የሁለቱ አገራት መሪዎች

ከ 8 ሰአት በፊት

ሁለቱ ባለግዙፍ ምጣኔ ኃብቶች አሜሪካ እና ቻይና ተፋጠዋል።

በሁለቱ ታላላቅ ምጣኔ ኃብቶች መካከል ያለው የንግድ ጦርነት የመቀዛቀዝ ምልክት የሚያሳይ አይመስልም።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉት ታሪፍ በእጥፍ ይጨምራል ብለው ዝተዋል። ትራምፕ ከዛቱ ከሰዓታት በኋላ ቻይና ፍንክች እንደማትል አስታውቃለች።

እስከ መጨረሻው ለመታገል ቃል ገብታለች።

ትራምፕ እንዳስፈራሩት በቻይና ላይ ታሪፉን እጥፍ የሚያደርጉት ከሆነ ወደ 104 በመቶ ይሆናል ማለት ነው።

ቻይና ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች፣ ቪዲዮ ጌምን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ለአሜሪካ ትልካለች።

ትራምፕ እነዚህን ተጨማሪ ታሪፎች ተግባራዊ ለማድረግ እስከ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።

ቻይና የጣለችውን 34 በመቶ ታሪፍ እንድታነሳ ትራምፕ በማስፈራራት ጭምር እየጠየቁ ይገኛሉ።

አገራቱ ከያዙት አቋም ፈቀቅ ይሉ ይሆን?

“ቻይና ታሪፉን በብቸኝነት ታነሳለች ብሎ ማሰብ ስህተት ነው” በማለት ‘ዘ ኮንፈረንስ ቦርድ’ በተሰኘው የምርምር ተቋም የቻይና ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አልፍሬዶ ሞንቱፋር ሄሉ ይናገራሉ።

አክለውም ይህ ሁኔታ “ቻይናን ደካማ አድርጎ ከመሳል በተጨማሪ አሜሪካ መያዣ የሚሆን እና የበለጠ እንድትጠይቅ የሚያስችል አቅምን ይሰጣታል። በአሁኑ ወቅት ረዘም ወዳለ የምጣኔ ኃብት ቀውስ ሊመራ የሚችል ችግር ላይ ደርሰናል” ይላሉ።

ትራምፕ ከመቶ በላይ በሚሆኑ አገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ የዓለም አክስዮን ገበያ አሽቆልቁሏል። በተለይም የእስያ አክስዮን ገበያ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ በከፋ ሁኔታ የወረደ ሲሆን፤ ማክሰኞ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. በተወሰነ መጠን አገግሟል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ ቻይና 34 በመቶ ታሪፍ በመጣል አጸፋውን መልሳለች። ትራምፕ ቻይና የጣለችውን ታሪፍ የማታነሳ ከሆነ 50 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ በመጣል የበለጠ አጻፋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲሉ ዝተዋል።

በአሁኑ ወቅት የዓለም የንግድ ሁኔታ እና ገበያ አጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ትራምፕ የጣሉት ታሪፍ ረቡዕ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።

በርካታ የእስያ ምጣኔ ኃብቶች በዚህ ታሪፍ ይመታሉ።

በቻይና ላይ የተጣለው ታሪፍ ወደ 54 በመቶ ከፍ የሚል ሲሆን፣ ቬትናም 46 በመቶ እንዲሁም ካምቦዲያ 49 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ሁኔታዎች እየሄዱበት ያለው ፍጥነት አስጨንቋቸዋል።

መንግሥታት፣ ገበያዎች፣ ባለሃብቶች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ሁኔታዎችን ለማስተካከልም ሆነ ለየት ላለ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ለመዘጋጀት ጊዜ አላገኙም።

የእስያ የአክስዮን ገበያ
የምስሉ መግለጫ,የእስያ የአክስዮን ገበያ

ቻይና ለተጣለባት ታሪፍ የሰጠችው ምላሽ

ቻይና ለመጀመሪያው ዙር የትራምፕ ታሪፍ በተወሰኑ የአሜሪካ ምርቶች ላይ አጻፋዊ ታሪፍ በመጣል ምላሽ ሰጥታለች።

በተጨማሪም ብርቅዬ የብረት ማዕድናት ላይ የወጪ ንግድ ቁጥጥር እንዲሁም ጉግልን ጨምሮ በአሜሪካ ተቋማት ላይ ገበያውን በበላይነት የመቆጣጠር ሁኔታ ላይ ምርመራ ከፍታለች።

ከዚህም በተጨማሪም ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

ቻይና የመገበያያ ገንዘቧ ዩዋን እንዲዳከም ያደረገች ሲሆን፣ ይህም የወጪ ንግዷን የበለጠ ሳቢ ያደርገዋል። ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ኢንተርፕራይዞች ገበያውን ለማረጋጋት በሚመስል መልኩ አክሲዮኖችን እየገዙ ነው።

ቻይና ለአሜሪካ ከፍተኛ ምርቶችን በመላክ በቁንጮነት ተቀምጣለች።

ለቻይናም የአሜሪካ ገበያ ትልቅ ስፍራ አለው።

“በአሁኑ ወቅት ቀውሱን መሸከም የሚችለው ማን ነው የሚል ጨዋታ ነው እያየን ያለነው። በየትኛውም በኩል የሚያተርፍ የለም” ይላሉ በፒተርሰን ኢንስቲትዪት የአሜሪካ- ቻይና የንግድ ባለሙያ ሜሪ ላቭሊ።

የምጣኔ ኃብቷ እንኳን ቢያሽቆለቁል ቻይና ይህንን “የአሜሪካ ጥቃት ነው ብላ የምታምነውን ነገር ላለመቀበል የትኛውንም ሁኔታ ልትቋቋም ትችላለች” ይላሉ።

