
ከ 7 ሰአት በፊት
የዩክሬን ኃይሎች ለሩሲያ ሲዋጉ የነበሩ ሁለት ቻይናዊያንን በዶኔትስክ ግዛት በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናገሩ።
ማክሰኞ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት በሩሲያ ጦር ውስጥ የሚዋጉ ቻይናዊያን ወታደሮች “ሁለት ብቻ አይደሉም” ብለዋል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሀ እንዳሉት በዩክሬን ግዛት የሚዋጉ ቻይናዊያን ወታደሮች “ቻይና ለሰላም ያላትን አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ናቸው” ብለው ኪየቭ የሚገኘው የቻይና ልዑክ ለማብራሪያ እንደተጠራ አሳውቀዋል።
ዩክሬን፤ ቻይና በጦርነቱ ለሩሲያ ድጋፍ ትሰጣለች በማለት ወቀሳ ስታቀርብ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ዩክሬን ያቀረበችውን ወቀሳ ተከትሎ እስካሁን ከሞስኮም ሆነ ከቤይጂንግ ኦፊሴላዊ ምላሽ አልተሰጠም።
ዜሌንስኪ በኤክስ ገፃቸው በፃፉት መልዕክት ቻይናዊያኑ ወታደሮች በሀገሪቱ ምስራቅ ዶኔትስክ ግዛት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰው የባንክ ካርድ እና ሌሎች “ግላዊ ማስረጃዎች” ይዘው ነበር ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ እንዳሉት የዩክሬን ወታደሮች ከስድስት ቻይናዊያን ወታደሮች ጋር ከገጠሙ በኋላ ሁለቱን መማረክ ችለዋል።
ዜሌንስኪ በለጠፉት ቪድዮ ላይ ቻይናዊ ወታደሮች ከተባሉት ግለሰቦች መካከል አንዱ በማንዳሪን ቋንቋ በቅርቡ ስላደረገው ውጊያ ሲያወራ ይደመጣል።
“ያለን መረጃ እንደሚያሳየው በወራሪው ኃይል ውስጥ ያሉ ቻይናዊያን ዜጎች ሁለት ብቻ አይደለም” ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
“ሩሲያ ከቻይና እና ከሌሎች ሀገራት ጋር አውሮፓ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የምታደርገው ትስስር ፑቲን ጦርነቱን ለመቋጨት ፍላጎት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው” ሲሉ ዜሌንስኪ አክለዋል።
- ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ “ከሀገር ሉዐላዊነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እንዲቆሙ የማድረግ” ኃላፊነት ተጣለባቸው8 ሚያዚያ 2025
- የቻይና እና የአሜሪካ የንግድ ጦርነት ወዴት ያመራል?ከ 9 ሰአት በፊት
- ካለፉት አሥር ዓመታት በበለጠ በዓለም ዙሪያ የሞት ቅጣት ለምን ጨመረ?ከ 8 ሰአት በፊት
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት “ዩናይትድ ስቴትስ፣ አውሮፓ እና ሌሎች ሰላም የሚፈልጉ የዓለም ሀገራት” ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ሀለቱ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ደኅንነት አገልግሎት ሥር መሆናቸውን ጠቁመው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ አሳውቀዋል።
ማክሰኞ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ ሁኔታው “የሚያሳስብ” ነው ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ ቻይና፣ ሩሲያ በዩክሬን በምታደርገው ጦርነት “ቀንደኛ ተዋናይ” ናት ብለው ለጦርነት የሚያገለግሉ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ታቀርባለች ሲሉ ወቅሰዋል።
የፈረንሳዩ ሌ ሞንድ ጋዜጣ ከዚህ በፊት እንደዘገበው ዱይን በተባለው ቻይና ውስጥ ብቻ በሚያገግለው ማኅበራዊ ሚድያ አማካኝነት ቢያንስ 40 ሰዎች በሩሲያ ለመዋጋት መመዝገባቸውን አሳውቆ ነበር።
የኪየቭ እና የምዕራባዊያን ሀገራት ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ድጋፍ እንዲሰጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ልካለች ብለው መውቀሳቸው አይዘነጋም።
ዜሌንስኪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ሰሜን ኮሪያዊያን በኩርስክ ግዛት ድንበር ላይ ነበር ሲዋጉ የነበሩት። ቻይናዊያኑ ግን የዩክሬንን ግዛት ዘልቀው ነው የተዋጉት” ብለዋል።
ባለፈው ጥር ዩክሬን ሁለት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ማለቷ ይታወሳል።
ምንም እንኳ ቤጂንግ እና ሞስኮ በፖለቲካው እና በምጣኔ ሀብቱ ቅርርብ ያላቸው ወዳጅ ሀገራት ቢሆኑም ቻይና በጦርነቱ ገለልተኛ እንደሆነች እና ለሩሲያ ወታደራዊ መሣሪያ አለማቅረቧን ስታስተባብል ቆይታለች።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በ2022 ነው ሁሉን አቀፍ ጦርነት ዩክሬን ላይ ያወጁት። ሩሲያ በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።