በተድባበ ማርያም

ግንቦት አንድ በዓል ንግሥ እየደረሰ ነው።

ይህ ህንፃ ቤተ ክርስቲያኗ አመሠራረት

=======🔹🔸🔹🔸🔹🔸=====

ተድባበ ማርያም በኦሪት ዘመን በቤተመቅደስ (ምኩራብ) አምልኮተ እግዚአብሔርና ፣ መሥዋዕተ ኦሪት ከተሰዋባቸው ቀደምት አድባራት መካከል አንዷና ዋናዋ ናት። ተድባበ ማርያም በ፱፻፹፪ [982] ዓመተ ዓለም (ከኢየሱስ ልደት በፊት) የተመሠረተች ሲሆን መሥራቹ ደግሞ የቤተ ልሔም ተወላጅና የአሚናዳብ ዘር የሆነው ሳቤቅ ነው። ሳቤቅ የቅዱስ ዳዊት የወንድም ልጅ ሲሆን ፤ በአዛሪያስ መሪነት ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ታቦተ ጽዮንን ተከትለው ከመጡት ፲፪፲፻12,000 (ዐሥራ ሁለት ሺህ) ነገደ እስራል መካከል አንዱ ነው። አዛሪያስ ደግሞ የተድባበ ማርያም የመጀመሪያው ፓትርያርክ ነው። በመጻሕፍትም እንደተደነገገው ተድባበ ማርያም የፓትርያርክ መቀመጫ ነበረች።

ተድባበ ማርያም ከክርስቶስ ልደት በፊት ፤ በዘመነ ብሉይ የነበረው መሥዋዕት ይሰዋባቸው ከነበሩት አራት ጥንታዊ አድባራት አንዷ ናት። ይቺ ጥንታዊ አድባር ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው በቀዳሚ ስሟ «ተድባበ ጽዮን» በደቡብ ወሎ በቀድሞው ቦረናና ሳይንት አውራጃ የምትገኘኝ በኢትዮጵያ ከሁሉም ቀድማ የተመሠረተች ታሪካዊ አድባር ናት፡፡ በመጽሐፈ ሱባኤ ዘአማኑኤል ካልእ ገጽ 2:6 ላይ እንደተጻፈው ፤ ከሳቤቅ ጋር ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ አብረውት ከመጡት መካከል ሊቀ ካህን አዛርያስ ፣ የዳዊት ልጅ ከአቢያጥ የተወለደው ጌዴዎን ፣ የእሴይ ልጅ የሰሎሞን አጎት ኤልያብ ፣ የዳዊት የልጅ ልጅ የአምኖን ልጅ ሔት ፣ ኢዩኤል ፣ ከነገደ ቢኒያም የተወለደው አብሔል ፣ ከከነዓን የተወለደው በልዳድ ፣ ከነገደ ይሁዳ የተወለደው አሴር ፣ ከመሳፍንት ወገን የሆኑት ሱርባ እና ጉርባ ጥቂቶቹ ናቸው። ከሌዋዊያኑ ካህናት ጋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት መሣፍንት፣ መኳንንትና ፣ ወይዛዝርት መካከል ፲፻፭፻ 1,500 (አንድ ሺህ አምስት መቶ) የሚሆኑት በተግባረ ዕድ [ የእጅ ሥራ ] የሠለጠኑ የወርቅና የብር ፣ የብረትና የመዳብ ፣ እንዲሁም የነሐስ

አንጥረኞች አዋቂዎች ጠቢባን ፀበርተ ዕፀውና ወቀርተ አዕባን ናቸው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከገቡም በኋላ ፪፲፻፭፻ 2,500 (ሁለት ሺህ አምስት መቶ) የሚሆኑት የሌዋዊያን ካህናትና ነገደ ፳ኤል ተከዜን ተሻግረው በየጁ በኩል አድርገው ተጕዘው በጥንቱ አጠራር «አምሐራ ሳይንት» የሚባለው አካባቢ ላይ ሰፍረዋል።

