ዋሽንግተን የተሰባሰቡ ሰልፈኞች

ከ 6 ሰአት በፊት

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር መንበረ ስልጣኑን ከተረከቡ ወዲህ ትልቅ ነው የተባለ የተቃውሞ ሰልፍ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ተካሄደ።

“የእጃችሁን አንሱ” የተቃውሞ መሪዎች በ50 የአሜሪካ ግዛቶች በሚገኙ በአንድ ሺህ 200 አካባቢዎች ሰልፎችን ለማድረግ አስበው ነበር።

በቦስተን፣ ቺካጎ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ኒውዮርክ እና ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቅዳሜ ዕለት በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ ተሳትፈዋል።

ተቃዋሚዎቹ ትራምፕ ከማኅበራዊ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚያራምዱት አጀንዳ ላይ ያላቸውን ቅሬታ አንስተዋል።

ትራምፕ በአብዛኛዎቹ የዓለም አገራት ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ካሳወቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ በለንደን፣ በፓሪስ እና በርሊንን ጨምሮ ከአሜሪካ ውጭ ሰልፎች ተካሂደዋል ።

የለንደን የተቃውሞ ሰለፍ

በቦስተን አንዳንድ ተቃዋሚዎች በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ለእስር እና ከአገር ለመውጣት በመገደዳቸው ሰልፉን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የሕግ ተማሪዋ ኬቲ ስሚዝ ለቢቢሲ እንደገለጸችው ከሆነ ባለፈው ወር ቦስተን ተፍትስ ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር የዋለው ቱርካዊው ተማሪ ሩሜሳ ኦዝቱርክ መያዙ ሰልፉን እንድትቀላቀል ምክንያት ሆኗታል።

“እኔ ሰልፍ አልወድም፤ ግን ዛሬ መቃወም ትችላለህ ካልሆነ ነገ ተራው ያንተ ሆኖ ልትወሰድ ትችላለህ” ስትል አክላ ገልጻለች።

በለንደን ተቃዋሚዎች “ሰዎችን መጉዳት አቁሙ” እና “እሱ ደደብ ነው” የሚሉ መፈክሮች ይዘው ታይተዋል።

የፓሪስ ተቃውሞ

ትራምፕ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያደረጓቸውን ለውጦች በመጣቀስ “ከካናዳ ላይ እጃችሁን አንሱ”፣ “ከግሪንላንድ ላይ እጃችሁን አንሱ” እና “ከዩክሬን ላይ እጃችሁን አንሱን” ሲሉ ተሰምቷል።

ትራምፕ ካናዳ እና ግሪንላንድን ለመጠቅለል ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር በይፋ አለመግባባት ውስጥ ከመግባታቸውም በላይ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሠላም ስምምነትን እንዲደረስ ማድረግ አልቻሉም።

በዋሽንግተን ዲሲ ደግሞ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሕግ አውጪዎችን ንግግር ለማድመጥ ተሰባስበዋል።

ብዙዎቹ አስተያየቶች ያተኮሩት በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ሃብታሞች ለጋሾች በሚጫወቱት ሚና ላይ ነበር። ዋነኛው ትኩረት ደግሞ የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በመሆን በሚያገለግሉት እና ወጪዎችን እና የፌደራል የሥራ ሃይልን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ጥረት በሚያደርጉት ኤለን መስክ ላይ ሆኗል።

የፍሎሪዳ ኮንግረስማን ማክስዌል ፍሮስት “መንግሥታችን በቢሊየነር ተወሯል” ሲሉ አውግዘዋል።

“ከሕዝብ ስትሰርቁ ሕዝቡ እንደሚነሳ ጠብቁ። ይህ ደግሞ በምርጫ ኮሮጆ እና በጎዳና ላይ ይገለጻል” ብለዋል።

ሰልፉ የተካሄደው በፍረሎሪዳ የተካሄደው ምርጫ በፕሬዚዳንቱ እና በአጋሮቻቸው ጠበሳ ካሳረፈ በኋላ ነው።

ሪፐብሊካኖች ማክሰኞ ዕለት ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት ልዩ የፍሎሪዳ ኮንግረስ ምርጫ ቢያሸንፉም፣ ያሸነፉት ካሰቡት በላይ በጠባብ ልዩነት ነው።

የዊስኮንሲን መራጮች ደግሞ በግዛቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲያገለግሉ ዲሞክራቲክ ዳኛን የመረጡ ሲሆን በመስክ የሚደገፉት የሪፐብሊካን ዕጩ በ10 በመቶ ድምጽ ተበልጠዋል።

