የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

ከ 8 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን ለመቀበል ዳተኛ በመሆኗ ምክንያት የደቡብ ሱዳን ፓስፖርት ለያዙ የተሰጠ ማንኛውም ቪዛ መሰረዙን አስታወቁ።

ሩቢዮ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ አገራቸው ማንኛውም የደቡብ ሱዳን ዜጋ ወደ አሜሪካ በየትኛውም መንገድ እንዳይገባ እንደምታግድ ተናግረዋል።

“የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎቹን በወቅቱ ባለመቀበሉ” ለችግሩ ተጠያቂ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚከተሉት አዲሱ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ የተነሳ ሕገወጥ ስደተኞችን “በጅምላ ከአገር” እያስወጡ ነው።

“የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት አሜሪካን መጠቀሚያ ማድረግ የሚያቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ ሩቢዮ አስጠንቅቀዋል።

“አሜሪካም ሆነች ሌሎች ከአገራቸው የሚያስወጧቸውን ሰዎች አገራት ወድያውኑ መቀበል ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የተሰማው ደቡብ ሱዳን እንደገና ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።

አሜሪካ በቀጠናው ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት የካቲት 29 2017 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ያልሆኑ ዜጎቿ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛ ነበር።

ደቡብ ሱዳናውያን ቀደም ሲል በአሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ (TPS) ተሰጥቷቸው ለተወሰነ ጊዜ በአገሪቱ መቆየት ይችላሉ።

አሜሪካ ለደቡብ ሱዳናውያን የሰጠችው ጊዜያዊ ከለላ ሚያዝያ 25 2017 ዓ.ም. ያበቃ ነበር።

ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ተገንጥላ ነፃነቷን ያወጀችው እአአ በ2011 ነው።

ነገር ግን ልክ ከሁለት ዓመት በኋላ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርታ ከ400,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በ 2018 በሁለቱ መካከል የተደረሰው የስልጣን ክፍፍል ስምምነት ጦርነቱን እንዲቆም አድርጓል።

ነገር ግን የስምምነቱ ዋና ዋና ክፍሎች የሆኑት አዲስ ሕገ መንግሥት ማጽደቅ፣ ምርጫ እና የታጠቁ ቡድኖችን ወደ በአንድ ጦር ሠራዊት መቀላቀል የሚሉት አልተተገበሩም።

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በጎሳና በአካባቢ ተወላጆች መካከል አልፎ አልፎ የሚካሄደው ግጭት እንደቀጠለ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ከአሜሪካ በሚባረሩ ዜጎቻቸው ምክንያት ከመንግሥታት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።

በጥር ወር የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቻቸውን የጫኑ ሁለት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች አገራቸው እንዳያርፉ ከልክለዋል።

ፔትሮ ትራምፕ በኮሎምቢያ ላይ ከበድ ያሉ ታሪፎችን እና ማዕቀቦችን ለመጣል ቃል ከገቡ በኋላ ውሳኔያቸውን አጥፈዋል።