
ከ 9 ሰአት በፊት
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ እንዳለው ባፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት (2024) በመላው ዓለም በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት የሞት ቅጣት እና ስቅላት የተፈጸመባቸው ሰዎች 1,518 ናቸው።
ይህም አሃዝ ቀደም ካለው ዓመት በ32 በመቶ ጨምሯል። የሞት ቅጣት የሚፈጽሙ አገራት ቁጥር ግን በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል።
በ2024 የተመዘገባው ቁጥር ከ2015 ጀምሮ ካሉት ዓመታት ከፍተኛው። የሞት ቅጣት የሚፈጽሙ አገራት ቁጥር ከ16 ወደ 15 ቀንሷል።
በርካታ ሰዎችን በሞት ትቀጣለች ተብሎ የሚታሰበው ቻይና ብትሆንም ተግብራዊ ያደረገችውን የሞት ቅጣት የሚያሳይ ይፋዊ ቁጥር ከአገሪቱ ማግኘት አይቻልም።
ቻይና ቁጥሩን እንደ አገራዊ ምሥጢር ነው የምትይዘው።
ቬትናት እና ሰሜን ኮሪያም ብዙ ሰዎችን በሞት ቢቀጡም ብዛቱን በይፋ አያሳውቁም።
በቁጥር የሚታወቁ ሰዎችን በሞት በመቅጣት ኢራን አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ካልማርድ “የሞት ቅጣት ቁጥር የጨመረው በኢራን፣ በኢራቅ እና በሳዑዲ አረቢያ ምክንያት ነው። እነዚህ አገራት ከ91 በመቶ በላይ የተመዘገቡ የሞት ቅጣቶችን ፈጽመዋል። ይህም ሕገ ወጥ ሲሆን፣ “ክሶቹ ከዕፅ ዝውውር እና ከሽብር ጋር ይገናኛሉ” ይላሉ።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 30 ሴቶችን ጨምሮ 972 ሰዎችን ኢራን በሞት ቀጥታለች። በ2023 ደግሞ 853 ሰዎች ሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።
የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በአገሪቱ ባለው ፖለቲካዊ ነውጥ ምክንያት የሞት ቅጣት ቁጥር ጨምሯል።
የኢራን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቦራህማን ቦሮማንድ “ተቃውሞዎች ከመበራከታቸው ጋር በተያያዘ የሞት ቅጣት ቁጥር ጨምሯል” ይላሉ።
- አሜሪካ ከ15 ዓመታት በኋላ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው በአልሞ ተኳሾች የሚፈጸም የሞት ቅጣት9 መጋቢት 2025
- የሞት ፍርድ በኢትዮጵያ እንዴት ይፈጸማል? ምን ያህልስ ተቀባይነት አለው?19 ሰኔ 2024
- የትኞቹ አገራት የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ምን ያህል ሰዎችስ ተገደሉ?27 ጥር 2024
በሳዑዲ አረቢያ 345 ሰዎች፣ በኢራቅ ደግሞ 63 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል።
ኢራን እና ሶማሊያ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ አራት ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ፈጽመዋል።
ኢራን እና አፍጋኒስታን በአደባባይ የሞት ቅጣት ፈጽመዋል።
በአምነስቲ የሞት ቅጣትን የሚከታተሉት ቺያራ ሳንጊሮጎ እንዳሉት በ2024 “በቻይና የተፈጸሙ በሺዎች የሚቆጠሩ የሞት ቅጣቶች እና ስቅላቶች አልተቆጠሩም።”
“መንግሥት ይዞታውን ለማጠናከር የሞት ፍርድን እየተጠቀመ መሆኑን አስተውለናል። ወንጀል እና አመጽ የተከለከለ ነው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይጠቀሙበታል” ይላሉ።
ቻይና በሙስና እና በዕፅ ዝውውር የተከሰሱ ሰዎች ላይ ሞት ትፈርዳለች። ይህም የመንግሥታቱን ድርጅት መርኅ የሚጥስ ነው።
የሞት ቅጣት “እጅግ አደገኛ በሆኑ ወንጀሎች” ምክንያት የሚፈረድ መሆኑ ተደንግጓል።
ቻይና ለዓመታት የሞት ፍርድን ተግብራለች። በአውሮፓውያኑ 1983 በወንጀለኛ ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ጀምራለች።
ሆኖም ግን አደገኛ ላልሆኑ የመኪና እና የቀንድ ከብት ስርቆትም ሞት ትፈርዳለች።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደመዘገበው በ1996 “ፀረ አደንዛዥ ዕፅ ቀን” በሚል በአንድ ቀን 230 የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።
የሞት ቅጣት እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ?
