አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ
የምስሉ መግለጫ,አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ

8 ሚያዚያ 2025

አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ “ከሕገ መንግሥቱን” እና “ከሀገር ሉዐላዊነት”፤ “ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ የማድረግ” ኃላፊነትን የሚጥልባቸው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ መፈረማቸው ተገለጸ።

የቃል ኪዳን ሰነዱ፤ የቀድሞ ታጣቂዎች “ትጥቅ መፍታት” እና “መልሶ መቋቋም” ተግባር “በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ የማድረግ” ኃላፊነትንም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ይሰጣል።

ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ሥልጣንን ከአቶ ጌታቸው ረዳ የተረከቡት ሌ/ጄነራል ታደሰ፤ በአዲሱ ኃላፊነታቸው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት የዘረዘረ ሰነድ ላይ መፈረማቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲራዘም ባስቻለው የሕግ ማሻሸያ ላይ የፌደራል መንግሥት ይህንን ዓይነቱን ተግባራት ሊሰጥ እንደሚችል ደንግጓል።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የጸደቀው የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት የሚደነግግ አዋጅ ማሻሻያ ካካተታቸው ሦስት ዋነኛ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በክልሎች የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር “ትኩረት ሰጥቶ” የሚሠራባቸውን ጉዳዮች የሚመለከት ነው።

ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በሚያስተላልፉት ውሳኔ ላይ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሊመላከቱ” እንደሚችሉ በአዋጁ ማሻሻያ ላይ ሰፍሯል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራባቸው የሚተላለፉ ጉዳዮች፤ በክልሉ “የፌደራል መንግሥት ጣልቃ መግባት ምክንያት የሆነውን ሁኔታ በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማጽናት አስፈላጊ የሆኑ” ተግባራት እንደሚሆኑ ማሻሻያው ያስረዳል።

ዛሬ ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ጋር የተለጠፈው ምሥል፤ አዲሱ ፕሬዝዳንት “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም ቃል ኪዳን ሰነድ ” በተባለ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ያመለክታል። የቃል ኪዳን ሰነዱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶች ለመወጣት በሙሉ ኃይሉ እና ትጋት ይሠራል” በማለት ስምንት ጉዳዮችን ዘርዝሯል።

በሰነዱ ላይ በቀዳሚነት የተጠቀሰው ኃላፊነት “የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ” ሂደትን የሚመለከት ነው። ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በጅምር” ላይ ያለውንን የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ተግባር “እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር” የማድረግ ኃላፊነት እንደተጠላበት በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ፊርማቸው ሲያኖሩ። ከጀርባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የቀድው ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ቆመው።

ከብዙ መጓተት በኋላ ቢጀመርም መስተጓጎል ያጋጠመው የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አዲስ ፕሬዝዳንት ለተሾመለት ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠ ሌላኛው ኃላፊነት ነው።”በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር” መከናወን እንዳለበት በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ሂደት “በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ማድረግ” እንዳለበትም በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም እና ፀጥታ ጋር የተያያዙ ተግባራትንም እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከተጠቀሱት ተግባራት መካከል “በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ” የሚለው ይገኝበታል።

“ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለፀጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግም” የዚህ ኃላፊነት አካል ነው። እነዚህን ተግባራት ለማከናወንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት” እንደሚኖርበት በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ከጦርነት በቅጡ ባላገገመው ትግራይ ክልል ውስጥ፤ “መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲሁም የመልሶ ማልማት ሥራዎች እንዲሳለጡ ማድረግ” የሚለውም በኃላፊነቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል።

ፌደራል መንግሥት፤ በደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራውን የህወሓት ክንፍ “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት” በመፍጠር በከሰሰበት ወቅት ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡት ሌ/ጄነራል ታደሰ፤ ከዚሁ ጋር የተያያዘ የሚመስል ኃላፊነት ጥሎባቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) በመጋቢት ወር መጀመሪያ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ይህንኑ ክስ አቅርበው ነበር። ጌድዮን፤ በደብረፂዮን የሚመራውን የህወሓት ክንፍ አመራሮች “ለኢትዮጵያ ጠበኛ ከሆኑ የውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ እና እየተባበሩ” መሆኑን በመጥቀስ ከስሰው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግንኙነት የተፈጠረው ከየትኛው ሀገር ጋር እንደሆነ በግልጽ ባይጠቅሱም፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው “የተወሰኑ” የህወሓት እና የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች “ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረጉ ነው” የሚል ክስ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ነበር።

ዛሬ በተሰፈረው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል “ከሕገ መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር ሉዐላዊነት እና ከፕሪቶሪያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ” የሚለው ይገኝበታል።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ወዲህ በጊዜያዊ መንግሥት እየተዳደረ ያለው የትግራይ ክልል “ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን” የማድረግ የቤት ሥራም ለአዲሱ አመራር ተላልፏል።

ተፈናቃዮች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ መደበኛ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ምርጫ ለማከናወን “ሁኔታዎችን የማመቻቸት” ተግባርን “በወቅቱ ማከናወን እንዳልቻለ” መግለጻቸው ይታወሳል። ባለፉት ሁለት ዓመታት መከናወን ያልቻለው ይህ ኃላፊነት ዛሬ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን ወደተረከቡት ሌ/ጄነራል ታደሰ ተዛውሯል።

በአዲሱ ፕሬዝዳንት የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር፤ “በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት” እንዲሁም “የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ዓውድ እንዲፈጠር” የመሥራት ኃላፊነትም ተሰጥቶታል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ “የተልዕኮ አፈጻጸም ቃል ኪዳን ሰነድ” ላይ የተካተተው ሌላኛው ጉዳይ በሂደት ላይ ያለውን የሀገራዊ ምክክር የሚመለከት ነው።

የካቲት ላይ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የሥልጣን ዘመኑ የተራዘመው የሀገራዊ ምምክር ኮሚሽን በአስር ክልሎች እና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች ውስጥ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊዎች ልየታ ተግባራትን አከናውኖ ቢያጠናቅቅም በአማራ እና በትግራይ ክልል ይህን ሠርቶ አልጨረሰም።

በግጭት ውስጥ በሚገኘው በአማራ ክልል ከቅዳሜ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም. ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን አስጀምሯል። እነዚህ ሂደቶች ያልተጀመረበት ብቸኛ ክልል ትግራይ ነው።

ዛሬ በተፈረው የቃል ኪዳን ሰነድ፤ “የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት” ኃላፊነትን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰጥቷል።

በሰነዱ ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻው ጉዳይ በክልሉ የሚገኙ “የሚዲያ እና የኮሚዩኒኬሽን እንቅስቃሴዎችን” ይመለከታል። በክልሉ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን እንቅስቃሴ “የሀገሪቱን ሕዝቦች ትስስር እና መልካም ግንኙት የሚያጠናክሩ” መሆን እንደሚገባቸው በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን እና የኮሚዩኒኬሽን እንቅስቃሴዎች “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ” ተግባርን የማከናወን ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በዚህ ሰነድ ላይ ስማቸው የተጻፈው አዲሱ ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ፊርማቸው ያኖሩት፤ “ሥራዬን ስጀምር ከላይ የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶች በትጋት እና በታማኝነት ለመውጣት ቃል እገባለሁ” ከሚል ጽሁፍ ስር ነው።