ምግብ እያበሰለች ያለች ግለሰብ

ከ 8 ሰአት በፊት

ዓለም እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችው የእርዳታ እገዳ ላይ እርምጃ እንዲወስድ የረድዔት ተቋማት ሲያሳስቡ፤ ግዛቲቷ ‘የግድያ ሜዳ ሆናለች’ ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ተናገሩ።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ “እርዳታ ሙሉ በሙሉ ቀጥ ብሏል እንዲሁም አስፈሪ ደጃፎች ተከፍተዋል” ሲሉ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሳስበዋል።

“ጋዛ የግድያ ሜዳ ናት፤ ሰላማውያን ዜጎች መቋጫ በሌለው የሞት ዑደት ውስጥ ናቸው” ሲሉ ማክሰኞ ዕለት የሁኔታውን አስከፊነት ተናግረዋል።

ዋና ጸሐፊው አስተያያታቸውን የሰጡት ስድስት የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ኃላፊዎች የምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ለፍልስጤማውያን እንዲደርስ የዓለም መሪዎች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ከተማጸኑ በኋላ ነው።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በጋዛ በቂ ምግብ እንዳለ አስታውቆ ዋና ጸሐፊውን “የእስራኤልን ስም በማጥፋት” ከሷቸዋል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ምንም አይነት እርዳታ እንዳይገባ እገዳ ከጣለች ከወር በላይ አስቆጥሯል።

እስራኤል በጋዛ ላይ ሙሉ የእርዳታ እገዳ እንዲሁም እንደ አዲስ ጥቃቷን የጀመረችው የጋዛ የተኩስ አቁም የመጀመሪያ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።

እስራኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነትን መራዘምን ሐማስ እንዲቀበል ትፈልጋለች።

ሐማስ በበኩሉ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት ያለመው ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ ይሁን እያለ ነው።

ሆኖም እስራኤል እና አሜሪካ ስምምነቱን በመቀየር አንደኛው ምዕራፍ እንዲራዘም እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

እስራኤል በአየር እና በመሬት የተቀናጀ ድጋሚ ጥቃት ከጀመረች በኋላ 1 ሺህ 449 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቀቋል።

የእስራኤል ጦር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አልፈጸምኩም ሲል ያስተባብላል።

ጉቴሬዝ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር እስራኤል ጋዛን እንደያዘ አካል በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የምግብ እና የህክምና አቅርቦቶች ለህዝቡ መድረሱን የማረጋጋጥ ግዴታ አላባት ብለዋል።

“አሁን እየተከሉት ያለው መንገድ በአለም አቀፍ ህግ እና ታሪክ እይታ ፈጽሞ የማይታገሰው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በጋዛ ምንም አይነት የእርዳታ እጥረት የለም ሲል አስተባብሏል።

ሰኞ እለት ስድስት የተባበሩት መንግሥታትት ድርጅት ኤጀንሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ጋዛውያን መውጫ በሌላቸው ሁኔታ በቦምብ እየተደበደቡ እንዲሁም ድጋሜ ለረሃብ እንዲጋለጡ ተደርገዋል” ብለዋል።

መግለጫውን ያወጡት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም የጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ እና የተባበሩት መንግሥታት የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ ናቸው።

እስራኤል በጣለችው እገዳ ምክንያት በጋዛ ያሉ ሁሉም በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ ዳቦ ቤቶች ተዘግተዋል፣ በርካታ ገበያዎች ባዶ ሆነዋል፤ እንዲሁም ሆስፒታሎች ያላቸው መድኃኒቶች ተመናምኗል።

“እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችው ጥብቅ እገዳ ሁለተኛ ወሩን እያስቆጠረ ነው። የዓለም መሪዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ መሰረታዊ መርሆዎች እንዲከበሩ በአስቸኳይ እና በቆራጥነት እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን” ብለዋል ተቋማቱ።

የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ባሉት 18 ወራት ዩኒሴፍ 18 ሺህ ህጻናት መገደላቸውን፣ ከ34 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን እንዲሁም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በተደጋጋሚ መፈናቀላቸውን ገልጿል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ50 ሺህ 399በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።