April 7, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ
ከሁለት ሳምንት በፊት ለፓርላማ በቀረበው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር የአዋጅ ረቂቅ የተካተተው እና “ለአደጋ ስጋት ምላሽ” የሚውል ገንዘብ ከግለሰቦች አንዲሰበሰብ የሚያዝዘው ድንጋጌ ጥያቄ ተነሳበት። የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ከሰራተኞች ደመወዝ እና ከግለሰቦች የሚጠበቀው መዋጮ መጠን፤ ወደፊት ውይይት ከተካሄደበት በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ የሚወሰን መሆኑን ገልጿል።
ለዝርዝር ዕይታ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ የተመራው አዋጅ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧዋቸው የተለያዩ አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” የሚውል ገቢ እንዲሰበስቡ ያስገድድዳል። ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጭ ለመሰብሰብ በአዋጁ ከተዘረዘሩ 15 አይነት አገልግሎቶች መካከል “የመንግስት እና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ ላይ የሚታሰብ” የሚለው ይገኝበታል።
አዋጁ የተመራለት የፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 29፤ 2017 ባዘጋጀው የአስረጂ እና የባለድርሻ አካላት መድረክ፤ ከተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የሚሰበሰበው ገቢ የግለሰቦችን የመክፈል አቅም ያገነዘበ መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦበታል። የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የህግ ዳይሬክተር አቶ አማረ ኢቲቻ፤ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ካቀረቡት አንዱ ናቸው።

አቶ አማረ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ለአደጋ ስጋት ፈንድ ገቢ እንዲሰበሰብባቸው ከሚጠበቁ አገልግሎቶች ውስጥ የተወሰኑትን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ባንክ ብድር፣ የዲጂታል ባንኪንግ እና የቴሌኮም አገልግሎት “የሌሎችንም ካየን ወደ ግለሰቦች ነው የሚሄደው” ያሉት አቶ አማረ፤ “ይህንን ሁሉ ግለሰቦች afford ማድረግ ይችላሉ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በዚህ የህግ ረቂቅ ላይ የተመላከቱት የተለያዩ የገቢ ምንጮች በተቋማት ላይ ሳይሆን “በተጠቃሚ ላይ እንዲሆን ተደርጓል” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ይህ አካሄድ ድርጅቶችን ገቢ ከማዋጣት “ነጻ እንዲሆኑ” (exempt) እንዳደረጋቸው መረዳታቸውንም አክለዋል። ድርጅቶቹ ገንዘቡን ከደንበኞቻቸው ላይ “ሰብስቦ” ከማስረከብ ባሻገር፤ “በልካቸው መሳተፍ የለባቸውም ወይ?” የሚል ተጨማሪ ጥያቄም ሰንዝረዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የህግ ዳይሬክተሩ፤ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ከተዘረዘሩ የገቢ ምንጮች ውስጥ “ከኮንትሮባንድ ንግድ የተያዘ ዕቃ በዓይነት ወይም በጨረታ ተሸጦ የሚገኝ” የሚለው ላይም ጥያቄ አንስተዋል። “ከህገ ወጥ እንቅስቃሴ ‘ገንዘብ አገኛለሁ’ ተብሎ ህግ አይወጣም፤ ህግ አይደነገግም። ኮንትሮባንድ የተከለከለበት ምክንያት አለው” ሲሉ ጉዳዩን አብራርተዋል።