በሆንግ ኮንግ የዩኒቨርስቲ መምህር ፕሮፌሰር ማይክል ማዮ እንዳሉት፣ የሞት ቅጣት እየጨመረ የመጣባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው።
በቻይና 40 ዳኞች እና ጠበቆችን ቢያነጋግሩም ትክክለኛውን የሞት ቅጣት ቁጥር አልደረሱበትም።
በቻይና የሞት ቅጣትን የተመለከቱ መረጃዎችን በመዳፈናቸው ምክንያት አጥኚዎች ትክክለኛውን አሃዝ አያውቁም።
“የተራዘመ የሞት ቅጣት የሚፈረደው በአፋጣኝ መቅጣት አስፈላጊ በማይሆንበት ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ሕጉ ይደነግጋል። የቻይና ዳኞች አስፈላጊ ነው ብለው የሚወስዱት በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ግልጽ አይደለም” ይላሉ ፕሮፌሰር ማይክል።
በአሜሪካ ያለው የመብት ተሟጋች ድርጅት ዱይ ሁዋ እንዳለው በቻይና በ2002 የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ሰዎች 12,000 ሲሆኑ በ2018 ወደ 2,000 ዝቅ ብሏል።
በቻይና የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የተስተዋለው ለውጥ ቁጥሩ እንዲቀነስ አስችሏል።
ተከሳሽ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለቴ ይግባኝ ማለት ይችላል። በሞት የሚያስቀጡ ወንጀሎች 74 የነበሩ ሲሆን፣ ከ2011 እስከ 2015 በተደረገ የሕግ ማሻሻያ ቁጥሩ ወደ 46 ቀንሷል።
“ግድያና ከዕፅ ጋር የተያያዘ ክስ ናቸው በዋናነት ለሞት ቅጣት የሚያበቁት” ሲሉ ፕሮፌሰሯ ያስረዳሉ።
በቀጣይ ዓመታት ከቴክኖሎጂ እድገትና የአኗኗር ለውጥ እንዲሁም የሕግ መሻሻል ጋር በተያያዘ ለውጥ እንደሚኖር ተስፋ አላቸው።
“ከአደንዛዥ ዕፅ ምርት እና ዝውውር ጋር የተያያዘ ክስ እየቀነሰ ነው። ከግድያ ጋር በተያያዘም እንዲሁ ቁጥሩ እየቀነሰ መጥቷል። በቀጣይ ዓመታት አሁን ካለውም ዝቅ እንደሚል እንጠብቃለን” ሲሉ ያስረዳሉ።
በቻይና ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙበት ምጣኔ 100 በመቶ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2022፤ ከ1,431,585 ተከሳሾች መካከል 631 ሰዎች ብቻ ጥፋተኛ ሆነው አለመገኘታቸውን በአሜሪካ ያለው የመብት ተሟጋች ድርጅት ዱይ ሁዋ መዝግቧል።
ጥፋተኛ ሆኖ የመገኘት መጠን ጨምሯል?
በቻይና ዢጄንግ ግዛት ዋንዡ ከተማ ከ1995 እስከ 1999 ተከሳሾች በአጠቃላይ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ጥናት ያሳያል።
“በቻይ የፍትሕ ሥርዓት አንድ ጉዳይ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ነው ቅድመ ምርመራ የሚደረግበት። ተከሳሾች ጥፋተኛ የመባል ዕድላቸውም በጣም ከፍተኛ ነው” በማለት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
ይህም በሞት ፍርድ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ነው።
በዚህ መካከል ፍትሕ የተዛባ የሚሆንባቸው ጉዳዮች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
በ2016 (እአአ) አንድ የ18 ዓመት ወጣት በመድፈር እና በግድያ ወንጀል በስህተት ሞት ተፈርዶበት 27 ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው ሲባረሩ፣ የወጣቱ ቤተሰቦች ካሳ ተከፍሏቸዋል።
በጃፓንም ጥፋተኛ ሆኖ የመገኘት ምጣኔው 99 በመቶ ነው። ሆኖም ከ2022 ወዲህ የሞት ቅጣት አልተፈጸመም።
ባለሙያዎች የቻይናን የሞት ቅጣት ቢኮንኑም በአገሪቱ የሞት ፍርድ በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉት ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ።