ከእስራኤል ጥቃት የተረፈው የህክምና ባለሙያ

ከ 8 ሰአት በፊት

“ባልደረቦቼ ላይ የተፈፀመውን በዐይኔ ያየሁ ብቸኛ ተጎጂ ነኝ” ይላል ሙንተር አቤድ በእጅ ስልኩ ላይ የባልደረቦቹን ፎቶግራፍ እየተመለከተ።

ከሳምንት በፊት በጋዛ 15 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በእስራኤል ጥቃት ሲገደሉ በአምቡላንሱ ወለል በመወርወር ሕይወቱ ተርፏል።

ከፊት የነበሩ ሁለቱ ባልደረቦቹ በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል።

“ረፋድ አካባቢ ከዋና መስሪያ ቤታችን ተነሳን” የሚለው ሙንተር፤ የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ፣ የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጄንሲ እና ከመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኛ ተልዕኮ የተውጣጡ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቡድን የቆሰሉ ሰዎችን ለማከም ወደ ራፋ ከተማ እያቀና ነበር።

ከጠዋቱ 5፡00 አካባቢ የመንግሥታቱ ድርጅት ተሽከርካሪ መንገድ ላይ በቀጥታ መመታቱን ይናገራል።

የእስራኤል መከላከያ ተሽከርካሪዎቹ መብራቶቻቸውን አጥፍተው ወደ ወታደሮቹ ሲጠጉ አጠራጣሪ ሆነው በመታየታቸው እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደደ ገልጿል።

በክስተቱ ዘጠኝ የሀማስ እና የፍልስጤም አክራሪ ቡድን አባላት መገደላቸውንም አስታውቋል።

ከዚህ ጥቃት ብቸኛ የተፈረው ሙንተር ግን ይህን አይቀበልም።

“ሌት ከቀን ተመሳሳይ ነገር ነው። የውጭ እና የውስጥ መብራት በርቷል። ሁሉም ነገር ተሽከርካሪው የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ንብረት የሆነ አምቡላንስ እንደሆነ ይናገራል። ሁሉም መብራት ቀጥታ እስኪተኮስብን ድረስ እየበራ ነበር” ይላል።

ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ከፍርስራሹ የእስራኤል ወታደሮች አውጥተው አይኑን ሸፍነው እንዳሰሩት ይናገራል።

ከመለቀቁ በፊትም ለ15 ሰዓታት ምርመራ እንደተደረገበት ይገልጿል።

የሙንተርን ቃል ቢቢሲ ለእስራኤል መከላከያ ኃይል ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ጥቃቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠይቀው “የእስራኤል መከላከያ ኃይል በዘፈቀደ አምቡላንስ አላጠቃም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“በርካታ ያልተቀናጁ ተሽከርካሪዎች ያለ ግንባር መብራት እና የአደጋ ጊዜ ምልክት አጠራጣሪ በሆነ መልኩ ወደ እስራኤል ወታደሮች ሲገሰግሱ ታይተዋል። ከዚያም ወታደሮች በተጠርጣሪ ተሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል” ብለዋል።

በቅድመ ግምገማ በጥቅምት 7ቱ ጥቃት የተሳተፉት መሀመድ አሚን ኢብራሂም ሽባኪ የተባሉ የሀማስ አመራር እና ሌሎች ስምንት አሸባሪዎች መገደላቸውን አክለው ተናግረዋል።

የህክምና ባለሙያዎቹ የቀብር ስነ ስርዓት

የመሀመድ አሚን ኢብራሂም ሽባኪ ስም በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፉት 15 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ውስጥ አልተካተተም።

ሟቾቹ ስምንት የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ባለሙያዎች፣ ስድስቱ ደግሞ የሲቪል መከላከያ የመጀመሪያ ምላሽ ሰጭዎች እና አንደኛው ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጤም ኤጄንሲ ባልደረባ ናቸው።

እስራኤል የመሀመድ አሚን ኢብራሂም ሽባኪ አስከሬን መገኛንም ሆነ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ስላሳደሩት ስጋት ማስረጃ አላቀረበችም።

ሙንታር አምቡላንሶቹን ሀማስ ለሽፋን ተጠቅሞባቸው የሚለውን የእስራኤል አቋም አይቀበልም።

“ይህ በፍፁም ውሸት ነው። ሁሉም ሰራተኞች ንፁሃን ናቸው” ይላል።

“የትኛውም የጦር ቡድን አይደለንም። ዋናው ተልዕኳችን የሰው ሕይወትን ለማትረፍ የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠት ነው” ብሏል።

የጋዛ የሕክምና ባለሙያዎች በዚህ ሳምንት የባልደረቦቻቸውን የቀብር ስነ ስርዓት ፈፅመዋል።

የእስራኤል ጦር በቅርቡ የገደላቸውን የህክምና ባለሙያዎችን ቀብር፣ የተባበሩት መንግሥት “የጅምላ መቃብር” ሲል ገልጾታል።

ዘጠኝ ሰዎችን ጭኖ የነበረው አምቡላንስ አልሃሺን በተባለ ስፍራ ከሳምንት በፊት ከፍተኛ ተኩስ እንደተፈጸመበት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ገልጿል።

ለሳምንት ያህል ወደ ስፍራው መድረስ በመከልከሉ አስከሬናቸው ከተገደሉ ከሳምንት በኋላ እሁድ፣ መጋቢት 21/ 2017 ዓ.ም መወሰዱ ተገልጿል።