“ከህገ ወጥ እንቅስቃሴ ‘ገንዘብ አገኛለሁ’ ተብሎ ህግ አይወጣም፤ ህግ አይደነገግም። ኮንትሮባንድ የተከለከለበት ምክንያት አለው። ኮንትሮባንድ የተከለከለበት ምክንያት የሀገር ውስጥ ገበያን እንዳያቀጭጭ ነው። ስለዚህ ዝም ብዬ ገልብጬ ሳየው፤ ኮንትሮባንድን ማደፋፈር ይሆናል።”– አቶ አማረ ኢቲቻ፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የህግ ዳይሬክተር
“ኮንትሮባንድ የተከለከለበት ምክንያት የሀገር ውስጥ ገበያን እንዳያቀጭጭ ነው። ስለዚህ ዝም ብዬ ገልብጬ ሳየው፤ ኮንትሮባንድን ማደፋፈር ይሆናል። ስለዚህ እንደ አንቀጽ ከማስቀመጥ ይልቅ፤ ‘በልዩ ልዩ የገቢ ምንጭ’ ተብሎ እዚያ ውስጥ ስሙን ሳንጠቅስ ብንጠቀም አይሻልም ወይ?” ሲሉ አማራጭ ያሉትን ሃሳብ አጋርተዋል።
ከገንዘብ ሚኒስቴር እንደመጡ የተናገሩት አቶ ሀቫና ሆርዶፋም፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ሰጥተዋል። የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሽያጭ በተመለከተ በአዋጅ ረቂቁ የሰፈረው ድንጋጌ “በደንብ ሊታይ” እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ሀቫና፤ “እንዲያውም ይሄ አንቀጽ እዚህ ውስጥ መቀጠል የለበትም ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
ከኮንትሮባንድ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ፤ “በአንድም በሌላም መንገድ” ለዕቃው የወጣው ወጪ “ከተቀነሰ” በኋላ በቀጥታ ወደ መንግስት ግምጃ ቤት እንደሚሄድም አቶ ሀቫና በዚሁ አስተያየታቸው ላይ ጠቅሰዋል። “በረቂቁ ላይ በፌደራል መንግስት፣ ከድሬዳዋ እና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ከጠቅላላ አመታዊ በጀት በድርሻ [ያዋጣሉ] የሚል አለ። ወደ መንግስት ትሬዠሪ ከሄደ ደግሞ፤ እዚያ ውስጥ ያርፋል የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

በጉምሩክ ኮሚሽን የተወረሱ ዕቃዎች በሽያጭ ከሚወገዱበት በተጨማሪ “በአይነት ለተቋማት የሚሰጡበት አሰራር” እንዳለ ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስቴሩ ተወካይ፤ በአዋጅ ረቂቁ ላይ “በአይነት ገቢ የሚደረግበት ሁኔታ ሊታይ እንደሚገባ” ጠቁመዋል። ኮሚሽኑ የወረሳቸው ንብረቶች በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በበጀትነት ተመዝግበው ለተለያዩ መንግስታዊ ድርጅቶች እንደሚሰጥ በመጥቀስም ጥያቄያቸውን አስከትለዋል።
“ለምሳሌ ተሽከርካሪ ሊሆን ይችላል። ያ ተሽከርካሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ለራሱ ለጉምሩክ ኮሚሽን ሊሰጠው ይችላል። ይሄ ሲሰጠው ገንዘብ ሚኒስቴር የሚያደርገው ምንድን ነው? በህግ አግባብ መሰረት የተወረሰውን ተሽከርካሪ ተቀብሎ፤ በተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ መሰረት ለተቋማት ያድላል። ገንዘብ ሚኒስቴር እንደ በጀትነት መዝግቦ ነው። ከዚህ ላይ እንዴት ነው የምንቆርጠው? ከዚህ ላይ ቆርጠን፣ ከዚያው ከመንግስት ተቋም ላይ በአይነት ከተገኘ ገቢ ላይ ወስደን፣ ለፈንዱ እንዴት ነው ምናዋጣው” ሲሉ አቶ ሀቫና ጠይቀዋል።
