና አገልግሎቶችን ኢላማ በማድረግ እንደ አፕል፣ እና ሜታ ላይ አጸፋዊ እርምጃ መውሰድ ይችላል። ሆኖም የአህጉሪቷ አላማ ይህ አይደለም ይልቁንስ ትራምፕን እንዲደራደሩ ማሳመንን እንደ አማራጭ ይዟል።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ታሪፉ ስህተት መሆኑን ቢናገሩም፤ ሆኖም ከአሜሪካ ጋር በመምከር ስምምነት ላይ ለመድረስ መጣር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
- ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ100 አገራት ላይ ታሪፍ ጣሉ3 ሚያዚያ 2025
- ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ የጣሉት አዲሱ ታሪፍ እና የዓለም መሪዎች ምላሽ3 ሚያዚያ 2025
- ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ይሆናሉ?3 ሚያዚያ 2025
ለቻይናው መሪ የአሜሪካ ታሪፍ ስጦታ ነው
ትራምፕ ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ 54 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። አሜሪካ ከጣለቻቸው ታሪፎች አንደኛው ትልቁ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ገበያ ላይ የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎችን እንደሚጎዳ ምንም ጥርጥር የለውም።
ሆኖም የቻይና የአጸፋ ምላሽ ግዙፉን የቻይና ገበያ ለመድረስ እየሞከሩ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎችንም ይጎዳል።
ነገር ግን የትራምፕ ይህ እርምጃ በአንድ መንገድ ለቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እንደ ስጦታ ነው።
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ቻይና ከሌላዋ የዓለማችን ኃያል አገር አሜሪካ ጋር በመዋዳደርን የነጻ ንግድ ሻምፒዮን፣ ብዝኃነት ያላቸውን ተቋማት ደጋፊ አድርገው ይስላሉ።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ሺ ከአውሮፓ የመጡትን ጨምሮ ከትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ጋር መክረው ነበር።
እዚህ ላይ ምስሉ ግልጽ ነው።
በዶናልድ ትራምፕ ስር የምትተዳደረው አሜሪካ ቀውስ፣ የንግድ ትርምስ፣ ግለኝነት ላይ ያተኮረ ብሄራዊ ጥቅም የሚለውን ያሳያል። በሌላ በኩል የቻይናው ሺ አገር መረጋጋት፣ ነጻ ንግድ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን የምትወክል ተደርጋ ታይታለች።
የትራምፕ አስተዳደር በቅርብ ጊዜ ያሳለፉትን ታሪፍን ለማጣጣል የቻይና መንግሥት ሚዲያውን አደራጅቷል።
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን በተመለከተ በርካቶች ሊወዛገቡ ይችላሉ ሆኖም ትራምፕ እነዚህን መሰል እርምጃዎች በወሰዱ ቁጥር ፕሬዚዳንት ሺን ስለ አገራቸው የሚያወሩት ጉዳይ በቀላሉ እንዲገዛ የሚያደርግ ነው።
የምጣኔ ኃብቱም ሁኔታ በርካታ አገሮችን ከአሜሪካ አርቆ ወደ ቻይና በበለጠ ሊስባቸው ይችላል።

በዩናይትድ ኪንግደም ታሪፉ ባያስደስትም እፎይታን ፈጥሯል
የዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት አሜሪካ አገራቸውን “በለየላቸው አጥፊዎች” ውስጥ አለማካተቷ እና በጥሩ አገራት ውስጥ መዘርዘሯ እፎይታን ፈጥሯላቸዋል።
ሆኖም አገራቸው በጥሩ ዝርዝር ውስጥ መካተቷ ምን ማለት እንደሆነ አስቀድመው አያውቁም ነበር።
ዩናይትድ ኪንግደም ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ሸቀጦች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል፤ ይህም የፕሬዚዳንቱ የታሪፍ መነሻ ምጣኔ ነው።
የዩኬ ሚኒስትሮች እፎይታ ቢሰማቸውም አልተደሰቱም። በዩናይትድ ኪንግደም ላይ የተጣለው ታሪክ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም የንግድ አጋሮች ላይ የተጣለው ታሪፍ በስራ፣ በኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የንግድ ፍሰቶች ላይ በመጪዎቹ ጊዜያት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው።
አንድ የመንግሥት ምንጭ ይህንን ታሪፍ “በከፍተኛ ሁኔታ የሚያናጋ” ሲሉ ገልጸውታል።
በተለይም ታሪፉ በመኪናው ኢንዱስትሪ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ግንዛቤ አለ።