በሁለቱም ግዛቶች ዲሞክራቶች በትራምፕ አስተዳደር ፖሊሲዎች እና በኤለን መስክ ተጽእኖ ላይ የመራጮች ቁጣን ለምርጫው ተጠቅመዋል።

የኒው ዮርክ ተቃውሞ
ፍሎሪዳ

አንዳንድ የሕዝብ አስተያየት ውጤቶች የፕሬዚዳንት ትራምፕ ተቀባይነት በጥቂቱ መቀነሱን አሳይተዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተለቀቀው ዋን ሮይተርስ/አይፕሶስ የሕዝብ አስተያየት ወደ 43 በመቶ ዝቅ ማለቱን እና ይህም ትራምፕ በጥር ወር ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ ወዲህ ዝቅተኛው ነጥብ መሆኑን አሳይቷል። ጥር 20 በዓለ ሲመታቸው ሲደረግ ቁጥሩ 47 በመቶ ነበር።

ተመሳሳይ ጥናት እንዳመለከተው 37 በመቶ አሜሪካውያን የኢኮኖሚውን አያያዝ ሲደግፉ 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በአሜሪካ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ያላቸውን ስትራቴጂ ደግፈዋል።

ሌላ በሃርቫርድ ካፕ/ሃሪስ የሕዝብ አስተያየት ውጤት ደግሞ ከመራጮች መካከል 49 በመቶዎቹ የትራምፕን አፈጻጸም ቢያጸድቁም ባለፈው ወር ከነበረበት 52 በመቶ መቀነሱ ታይቷል።

54 በመቶ መራጮች ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሻለ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በዋሽንግተን ለተቃውሞ የወጣች ቴሬሳ የተባለች ግለሰብ “ዲሞክራሲያዊ መብታችንን እያጣን ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

“በፌዴራል መንግሥት ደረጃ እያደረጉት ያለው ቅናሽ በጣም አስግቶኛል” ስትል የጡረታ እና የትምህርት ጥቅማ ጥቅሞች እንዳሳሰባት ተናግራለች።

ትራምፕ የተቃዋሚዎቹን መልዕክት ሰምተው እንደሆነ ስትጠየቅም “[ትራምፕ] በየቀኑ ጎልፍ ስለሚጫወቱ የሚሆነውን እናያለን” ስትል መልሳለች።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ምንም ዓይነት ኦፊሴላዊ ዝግጅቶችን ያላደረጉ ሲሆን ፍሎሪዳ በሚገኘው ሪዞርታቸው ጎልፍ በመጫወት ቀኑን አሳልፈዋል። እሑድ ጎልፍ እንዲጫወቱ ዕቅድ ተይዞላቸዋል።

ዋሽንግተን
ሂውስተን ቴክሳስ

ኋይት ሃውስ የትራምፕን አቋም የሚከላከል መግለጫ በማውጣት እንደሜዲኬር ያሉ ፕሮግራሞችን መጠበቃቸው እንደሚቀጥሉ እና ዴሞክራቶችን ስጋት ሲል ገልጿቸዋል።

“የፕሬዚዳንት ትራምፕ አቋም ግልጽ ነው፡ ሁልጊዜም ለሶሻል ሴኪውሪቲ፣ ለሜዲኬር እና ለሜዲክኤይድ ብቁ ሆኑ ተጠቃሚዎች ይጠብቃል። የዴሞክራቶች አቋም ደግሞ ለሕገ-ወጥ የውጭ ዜጎች የሶሻል ሴኪውሪቲ፣ ሜዲክኤይድ እና ሜዲኬር ጥቅማጥቅሞችን በመስጠት እነዚህን ፕሮግራሞች ከማክሰር ባለፈ የአሜሪካ ዜጎችን ያደቃል” ብሏል መግለጫው።

ከትራምፕ ከፍተኛ የኢሚግሬሽን አማካሪዎች አንዱ ቶም ሆማን ቅዳሜ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ተቃዋሚዎች ከኒውዮርክ መኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ሰልፍ ማድረጋቸውን ነገር ግን እሳቸው በወቅቱ በዋሽንግተን እንደነበሩ ተናግረዋል።

“ባዶ ቤት የፈለጉትን ሁሉ ተቃውሞ ማሰማት ይችላሉ” ያሉት ሆማን፤ “ተቃውሞ እና ሰልፍ ምንም ማለት አይደለም” ሲሉ አክለዋል።

“ስለዚህ ይቀጥሉ እና የመናገር ነፃነት መብቶቻቸውን ይጠቀሙ። ይህ እውነታውን አይለውጥም” ብለዋል።

ሚኔሶታ