ለአስተያየቶቹ ምላሽ የሰጡት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፤ ከዚህ ቀደም በደርግ የስልጣን ዓመታት “ሰራተኛው የአንድ ወር ደመወዙን በአንድ አመት እየከፈለ” የሚደጉምበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን በአዋጅ ረቂቅ ውስጥ የተካተተው ድንጋጌ፤ ከዚህ ቀደም “ያልነበረ ልምምድ” አለመሆኑንም አስረድተዋል።

“የተለያየ ስም አላቸው እንጂ በየቦታው አሉ። [ህዝቡ] በየቦታው የሚረዳዳበት ሁኔታ አለ። ሰዉ ለለቅሶ፣ ለሰርግ ሲተጋገዝ ነው የኖረው። ስለዚህ ይሄ የሚተጋገዘውን ነገር፣ በተወሰነ ደረጃ አባካኝነቱን ቀንሰን፣ ወደዚህ ሰብሰብ ብናደርግ፤ ከችግሮቻችን እንወጣለን። ዋናው የአደጋ ስጋት ፈንድ ጋር ያለው ነገር፤ የአካታችነት ነው። የዜጋም ተቋማትም ተሳትፎ ምክንያት አንዱ ሌላውን ለመጥቀም ሳይሆን፤ ሁላችንንም የተሳተፍንበት፣ ሁላችንንም እንዲጠቅም በሚል ነው” ሲሉ ከመዋጮው ጀርባ አለ ያሉትን አመክንዮ አብራርተዋል።
ለአደጋ ስጋት ፈንድ የሚሰበሰበው ገንዘብ “ጫና በማይፈጥር”፣ “የአገልግሎት ተጠቃሚነትን በማያስወግድ መንገድ ነው መሰራት ያለበት” የሚል መርህ መቀመጡንም ኮሚሽነር ሽፈራው አመልክተዋል። የድርጅቶች “የማህበራዊ ኃላፊነት” (corporate social responsibility) ጉዳይ በአዋጅ ሳይሆን፤ በተቋማቱ በኩል “በበጎ አድራጎት መንገድ የሚሰሩት በመሆኑ” በዚያው አግባብ እንደሚታይ አስረድተዋል።
“[ግለሰቦች] privilege በሆኑበት የአገልግሎት ጣቢያ ላይ በጣም መለስተኛ እና አነስተኛ የአገልግሎት ድርሻ ቢኖራቸው፤ ይሄ ለግለሰቡ በጣም ትንሽ ነገር ቢሆንም ሰፊው የአገልግሎት ተጠቃሚ በዚህ ጉዳይ ላይ አካል እንዲሆን ብናደርግ የምንስበውን ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅምም የምናስበውን ችግር ልንወጣ እንችላለን የሚል ነው። ግልጽ የሆነ አቋምም ግልጽ የሆነ አረዳድ መውሰድ ይጠይቃል” ሲሉ ኮሚሽነሩ አክለዋል።

ዶ/ር ሽፈራው ግለሰቦች የሚያዋጡትን ገቢ መጠን በተመለከተ፤ አዋጁን ለማስፈጸም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ ወደፊት የሚታይ እንደሆነ ጠቁመዋል። “አሁን ምን እንደሚሆን [አናውቅም]። ምንድን ነው የሚወሰነው? የሚለው [የለም]” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ሆኖም “በራስ አቅም” ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ገቢን በተመለከተ፤ የማይመለከተው ተቋም እና ዜጋ ሊኖር እንደማይገባ አሳስበዋል።
ለፓርላማ በቀረበው የአዋጅ ረቂቅ ላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች ሽያጭ የተጠቀሰበት ምክንያት፤ “ከአዋጅ ውጭ በሆነ መንገድ ገንዘብ የሚሰበሰብበትን ቋት ማዘዝ ስለማይቻል ነው” ሲሉም የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ምላሽ ሰጥተዋል። “ይሄንን [በአዋጁ] አመላክተን ካልሄድን፤ በኋላ ይህ ገንዘብ ከገንዘብ ሚኒስቴር ቋት ወጥቶ ወደ አደጋ ምላሽ ፈንድ የሚሄድበት እድል እንዳይስተጓጎል ነው” ሲሉ አንቀጹ በአዋጅ ረቂቁ ላይ እንዲካተት የተደረገበትን ምክንያት አስረድተዋል።
“ሁለቱም ሀብቶች፤ የመንግስት ሀብቶች ናቸው። ግልጸኝነቱ እና አሰራሩን በሙሉ ተከትሎ ይሄዳል። እዚህ ስለተሰበሰበ ‘የመንግስት ነው’፤ ‘እዚያ ስላልተሰበሰበ የመንግስት ነው’ የሚባል ነገር ስለሌለ ነው” ሲሉም ኮሚሽነሩ አክለዋል። ሆኖም ኮንትሮባንድ የተመለከተውን ድንጋጌ “እንዴት አርገን እንጻፈው” የሚለው ላይ መነጋገር እንደሚቻል ዶ/ር ሽፈራው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)