ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስብሰባው ላይ እና ከከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር

9 ሚያዚያ 2025, 14:06 EAT

ተሻሽሏል ከ 1 ሰአት በፊት

የፌደራል መንግሥት “የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት” ለማስከበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ “በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል አቅጣጫ” ማስቀመጡን አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ በቀጣናው “ሰላምንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የነበራትንና ያላትን ከፍተኛ ሚና” እንዲረዳም መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።

ይህ የፌደራል መንግሥት ውሳኔ የተገለጸው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም. ያደረገውን ስብሰባ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት የተካሄደው ስብሰባ “ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች” የተገመገሙበት እንደሆነ መግለጫው አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው “ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች” በሚል ከጠቀሳቸው ጉዳዮች ውስጥ “ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም” መንገድን የተከተሉ አካላትን የተመለከተው አንዱ ነው።

“እነዚህ አካላት መልካቸው ይለያይ እንጂ በተለያዩ አካባቢዎችና በውጭ ይገኛሉ” ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ “ሤራ፣ ወጥመድ፣ ዝርፊያ፣ እገታ፣ ጭካኔ፣ ሕገ ወጥ ንግድ እና ፍላጎት በኃይል ብቻ ማስፈጸም መለያቸው” እንደሆነ ገልጿል።

መግለጫው፤ እነዚህ አካላት “በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር” እንደሚተባበሩ እንዲሁም “የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን የሚመሩ ክንፎች” እንዳላቸውን በመጥቀስ ከስሷል።

ምክር ቤቱ “በጥልቀት” ተመልክቷቸዋል የተባለው ሌላኛው ጉዳይ “ከዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች” ጋር የተያያዘ ነው። የምክር ቤቱ መግለጫ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሀገሪቱ ላይ “ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ በዝርዝር ውይይት” መደረጉን ያስረዳል።

በኢትዮጵያ ላይ ተጸዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ከተባሉት ጉዳዮች መካከል የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ እየተከሠቱ ያሉ ውጥረቶች፣ የሽብር እንቅስቃሴዎች እንዲሁም እየታወኩ ያሉ ዓለም አቀፍ የንግድ መሥመሮች እንደሚገኙበት አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስብሰባው ላይ

በተጨማሪም “እየፈረሱ እና እየተዳከሙ የሚገኙ ሀገሮች፣ እየተበራከቱ ያሉ የሳይበር ጥቃቶች፣ እየተነጣጠሉ ያሉ ነባር ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች እንዲሁም እየተፈጠሩ ያሉ አዳዲስ ዓለም አቀፋዊ ጥምረቶችን” የተመለከቱ ጉዳዮችም ዝርዝር ውይይት እንደተካሄደባቸው ተገልጿል።

“እየፈረሱ እና እየተዳከሙ” የተባሉት አገራት የትኞቹ እንደሆኑ ይህ መግለጫ ያለው የለም።

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ “አቅጣጫዎችን” እንዳስቀመጠ መግለጫው ያስረዳል።

ምክር ቤቱ አቅጣጫ ያስቀመጠበት አንዱ ጉዳይ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚመለከት ነው።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ችግሮችን “በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬ እያፈራ” መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ “ባህላዊ መንገዶችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰላማዊ መንገዶች መጠቀም” ይህንን ተግባር “ይበልጥ ውጤታማ” ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል።

ይሁን እንጂ “የሰላም አማራጮችን ዘግተው ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱት” ቡድኖች ላይ “ሕግ የማስከበር ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል” እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል።

“ከኢትዮጵያ ጠላቶች ተልዕኮ እየተቀበሉ በሀገር ውስጥ ችግር ለመፍጠር የሚጥሩ” አካላት “ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ሕግ የማስከበር፣ የሰላም አማራጮችን” ተግባራዊ እንደሚሆኑም ተገልጿል።

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ መግለጫ የሀገሪቱን “ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት የሚያሳድጉ የዲፕሎማሲ ውጤቶች እየጨመሩ” መምጣታቸውን ይጠቅሳል።

ይህንን ውጤት ያስገኙ ተግባራትን “ይበልጥ በማስፋፋት እና በማጠናከር፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስከበር ተገቢ” እንደሆነ መግለጫው ያትታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስብሰባው ላይ እና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች

ምክር ቤቱ በስብሰባው ላይ ከዚህ በተያያዘ የሰጠው “አቅጣጫ” የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የተመለከተ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተለይም በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ “የኅልውና ጉዳይ” መሆኑን ከገለጹበት በ2016 ዓ.ም. መጀመሪያ አንስቶ ይህ ጉዳይ በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በመገናኛ ብዙኃን በኩል በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅትም የባሕር በር የማግኘት ጉዳይን አንስተው ነበር።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር እና የአባይ ወንዝ ውሃን በተመለከተ ያላት አቋም “በጎረቤት አገራት ዘንድ ግልጽ” እንዳልነበሩ የተናገሩት ጠ/ሚ ዐቢይ፤ አሁን ግን “የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ አቁሟል” ሲሉ ተደምጠዋል።

“የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቋምም በዓለም ላይ ትልቅ አገር ሆኖ የባሕር በር የሌለው የለም፤ ስለሆነም በሰጥቶ መቀበል መርኅ ሊሆን ይገባል የሚል ነው” ሲሉም ተደምጠው ነበር።

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ መግለጫ፤ መንግሥት በተደጋጋሚ እያነሳው ያለው የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ “በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል የሚያስችል አቅጣጫ” መቀመጡን አስታውቋል።

“የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማስከበር ዲፕሎማሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶችን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሥራ በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል” ሲል ውሳኔውን ገልጿል።

ኢትዮጵያ “በአሁናዊ የዓለም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ የፖሊሲ ነጻነቷን አስጠብቃ፣ ጥቅሞቿን አስከብራ ተገቢ ሚናዋን” እየተጫወተች መሆኑን የሚጠቅሰው መግለጫው፤ ሀገሪቱ “ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ሁሉ ተሻግራ ተገቢ ሉላዊ ደረጃዋን እንድትይዝ” የሚያስችል “ጥበባዊ አመራር ተጠናክሮ” ይቀጥላል የሚል እምነቱን ገልጿል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኢትዮጵያ “ሰላምን እና ደኅንነትን በማረጋገጥ” ረገድ “በቀጣናው፣ በአህጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ “የነበራትንና ያላትን ከፍተኛ ሚና” ተረድቶ የሚያደርገውን ድጋፍ “አጠናክሮ እንዲቀጥልም” ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።