
ከ 8 ሰአት በፊት
የህንድ ፖሊስ እንግሊዛዊ ዶክተር መስሎ ሲያጭበርብር ነበር ያለውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ግለሰቡ በሰራው ቀዶ ጥገና የሰው ሕይወት ጠፍቷል በሚል ነው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው።
ናሬንዳ ቪክራማዲትያ ያዳቭ አሊያም በቅፅል ስሙ ዶ/ር ኤን ጆን ካም በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የልብ ቀዶ ጥገና ባለሙያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
ፖሊስ ግለሰቡን በማጭበርበር እና ሀሰተኛ የምስክር ወረቀት በማቅረብ የከሰሰው ሲሆን የ53 ዓመቱ ተጠርጣሪ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሀሰተኛ የሕክምና ማስረጃ ሲያገለግል ቆይቷል ብሏል።
ግለሰቡ በዩናይትድ ኪንግደም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆስፒታል የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ጆን ካም የተባሉ ጉምቱ የልብ ቀዶ ጥገና ባለሙያን ስም ወስዶ ሲጠቀም ነበር ተብሏል።
ያዳቭ የቀረቡበትን ክሶች አስተባብሏል።
ሰኞ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ ከሰዓታት በፊት “ሌላ የልብ ቀዶ ጥገና ባለሙያ አስመስሏል” ብለውኛል ላላቸው ግለሰቦች እና መገናኛ ብዙኃን የ50 ሚሊዮን ሩፒ ማስጠንቀቂያ ልኳል።
ያዳቭ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ያገለገለበት ዳሞህ ከተማ የሚገኘው ሚሽን ሆስፒታል ስለግለሰቡ ሀሰተኛ የምስክር ወረቀቶች የማውቀው ነገር የለም ብሏል።
“ማንም ሰው ሀሰተኛ ዶክተር ነው ብሎ የጠረጠረ የለም። ሥራው ላይ ጎበዝ ነው። ሁኔታውም ብዙ እውቀት እንዳለው ፕሮፌሰር ነው” ሲል ሆስፒታሉ ለኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ ተናግሯል።
- ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ “ከሀገር ሉዐላዊነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እንዲቆሙ የማድረግ” ኃላፊነት ተጣለባቸው8 ሚያዚያ 2025
- የቻይና እና የአሜሪካ የንግድ ጦርነት ወዴት ያመራል?ከ 8 ሰአት በፊት
- ካለፉት አሥር ዓመታት በበለጠ በዓለም ዙሪያ የሞት ቅጣት ለምን ጨመረ?ከ 8 ሰአት በፊት
ግለሰቡ ሀሰተኛ ዶክተር ሊሆን እንደሚችል መጀመሪያ የተነገረው ባለፈው የካቲት ሲሆን የአካባቢው ባለሥልጣናት መሞታቸውን ተከትሎ ነው ወሬው የተናፈሰው።
“ጥርጣሬ ገብቶን ኢንተርኔት ላይ ስናፈላልግ ሌሎች ሶስት ግዛቶች ውስጥ ክስ ቀርቦበታል” ሲሉ የአካባቢው ባለሥልጣን ተናግረዋል።
በምርመራ ሊረጋገጥ እንደቻለው ያዳቭ የካቲት ላይ ያለምንም ምክንያት ሥራውን አቋርጦ “አድራሻው ጠፍቶ” ነበር።
ነገር ግን ሰኞ አመሻሹን ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
“ተጠርጣሪው 64 ሕክምናዎችን ያከናወነ ሲሆን 7 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል” ሲሉ የፖሊስ ኃላፊ ሽሩት ኪርቲ ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግረዋል።
እስካሁን ድግሪዎቹ ትክክለኛ ይሁኑ ሀሰተኛ ያልተረጋገጠ ቢሆንም ፖሊስ ግን ለእያንዳንዱ ተማሪ የሚሰጠው ልዩ መለያ ቁጥር የለውም ብሏል።
ግለሰቡ ዩናይትድ ኪንግደም አቅንቶ በፕሮፌሰር ኤ ጆን ካም ሥር እንደሰለጠነ፤ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ጀርመን እና ስፔን እንዳገለገለ ይናገራል።
በ2023 ፕሮፌሰር ኤን ጆነ ካም በተሰኘ ስም የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) አካውንት የከፈተ ሲሆን ትክክለኛው ፕሮፌሰር ካም ገፁ የሳቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በ2019 ለሥራ የጋበዘውን እንግሊዛዊ ዶክተር አግቷል በሚል ለእስር ተዳርጎ ያውቃል። በ2014 ደግሞ “በፕሮፌሽናል የሥነ-ምግባር ጉድለት” ምክንያት በህንድ የመደኃኒት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ለአምስት ዓመታት ታግዶ ነበር።
በ2013 በኡታር ፕራዴሽ ግዛት በማጭበርበር እና በማታለል የተከሰሰ ቢሆንም ጥፋተኛ አልተባለም።