ቻይና የወጪ ንግዷ የሚያሽቆለቁል ከሆነ ወሳኝ የሆነው የገቢ ምንጯ መጎዳቱ የማይቀር ነው።

ለቻይና ምጣኔ ኃብት በከፍተኛ ሁኔታ መመንደግ የወጪ ንግዷ ለረጅም ጊዜ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

አገሪቷ ምንም እንኳን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እና የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመጨመር የገቢ ሁኔታዋን ለማስፋፋት እየሞከረች ቢሆንም፣ የወጪ ንግዷ አሁንም መሠረታዊ ነው።

በቻይና ላይ የተጣሉት ታሪፎች መቼ ተጽዕኗቸው ሊታይ ይችላል ለሚለው በቅርቡ እንደሚሆን በሃርቫርድ ኬኔዲ ስኩል፣ የሞሳቫር ራህማኒ የንግድ እና የመንግሥት ማዕከል ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት አንድሩ ኮሊየር ያስረዳሉ።

“ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በአገሪቱ የምጣኔ ኃብት መቀዛቀዝ እና ገቢ መቀነስ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ አጣብቂኝ የሆነ ምርጫ ይገጥማቸዋል” ይላሉ።

ቻይና የአለማችን ትልቋ ወጪ ንግድ የምታደርግ አገር ናት

ታሪፉ በሁለቱ አገራት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ

ጉዳቱ ለቻይና ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ሁኔታ አሜሪካም የምታጠው ነገር ቀላል የሚባል አይሆንም።

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2024 ከቻይና ያስገባቻቸው ምርቶች 438 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ከአሜሪካ የንግድ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

አሜሪካ ለቻይና ያደረገችው ወጪ ንግድ ደግሞ 143 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ይህም ማለት አሜሪካ ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ 295 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት (ትሬድ ዴፊሲት) ገጥሟታል።

አሜሪካ ከቻይና የምታስገባቸውን ምርቶች በአጭር ጊዜ ከየትኛው አገር በሚገኙ ምርቶች እንደምትተካቸው ግልጽ አይደለም።

“ሁለቱ አገራት በምጣኔ ኃብቱ ረገድ በብዙ መንገዶች የተሳሰሩ ናቸው። በሁለቱ አገራት መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት፣ የዲጂታል ንግድ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ አላቸው” ሲሉ የሚናገሩት ደግሞ በሲንጋፖር የሂንሪሽ ፋውንዴሽን የንግድ ፖሊሲ ኃላፊ ዲቦራ ኤልምስ ናቸው።

“ታሪፍ መጣል የሚቻለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። ነገር ግን ሁለቱም አገራት አንዱ አንዱን የሚጎዳበት ሌሎች መንገዶች አላቸው። ምናልባት ነገሮች ሊከፉ ይችሉ ይሆናል። ሊከፉ የሚችሉበትም ብዙ መንገዶች አሉ” ሲሉ ያክላሉ።

ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶቿን ወደየት ትልካለች? የሚለውን ለማየት የተቀረው ዓለም እየጠበቀ ነው።

ምናልባትም እንደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ ወዳሉ ገበያዎች ሊሄዱ እንደሚችሉ ዲቦራ ያስረዳሉ።

ሆኖም “እነዚህ ሀገራት ከተጣለባቸው ታሪፍ ጋር በተያያዘ ምርቶቻቸውን የት መሸጥ እንዳለባቸው እያጤኑ ይገኛሉ” ይላሉ።

“በተለየ ዓለም ውስጥ ነን ያለነው፤ ጨለም ባለ ሁኔታ” ብለዋል።

መጨረሻው ምን ይሆን?

በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በነበረው የሁለቱ አገራት የንግድ ጦርነት ድርድሮች ነበሩ።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት “ነገሮች ከዚህ በኋላ ወደየት ሊያመሩ እንደሚችሉ ለመተንበይ በጣም ከባድ ነው” የሚሉት በሎይ ኢንስቲትዩት የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ሮላንድ ራጃ ናቸው።

ቻይና ለአሜሪካ ታሪፍ አጻፋዊ ምላሽ የሚሆን “በርካታ መሳሪያዎች” በእጇ ላይ እንዳለ ሮላንድ ያስረዳሉ።

ሮላንድ ከሚጠቅሱት መካከል የመገበያያ ገንዘቧን የበለጠ ማዳከም ወይም በገበያዋ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎችን ልታዳከማቸው ትችላለች።

ሆኖም አንዳንድ ባለሙያዎች አሜሪካ እና ቻይና በተናጠል ውይይቶች ሊያደርጉ እንደሚችሉም ያምናሉ።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር አልተነጋገሩም።

ቻይና በበኩሏ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆኗን ደጋግማ ገልጻለች።

ሌሎች ግን በሁኔታው ላይ ብዙም ተስፋ የላቸውም።

“አሜሪካ አለኝ ብላ የምታስበው ጥንካሬ ከእውነታው በላይ ይመስለኛል” ይላሉ ዲቦራ።

ትራምፕ የአሜሪካ ገበያ በጣም አዋጭ በመሆኑ የቻይና ወይም የትኛውም ሀገር ውሎ አድሮ ይቀበላል ብለው የሚያምኑት ነገር ለሳቸው አጠራጣሪ ነው።

“ይህ እንዴት ይቋጫል። ማንም አያውቅም” የሚሉት ዲቦራ አክለውም “ፍጥነቱ እና የተፈጠረው ውጥረት በእውነቱ አሳስቦኛል። መጪው ጊዜ በጣም ፈታኝ ነው፤ አደጋውም እንዲሁም በከባዱ የከፋ ነው” ይላሉ።