የንግድ ስምምነቶች ላይ እንዲደረስ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ድርድር ቀጥሏል።
አራት የዩናይትድ ኪንግደም ተደራዳሪዎችን ያቀፈ ቡድን ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር በርቀት ቢሆንም በከፍተኛ ውይይት ተጠምደዋል።
ነገር ግን ስምምነት መፈራረሙ የማይቀር ከሆነም ወደ ዋሽንግተን ለመሄድ ፈቃደኛ ናቸው።
ህንድ ተጽዕኖዎችን ብትፈራም፤ አንዳንድ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተስፋን ሰንቀዋል
በትራምፕ ታሪፎች ተጠቂ ከሆኑት መካከል የእስያ ምጣኔ ኃብቶች አንዱ ነው። አሜሪካውያን ከቬትናም በሚገቡ ምርቶች ላይ 46 በመቶ እንዲሁም ከካምቦዲያ ለሚመጡ ደግሞ 49 በመቶ ግብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
ከነዚህ ጋር ሲነጻጸር በህንድ ላይ የተጣለው ታሪፍ የተሻለ ነው።
ነገር ግን የተጣለባት 26 በመቶ ታሪፍ አሁንም ከፍተኛ እንደሆነ በተለይም ወደ አሜሪካ በሚላኩ “የሰው ጉልበትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀሙ” ምርቶችን በእጅጉ እንደሚጎዳ ኤዢያ ዲኮድድ የተሰኘ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሪያንካ ኪሾር ይናገራሉ።
“ይህም በአገር ውስጥ ባለው ፍላጎት እና በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ)ን ሊያንገዳድግደው እንደሚችል” ፕሪያንካ ይናገራሉ።
ነገር ግን እንደ ቬትናም ባሉ ተፎካካሪዎች ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታሪፍ የንግድ አቅጣጫዋን ሊያስቀይራት ስለሚችል የህንድ የኤሌክትሮኒክስ የወጪ ንግድ በዚህ ሊጠቀም ይችላል።
ነገር ግን ይህ ትራምፕ እየወሰዱት ባለው እርምጃ በአጠቃላይ በእድገት ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን አሉታዊ ሁኔታ የመቀነስ እድሉ አነስተኛ ነው።
ህንድ ከካናዳ፣ ከሜክሲኮ ወይም ከአውሮፓ ህብረት በተለየ ሁኔታ ከትራምፕ ጋር የማቻቻል ዘዴን በመከተል ከአሜሪካ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተደራደረች ነው።
ሆኖም ይህ የትራምፕ እርምጃ በህንድ ባለስልጣናት ዘንድ አጸፋዊ እርምጃ ያመጣ እንደሆነ የሚታይ ይሆናል።
የህንድ ትልቁ ወጪ ንግድ የሆነውና በየዓመቱ 13 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገባላት የመድኃኒት ኢንዱስትሪ እፎይታን የሚሰጥ ይሆናል። ነገር ግን መድኃኒቶች ከታሪፎች ነጻ ናቸው።
ደቡብ አፍሪካ ቅጣት ነው ያለችው ታሪፍ
የትራምፕ “አጸፋዊ ታሪፍ” በበርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ አነጣጥሯል። ከነዚህም መካከል 30 በመቶ በደቡብ አፍሪካ ላይ እና 50 በመቶ ደግሞ በሌሴቶ ላይ ተጥሏል።
የትራምፕን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የውጭ እና ሰብዓዊ እርዳታ በመቋረጡ ምክንያት እነዚህ አብዛኛዎቹ አገራት ከችግሩ ጋር እየታገሉ ይገኛል።
ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እና ኬንያን ጨምሮ እንደ አንዳንድ የአህጉሪቱ ታላላቅ ምጣኔ ኃብቶች ከአሜሪካ ጋር ለረጅም ጊዜ ነጻ የሆነ የንግድ ስምምነቶች ነበሯት።
እናም ይህ ታሪፍ በአገራቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል።
ትራምፕ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ 60 አገሮች “የለየላቸው አጥፊዎች” የሚል ምድብ ውስጥ አካተዋል።
በዚህ ምድብ ውስጥ የተካተቱት አገራት ለተከተሉት ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲ ምክንያት ከፍተኛ የታሪፍ ምጣኔ እንደሚጣልባቸው ትራምፕ ተናግረዋል።
“በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ መጥፎ ነገሮች እየተከናወኑ ነው። እኛ በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር እየከፈልናቸው ነው። ገንዘቡንም የቆረጥነው በነዚህ መጥፎ ነገሮች ነው” በማለት ትራምፕ ሌሎች አገራትን ከመጥቀሳቸው በፊት ስለ ደቡብ አፍሪካ በዚህ መልኩ ተናግረዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የትራምፕን ታሪፍ “ቅጣት” በማለት ያወገዙት ሲሆን “ለንግድ እና ለጋራ ብልጽግና እንቅፋት ሊሆን ይችላል” ብለዋል።