አማራ ሳይንት የአሁኗ ተድባበ ማርያም ካለችበት አምባ ላይ እንደደረሱ ፲፪ [12] በር ባለው ታቦር ተራራ ላይ ለእግዚብሔር ቤተ መቅደስ ሠርተው የአምልኮ ሥርዓታቸውን ማከናወን ጀመሩ። ቦታዋንም በሀገሩ ስም «ገሊላ» ብሎ ጠራት፡፡ ፓትርያርክ አዛሪያስ ደስ አለውና ስሙን በቡራኬ አጸደቀለት፡፡ ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ሲጨርስ ከሌዋውያኑም ከካህናቱም ከፍሎ መሥዋተ ኦሪት የሚሠው ካህናትና ሌዋውያንንም ሾመ፡፡ መሥፍኑ ሳቤቅ ቤተ ልሔማዊም በገጸ ንጉሥ በወርቅ ወንበር የሚቀመጥ ነበር፡፡ በኋላም ሌዋዊያኑ ካህናት ግማሾቹ ደብር ደባብ እንበላት አሉ አዛርያስ እና የዳዊት የወንድም ልጆች ሳቤቅ ይህቺማ

የኢየሩሳሌም የዳዊት መታሰቢያ ከተማ ትሆን ዘንድ «ተድባበ ጽዮን» እንበላት ብለው እንደሰየሟት ይነገራል፡፡ በኋላም በዘመነ ሐዲስ ክርስትና ሲስፋፋ አምሐሮች «ተድባበ ጽዮን» የሚለውን ስያሚ እንዲቀይሩ የአኵሱም ነገሥታት የነበሩት አብረሃ ወአጽበሃ አሰገደዷቸው፡፡ ነገሥታቱም ተድባብ ጽዮንን «ተድባበ ማርያም» ብለው ሰየሙ፡፡ ትርጓሜውም ለእግዚአብሔር የተመረጠ ከፍተኛ ቦታ ማለት ነው፡፡

ተድባበ ማርያም የተመሠረተችበት ተራራ 12 በሮች ሲኖሩት ፣ ወደ ተራራው መዝለቅ ወይም መግባት የሚቻለው ግን በሁለት የተፈጥሮ በር ብቻ ነው። እነዚህ 12 በሮችም ለነገደ እስራኤል መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ሳቤቅ አገሮቹን አሻግሮ እያየ በሀገሩ ምሳሌ ሰይሟዋቸዋል፡፡ እነዚህም በሮች ገሊላ ፣ ደብረ ዘይት ፣ ኬብሮን ፣ እያሪኮ ፣ ሎዛ ፣ ታቦር ፤ ቦረና መግቢያ ላይ ሊባኖስ ፣ ደማስቆ ፣ አርሞንኤም ፣ ደብር ፋራን ፤ በሰሜን በኩል ደግሞ ኮሬብ ፣ ቃዴስ ደብረ ፍጌህ፣ ቂሣርያ ፣ ቢታኒያ ፣ ጋዛ ፣ ጎልጎታ ፣ ፌልስጥኤም በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሳቤቅ አማራ ሳይንትን ያስተዳድር እንደነበር ተጽፏል። ዙፋኑ ፣ ዳታኑና ፣ ወንበሩ የብረት ዙፋን በመባል ይታወቃል።/ያሬድ ግርማ ጎንደር ታሪክ 1999 ዓ.ም ርእሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም በብሉይ ኪዳን ስለመመሥረቷ

ምስክር የሚሆኑ አንዳንድ የኦሪት ሥረዓቶች ሲከናወኑ ይስተዋላሉ ታቦታቱ በሚነግሡበት ወቅት በምሥራቅ ያሉ ምእመናን ነዋያተ ቅዱሳቱን ይዘው በምዕራብ ካህናት ተሰልፈው በሰሜን ያሉ ምእመናን መጋረጃን ይዘው በደቡብ ያሉ ምእመናን ጎራዴውንና ካሰማውን ይዘው መንቀሳቀሳቸው በኦሪት ዘኁልቁ ፪፥፫-፬ ያለውን የኦሪት ሥርዓት ያመለክታል።

ዐጼ ይኵኖ አምላክ በ፲፫ኛው (13ኛው) ክ/ዘ ቤተ መንግሥታቸውን በታቦር ተራራ አድርገው በብሉይ ዘመን የፍርድ መስጫ የነበረውን አደባባይ (ጕላቴ) እንዳሉት ይነገራል። በተራራው በስተቀኝ በኩል በሚገኘው በዚህ አደባባይ በ ፲፻፪፻፸ [1270] ዐጼ ይኵኖ አምላክ የአማርኛ ቋንቋን ብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆን አውጀውበታል። በተጨማሪም በተጋር ተራራ ዮሐንስ ገብላዊ የቅኔ መድብል ያዘጋጁበት ብሉያተ ካህናት የተናገሩበት ጽዋተ ዜማ የተዘመረበት ቦታ ነው። የዐፄ ይኵኖ አምላክ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ይገኝበታል ተብሎ የሚታመነዉ በታቦር ተራራ ነው።

