በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች የሟቾችን ፎቶ ይዘው
የምስሉ መግለጫ,በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች የሟቾችን ፎቶ ይዘው

ከ 3 ሰአት በፊት

ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ላይ ክስ ከመሠረቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጎጂ ሁለት ቤተሰቦች ጋር ስምምነት ላይ ደረሰ።

ኩባንያው ከስድስት ዓመት በፊት በደረሰው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የቀረበበትን ክስ በስምምነት የፈታው ከችሎቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ እንደሆነ ሮይተርስ የቦይንግ እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ጠበቆች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ቦይንግ በአውሮፕላን አደጋው ሕይወታቸውን ካጡት አንቶኒ ሊውስ እና ዳርሲ ቤላንገር ቤተሰቦች ጋር የደረሰው ስምምነት ዝርዝር ይፋ አልሆነም።

በቺካጎ ሊታይ የነበረው የፍርድ ሂደት የ157 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ እንዲሁም ለ189 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት በሆነው የኢንዶኔዥያ አየር መንገድ አደጋ በተጎጂ ቤተሰቦች የቀረበ የመጀመሪያ ክስ ይሆን እንደነበር መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የአሁኑ ክስ ቦይንግ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ተጎጂ ቤተሰቦች የደረሰባቸውን ሰቆቃ እና ጉዳት ለማማካስ መከፈል ያለበትን የገንዘብ መጠን ችሎቱ እንዲወስን ነበር።

ቦይንግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 8 አደጋ ከሞቱት 157 መንገደኞች እና የበረራ ሠራተኞች ቤተሰቦች ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው በ2014 ዓ.ም. ነበር።

ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድና የካሳ ተጠያቂነቱንም እቀበላለሁ ያለ ሲሆን፣ በምላሹም የተጎጂ ቤተሰቦች ኩባንያው ላደረሰው ጉዳት ፍርድ ቤት እንደማይወስዱት ተስማምተው ነበር።

ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት የሁለቱ አደጋዎች ተጎጂ ቤተሰቦች ለደረሰባቸው ጉዳት አውሮፕላን አምራቹን መጠየቅ እንደሚቻል ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ መድረሱን ተከትሎ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስዱት መንገድ የከፈተ ሆኗል።

በአውሮፕላን አምራቹ ላይ ክሱን የመሠረቱት በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሁለት አሜሪካውያን ቤተሰቦች ናቸው።

የ39 ዓመቱ ሊውስ የጦር ሠራዊት አባል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍሮ ወደ ኬንያ ሲያቀና የነበረው የሎጂስቲክ ንግድ ላይ ያሉ ዕድሎችን ለማየት ነበር። ሌላኛው የ46 ዓመቱ ቤላንገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ሲጓዝ እንደነበረ ዘገባው አስነብቧል።

መጋቢት 01/2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አሰቃቂው አደጋ የደረሰበት።

በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ቦይንግ ሰኞ ዕለት የተጎጂ ቤተሰቦችን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን “የተጎጂ ቤተሰቦችን በሙሉ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመካስ ቁርጠኝነት እንዳለው እንዲሁም ለአደጋው ሕጋዊ ኃላፊነትን ተቀብያለሁ። የተጎጂ ቤተሰቦችን ጥያቄ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመመለስ መሥራታችንን እንቀጥላለን” ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

ቦይንግ በሁለቱ 737 ማክስ 8 የአውሮፕላን አደጋዎች ከ90 በመቶ በላይ የተጎጂ ቤተሰቦችን ጥያቄ እንደመለሰ እንዲሁም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ካሳ ለቤተሰቦቻቸው በክስ፣ ከዐቃቤ ሕግ ጋር በተደረሰ ስምምነት እና በሌሎች ክፍያዎች መፈጸሙን ገልጿል።

ሆኖም ሌሎች ሁለት የፍርድ ሂደቶች ሐምሌ እና በመጪው ዓመት ኅዳር ይጠብቁታል።

ቦይንግ በ737 ማክስ 8 ላይ ቁልፍ የደኅንነት ሥርዓትን በተመለከተ ለተቆጣጣሪዎች የሰጠው መረጃ ሐሰተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሚቀርብበት የማጭበርበር ሴራ የወንጀል ክስ ላይ የተሻሻለ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ጋር እየተነጋገረ ነው ተብሏል።

ቦይንግ የቀረበበትን የማጭበርበር የሴራ የወንጀል ክስ ጥፋተኝነቱን አምኖ እስከ 487.2 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ቅጣት ለመክፈል በሐምሌ ወር ተስማምቷል።

ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የፍርድ ሂደቱ በመጪው ሰኔ ወር እንዲጀምር ዳኛው ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከፍትህ መሥሪያ ቤቱ ጋር በወንጀል እንዳይጠየቅ አሠራሩን ለማሻሻል ገብቶ የነበረውን ስምምነት መጣሱን ተከትሎ ነው የወንጀል ክስ የቀረበበት።

ቦይንግ ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀረበበት የአሜሪካ ፌደራል የአቪዬሽን አስተዳደርን የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

የአሜሪካ ዐቃቢያነ ሕግ ቦይንግ ለሁለቱም አደጋዎች ምክንያት የሆነው የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን በተመለከተ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ተቆጣጣሪዎችን አጭበርብሯል በሚልም ከአራት ዓመታት በፊት ክስ መሥርተውበት ነበር።

ቦይንግ ቺካጎ በነበረው የፍርድ ሂደት በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማምቶ፣ በምላሹም የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ለአውሮፕላን አምራቹ ከ737 ማክስ ማክስ 8 አውሮፕላኑ ዲዛይን ጉድለት ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ሴራ በወንጀል እንዳይከሰስ ከለላ ሰጥቶት ነበር።

የአውሮፕላን አምራቹ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እና ተጠያቂነቱን ተቀብሎ ለአሜሪካ መንግሥት፣ አደጋ ለደረሰባቸው አየር መንገዶች እና ለተጎጂዎች የሚሆን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

ቦይንግ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ከአሜሪካ ዐቃቢያነ ሕግ ጋር የደረሰው ስምምነት ኩባንያው በአደጋው ዙሪያ የሚካሄደው የወንጀል ምርመራ እንዲቀር የተስማማበት ነው።

ቦይንግ የሚያመርታቸውን አውሮፕላን ምርቶች ደኅንነት እና ጥራት ለማስጠበቅ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የክትትል እና የቁጥጥር መርሃ ግብር ስምምነትም ገብቶ ነበር።

ነገር ግን የአላስካው አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በር ስምምነቱ ጊዜው ከማለፉ ከሁለት ቀናት በፊት ታኅሣሥ 26/ 2016 ዓ.ም. ተገንጥሎ ከአየር ላይ መውደቁን ተከትሎ ስምምነቱን መጣሱ ተመልክቷል።

ከስድስት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።