ሱዛን ልጅ ሳለች
የምስሉ መግለጫ,ሱዛን ልጅ ሳለች

ከ 8 ሰአት በፊት

ሱዛን የዘረ መል መመርመሪያ መሣሪያ ገዝታ ነበር በቤቷ ምርመራ ያደረገችው። ውጤቱን ስታይ ማመን ተሳናት።

አሁን በ70ዎቹ አጋማሽ ላይ ትገኛለች። ስለ አያቷ ብዙም አታውቅም ነበር።

“ከአየርላንድ የሚመዘዝ የዘር ግንድ እንዳለ ባስተውልም ስህተት ይመስለኝ ነበር” ትላለች።

ነገሩን ችላ ብላው ብትቆይም የኋላ ኋላ እውነታውን ማወቋ አልቀረም።

ስለ ቤተሰቧ የምታውቀው ሁሉ ስህተት መሆኑን ደርሳበታለች።

በ1950ዎቹ በሕጻናት ማዋለጃ ክፍል ውስጥ ከሌላ ልጅ ጋር እንደተለዋወጠች አወቀች።

የዘረ መል ምርመራ በቤት ማድረግ ርካሽ እየሆነ ሲመጣ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። እንደ ሱዛን ያሉ ታሪኮችም መሰማት ጀምረዋል።

ሱዛን በደቡብ ኢንግላንድ ነው የምትኖረው። ተጫዋች ናት። ባለቤቷ ከጎኗ ተቀምጦ የረሳችውን የታሪክ ክፍል ያስታውሳታል።

የዘረ መል ምርመራ ያደረገችው ከአሥር ዓመት በፊት ነበር። ውጤቱ የተመዘገበበት ድርጅት መረጃዋን በቋት ውስጥ አኑሮታል።

የቅርብም ይሁን ዘመዶቿ ድንገት ምርመራ ካደረጉ የድርጅቱን መረጃ ያገኛሉ።

ከስድስት ዓመት በፊት ያልተጠበቀ ዜና ሰማች።

አንድ ሰው በዘረ መል ውጤቱ ከሷ ጋር እንደሚዛመድ ነገራት።

“በጣም ደነገጥኩ። አእምሮዬ ከቁጥጥሬ ወጣ” ሰትል ወቅቱን ታስታውሳለች።

ምናልባት ወላጆቿ ሳይነግሯት በማደጎ አሳድገዋት እንደሆነ ጠረጠረች።

እናትና አባቷ ስለሞቱ ታላቅ ወንድሟን ጠየቀችው። እንዛመዳለን ያላት ሰው እያጭበረበረ መሆኑን ነበር ወንድሟ ያሰበው።

እናታቸው ሱዛንን እርጉዝ ሆና እንደሚያስታውስ ታላቅ ወንድሟ ነገራት።

ሱዛን ግን ጥርጣሬ ነበራት።

ሱዛን ከወንድሟ በቁመት ትበልጣለች። ፀጉሯ ወርቃማ ቀለም ከመሆኑ በተጨማሪ ከሌሎቹ ቤተሰቦቿ ጋር አትመሳሰልም።

ልጇ ጉዳዩን ማጣራት ጀመረች።

ሱዛን በተወለደችበት አካባቢ የተመዘገቡ ልጆችን ዝርዝር አፈላለገች።

ከሱዛን ስም ቀጥሎ ያለው ስም ለሱዛን መልዕክት ከላከላት ሰው የአባት ስም ጋር ይመሳሰላል።

ለሱዛን ዘመድ ነን ብሎ መልዕክት የላከላት ሰው ስም በዝርሩ ውስጥ ከሱዛን ቀጥሎ መመዝገቡ አስደነገጣቸው።

አጋጣሚ ሊሆን አይችልም። ከ70 ዓመት በፊት ልጆች ተለዋውጠው መሆን አለበት።

አሁን ላይ የዩኬ ብሔራዊ ጤና ተቋም ልጆች ሲወለዱ እግራቸው ላይ መለያ ያስርላቸዋል። እናትና ልጅ አብረው እንዲቆዩም ይደረጋል።

በ1950ዎቹ የነበረው አሠራር ግን ይለያል። ልጆች በትልቅ ማቆያ ውስጥ ስለሚደረጉ ከእናቶቻቸው ጋር ይለያያሉ። የሚንከባከቧቸውም አዋላጆች ናቸው።

