በጋዛ አምቡላንሶቹ የነበሩበትን ሁኔታ ከሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የተወሰደ

ከ 6 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጦር ወታደሮቹ በደቡባዊ ጋዛ መጋቢት 14/2017 ዓ.ም. በ15 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ግድያ ላይ ስህተት መሥራታቸውን አመነ።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማሕበር አምቡላንሶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የእሳት አደጋ መኪና በራፋህ አቅራቢያ በእስራኤል ጦር የተኩስ እሩምታ ተከፍቶባቸው 15 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተገድለዋል።

እስራኤል መጀመሪያ ላይ ወታደሮቿ ተኩስ የከፈቱት መኪኖቹ የፊት መብራትና የአምቡላንስ መብራቶችን ሳያበሩ በጨለማ ውስጥ “አጠራጣሪ” በሆነ መልኩ እየቀረቡ በመምጣታቸው ነው ብላ ነበር።

የተሽከርካሪዎቹ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል ከሠራዊቱ ጋር የተቀናጀ ወይም ስምምነት የተደረገበት አልነበረም።

ከተገደሉት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መካከል በአንዱ ሞባይል የተቀረፀው ተንቀሳቃሽ ምስል ተሽከርካሪዎቹ የቆሰሉ ሰዎችን ለመርዳት ሲሄዱ መብራታቸውን ማብራታቸውን ያሳያል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከሕክምና ባለሙያዎች መካከል ቢያንስ ስድስቱ፣ ምንም እንኳ ማስረጃ ባያቀርብም፣ ከሃማስ ጋር ግንኙነት አላቸው ሲል ተከራክሯል።

የእስራኤል ወታደሮች የተኩስ እሩምታ ሲከፍቱ የሕክምና ባለሙያዎቹ ያልታጠቁ መሆናቸውን አምኗል።

በመጀመሪያ በኒውዮርክ ታይምስ የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ተሽከርካሪዎቹ ተኩስ ሲከፈትባቸው መቆማቸውን ያሳያል።

ቀረጻው ከአምስት ደቂቃ በላይ የቀጠለ ሲሆን፣ ሬፋት ሬድዋን የተባለ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ተሽከርካሪዎቹ ሲቃረቡ ድምፅ ከመሰማቱ በፊት፣ የመጨረሻውን ፀሎት ሲያደርግ ይሰማል።

የእስራኤል መከላከያ ባለስልጣን ቅዳሜ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወታደሮቹ ቀደም ብለው ሦስት የሃማስ አባላትን የያዘ መኪና ላይ ተኩስ ከፍተው ነበር ብሏል።

አምቡላንሶቹ የደረሳቸውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አካባቢው ሲቃረቡ ከአየር ላይ ቅኝት እና ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት በምድር ላይ ለሚገኙት ወታደሮች መኪኖች “አጠራጣሪ በሆነ ሁኔታ እየቀረቡ” መሆኑን አሳውቀዋል።

አምቡላንሶቹ ከሃማስ መኪና አጠገብ ሲቆሙ፣ ምንም እንኳ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞቹ መሳርያ ስለመያዛቸው መረጃ ባይኖርም፣ ወታደሮቹ አደጋ ላይ እንደሆኑ ገምተው ተኩስ ከፍተዋል።

እስራኤል ቀደም ሲል መኪኖቹ መብራት ሳያበሩ ተቃርበዋል ስትል የሰጠችው መግለጫ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ መረጃው በስፍራው ከነበሩ ወታደሮች መገኘቱን ገልጻለች።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደሚያሳየው ተሽከርካሪዎቹ በግልጽ ምልክት የተደረገባቸው ሲሆን የሕክምና ባለሙያዎቹም አንጸባራቂ የደንብ ልብስ ለብሰዋል።

የእስራኤል ባለስልጣን ወታደሮች የ15ቱን ሟቾች አስከሬን ከአውሬ ለመጠበቅ በሚል አሸዋ ውስጥ ቀብረዋል ብለዋል።

ባለስልጣኑ አክለውም በማግስቱ ተሽከርካሪዎቹ ተነስተው ሟቾቹ የተቀበሩት መንገዱን ለማስለቀቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች በወቅቱ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ወደ አካባቢው ለማለፍ እንዲቻል ባለማድረጋቸው ወይም ትክክለኛውን ቦታ ማመላከት ባለመቻላቸው ሟቾቹ ግድያው ተፈጽሞ ሳምንት እስኪያልፈው ድረስ አልተገኙም ነበር።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ሠራተኞች አስከሬኖቹን ሲያገኝ የሬፋት ሬድዋን ተንቀሳቃሽ ስልክም አብሮ ተገኝቷል።

የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን አንድም የሕክምና ባለሙያ ከመሞቱ በፊት እጁ በካቴና አለመታሰሩን እና አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በቅርብ ርቀት እንዳልተተኮሰባቸው ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አንድ በሕይወት የተረፈ የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያ ለቢቢሲ አምቡላንሶቹ መብራታቸውን አብርተው እንደነበር፣ ባልደረቦቹ ከማንኛውም ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳልነበራቸው ተናግሯል።

የእስራኤል ጦር “የተፈጠረውን አንድ በአንድ እና የሁኔታዎችን አያያዝ በሚገባ ለመረዳት” ጉዳዩን “በጥልቅ ለመመርመር” ቃል ገብቷል።

የቀይ ጨረቃ እና ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ እየጠየቁ ነው።