April 9, 2025

የአማራ ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች ካለፈው እሁድ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲያካሄዱት የቆየው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቀቀ። የማህበረሰብ ተወካዮቹ፤ በመጪዎቹ ቀናት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ የምክክር ሂደት የሚሳተፉ 270 ወኪሎቻቸውንም መርጠዋል።
በቁጥር ከ4,500 በላይ የሚሆኑት እነዚህ የማህበረሰብ ተወካዮች፤ በክልሉ ካሉ 263 ወረዳዎች የተመረጡ ናቸው። አስር የማህበረሰብ ክፍሎችን የወከሉት እነዚህ የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች፤ በባህርዳር ከተማ በነበራቸው ቆይታ ከዘጠኝ እስከ 12 አባላት በሚገኙባቸው ቡድኖች ተከፋፍለው በአበይት ክልላዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሲወያዩ ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ አቶ መላኩ ወልደማርያም፤ የማህበረሰቡ ተወካዮች ያቀርቧቸው የነበሩ አጀንዳዎች “በትናንሽ ነገሮች ላይ ያተኮሩ አልነበሩም” ሲሉ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል። “ትላልቅ አጀንዳዎች፤ ለሀገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን ነበር የሚያነሱ የነበሩት” ሲሉም አክለዋል።
የማህበረሰብ ተወካዮቹን ምክክር “በጣም የተሳካ” እና “በጣም ውጤታማ” ሲሉ የገለጹት አቶ መላኩ፤ ሂደቱን “አሳታፊ፣ አካታች፣ ግልጽነት የተሞላበት እና በነጻነት የተካሄደ ነበር” ብለውታል። በምክክር ሂደቱ “ዜጎቻችን የት ደረጃ እንደደረሱ ማየት የቻልንበት ነው” ሲሉ የተደመጡት ኮሚሽነሩ፤ “ትምህርት የተማርንበት ሂደት ነው ማለት እንችላለን” በማለት ያን ያሉበትን ምክንያት አብራርተዋል።
“ከዚህ የምክክር ሂደት አማራ ክልል ያየነው ነገር፤ ትምህርት ያገኘንበት፣ የዜጎቻችን ንቃት ከፍተኛ እንደሆነ፣ ያለው ችግር ሳይበግራቸው፣ ያለው ፈተና፣ ያለው መከራ ሳይበግራቸው፣ ያንን ዋጥ አድርገው፤ ትልቁን ምስል ነበር የሚያሳዩት። ሀገራዊ የሆነውን ነበር የሚያሳዩት” ሲሉ በዚህ ሁኔታ በግላቸው መደነቃቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አንስተዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)