ሱዛንን የሚወክላት ጠበቃ ራሰል ኩክ “ያኔ አሠራሩ አስተማማኝ አልነበረም። እንደተወለደች መለያ አልሰጧትም ይሆናል። አልያም መለያው ጠፍቶ የተሳሳተ አልጋ ላይ አስተኝተዋታል” ይላል።

ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በዩኬ በድኅረ ጦርነት የወሊድ ቁጥር ጨምሯል። የልጆች ማዋለጃ ክፍሎች ጫና ውስጥም ነበሩ።

ሱዛን በመንግሥት ሠራተኛ ቤተሰብ ውስጥ አድጋ የብሔራዊ ጤና ተቋም ሠራተኛ ሆናለች።

ወላጆቿን “በጣም የሚዋደዱ ጥሩ ቤተሰቦች ነበሩ። በአቅማቸው ያበረታቱኝ ነበር” ስትል ትገልጻለች።

ልጆች
የምስሉ መግለጫ,በ1950ዎቹ ልጆች በትልቅ ማቆያ ውስጥ ስለሚደረጉ ከእናቶቻቸው ጋር ይለያያሉ።

“በሕይወት ኖረው እንኳንም ይሄንን ጉድ አላዩ። ከሰማይ ሆነውም ይሄንን ባያዩ እመኛለሁ” ትላለች።

ቤተሰቦቿን ማሳዘን ስለማትፈልግ እውነታውን በሕይወት ሳሉ ብታውቅም እንኳን እንደማትነግራቸው ትገልጻለች።

“ለኔ ስለነሱ የተለወጠ ነገር የለም። አሁንም እናትና አባቴ ናቸው” ትላለች።

ከታላቅ ወንድሟ ጋር ያላት ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሯል።

“ፖስት ካርድ ሲልክልኝ ‘ለውድ እህቴ’ ብሎ ይጽፍበታል። ሌላ የአጎቴ ልጅም ሁሌም ቤተሰባችን ነሽ፤ አትጨነቂ ብሎኛል” ስትል ቤተሰቦቿን ትገልጻለች።

እውነተኛ ወንድሟን ስታገኘው ቁርጥ እሷን የሚመስል መሆኑ አስገርሟታል።

“ፀጉሩ ላይ ዊግ አድርጋችሁ ሊፒስቲክ ብትቀቡት እኔን ያያችሁ ነው የሚመስላችሁ” በማለት እየሳቀች ትናገራለች።

ከሷ ጋር የተለዋወጠችውን ልጅ ፎቶና የልጆቿንም ፎቶ አይታለች። ከቤተሰቡ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ግን ቀላል አልሆነም።

“የሥጋ ቤተሰቦቼና ዘመዶቼ ቢሆኑም አብረን አላደግንም። እህታችን ብለው ላሰቧት ሴት ወገንተኝነት ማሳየታቸውን አደንቃለሁ” ትላለች።

የሥጋ እናትና አባቷ ቢሞቱም እናቷን እንደምትመስል ተነግሯታል።

“ምን ዓይነት ሴት እንደነበረች ማወቅ እፈልግ ነበር። ግን አልችልም” ትላለች ሱዛን።

ነገሩን ከስሜታዊነት ወጥታ ስትመለከተው ባደገችበት መንገድ ደስተኛ ናት።

ሱዛን ሆስፒታል ውስጥ ከሌላ ልጅ ጋር በመለዋወጧ ካሳ የተሰጣት የመጀመሪያዋ ሰው ናት።

ብሔራዊ የጤና ተቋም ዘለግ ያለ የይቅርታ መልዕክት ልኮላታል።

ሱዛን ከገንዘብ ካሳው ይልቅ ስህተት መሠራቱን ማመናቸው ያስደስታታል።

“የሆነን አካል ተጠያቂ ማድረግ እንፈልጋለን። የኔ ፍላጎት ግን ለጥያቄዬ መደምደሚያ መልስ ማግኘት ነው” ትላለች።