✥ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗ አመሠራረት ✥

ተድባበ ማርያም ስትመሠረት በኦሪት ዘመን በነበረው ሥርዓተ አምልኰት

ስለነበር አመሠራረቷ እንደ ቤተ መቅደስ (ምኩራብ ፣ አድባር) ነበር። በገድለ ገላውዲዎስ ላይ እንደተመለከተው ግን ለዘመናት በድንኳን ውስጥ እንደነበረች ተገልጿል። የኋላ ኋላ በዘመነ ሐዲስ የክርስትና መስፋፋትን ተከትሎ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶላታል። የተድባበ ማርያምን የመጀመሪያ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ያሠሩት ዐጼ ገላውድዎስ ናቸው። በስማቸውም ጽላት ተቀርፆላቸው በየዓመቱ ግንቦት ፪ [ 2 ] እየተከበረ ይገኛል። ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በየዘመናቱ በተነሱ ነገሥታት ሲሠራና ሲፈርስ ኖሮ አሁን ያለውና ከነሞገሡ የሚታየው ሕንፃ ዘጠነኛው ሕንፃ ሲሆን የተሠራው በንጉሥ ሚካኤል ነው፡፡ የሳር ጣሪያዋ ደግሞ በ፲፻፱፻፶፭ ፤ 1955 ዓ.ም. በእቴጌ መነን መልካም ፍቃድና ገንዘብ ቆርቆሮ እንዲለብስ ተደርጓል፡፡ ዐጼ ገላውድዎስ አባታቸውን ዐጼ ልብነ ድንግልን ተክተው አገራችን ኢትዮጵያ ከ፲፻፭፻፴፫-፲፻፭፻፶፩ ፤ 1533 አስከ 1551 ዓ.ም ድረስ ለ፲፱ ፤ 19 ዓመታት አስተዳድረዋል ፡፡ ዐጼ ገላውድዎስ በልዩ ልዩ ስፍራዎች ከግራኝ አህመድ ጋር ጦርነት አካሂደዋል፡፡ በመጨረሻም ዐጼ ገላውድዎስ የተድባበ ማርያምን ጽላት በመያዝ ዘምተው

በ፲፻፭፻፴፭ ፤ 1535 ዓ.ም በበጌምድር ግዛት ግራኝን ድል አድርገው አሸንፈዋል፡፡ ጽላቷን ይዘው ከዐጼ ገላውዴዎስ ጎን የተሰለፉት በወቅቱ የተድባበ ማርያም ፓትርያርክ የነበሩት አባ ዮሐንስ ናቸው። ከዚያም ዐጼ ገላውድዎስ ዋና ከተማቸውን ተድባበ ማርያም ካስማ ከተባለ ቦታ ላይ አደረጉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተድባበ ማርያም በአካባቢው ኅብረተሰብ ‹‹የግራኝ እመቤት›› እየተባለች ትጠራለች፡፡ ቤተክርስቲያኑ አራት በሮች ( ሦስት ሜትር ቍመት) እና ፴፪ ፤ 32 መስኮቶች (ሁለት ሜትር ቍመት) በውጭ በኩል ክብ ነው። በንድፍ ፣ ቤተ ክርስቲያኑ በሦስት ክፍሎች በተሰበሰቡ ክበቦችተደራጅቷል። በማዕከሉ ውስጥ ያለው አብዛኛው ክፍል ውስጠ ቅድስት (ቅድስተ ቅዱሳን) እና ዲያሜትር ፳፬ ፤ 24 ሜትር

ያህል ነው። ታቦቱ በግልጽ ድንኳን ውስጥ (ድንኳን) ውስጥ እንደሚቀመጥ የታመነበት ይህ ነው። አሁን ባለችበት ሁኔታ ፣ ቤተ ክርስቲያኑ በአጠቃላይ ወደ ፴፬ ፤ 34 ሜትር ዲያሜትር ትለካለች።

የአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ያላችሁ ጎብኝዎች እንዲሁም የተዋህዶ ልጆች ግንቦት 1 በጥንታዊትና ታሪካዊት ተድባበ ማርያም ተገኝታችሁ ትናንታችንን እንዲትመለከቱ ከወዲሁ ጥሪ እናስተላልፋለን