April 8, 2025

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነትን በዛሬው ዕለት የተረከቡት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፤ “ከህገ መንግስታዊ”፣ “ከህጋዊ ስርዓት”፣ “ከሀገር ሉዓላዊነት” እና “ከፕሪቶሪያ ስምምነት” ያፈነገጡ የተባሉ “ግንኙነቶች” እና “እንቅስቃሴዎች” እንዲቆሙ ለማድረግ ተስማሙ። አዲሱ ፕሬዝዳንት ይህን ቃል የገቡት፤ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ በፈረሙት የጊዜያዊ አስተዳደሩ “የተልዕኮ አፈጻጸም” “የቃል ኪዳን ሰነድ” ላይ ነው። 

ሌተናል ጄነራል ታደሰ ክልሉን የመምራት ስልጣን ከአቶ ጌታቸው ረዳ የተረከቡት፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 30፤ 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ ስነ ስርዓት ላይ ነው። በትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የሚያስችል ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው መጋቢት 9፤ 2015 ዓ.ም. ነበር። 

ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንዲመሩ በመጋቢት 14፤ 2015 ዓ.ም መሾማቸው ይታወሳል። አቶ ጌታቸው የፕሬዝዳትነት ስልጣኑን ከተረከቡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ ባደረጉት ካቢኔያቸው፤ ምክትላቸው አድርገው የሾሟቸው ሌተናል ጄነራል ታደሰን ነበር። 

ሌተናል ጄነራል ታደሰ፤ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው በተጨማሪ የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰሩ ቆይተዋል። የዛሬውን የስልጣን ርክክብ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ሌተናል ጄነራል ታደሰን “ባለፋት ሁለት ዓመታት የነበሩ ድካሞችን እና ጥንካሬዎችን በግልጽ የሚገነዘቡ ሰው ናቸው” ብለዋቸዋል።

የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንዲመሩ የተመረጡት፤ “አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ” በሚል “በብዙ አካላት በመታመኑ” ምክንያት እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ለትግራይ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ብቁ የሚሆኑ ዕጩዎችን እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርበው ነበር።

አብይ በዚሁ ጥሪያቸው፤ ዕጩዎቹ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራዎች “በብቃት የሚያከናውኑ” እንዲሁም “የክልሉን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ የሚችሉ መሆን” ይገባቸዋል ብለው ነበር። በዛሬው የስልጣን ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ሌተናል ጄነራል ታደሰ የፈረሙት፤ የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር “የተልዕኮ አፈጻጸም” “የቃል ኪዳን ሰነድ” ላይ ከሰፈሩ ስምንት ነጥቦች ሶስቱ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ናቸው። 

ሌተናል ጄነራል ታደሰ “በትጋት” እና “በታማኝነት” ለመፈጸም ቃል ከገቧቸው ኃላፊነቶች መካከል፤ “ከህገ መንግስታዊ እና ከህጋዊ ስርዓት፣ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶሪያ ስምምንት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እንዲቆሙ ማድረግ” የሚለው አንዱ ነው። እርሳቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል “የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የማድረግ” ኃላፊነትም በቃል ኪዳን ሰነዱ አማካኝነት ተጥሎበታል።

አካታች ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ለህዝብ ደህንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ” የተባሉ “ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች” እንዲቆሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት በቃል ኪዳን ሰነዱ ሰፍሯል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ለማድረግ “ተገቢውን የቁጥጥር እና የህግ ማስከበር ስራ የመስራት” ተልዕኮም ተሰጥቶታል።

በዚሁ የቃል ኪዳን ሰነድ የተጠቀሰው ሌላው የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ “የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የመፍታት” ጉዳይ የሚመለከት ነው። በሰነዱ ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ማድረግ” እንዳለበት ተቀምጧል።

በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን “የማረጋገጥ፣ ዲሞቢላይዝ የማድረግ፣ የመመዝገብ እና የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል” ስራዎች የተጀመሩት ባለፈው ህዳር ወር ውስጥ ነበር። በዚህም መሰረት ስምንት ሺህ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።   

ኮሚሽኑ በየካቲት ወር መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፤ “በአንዳንድ ቴክኒካዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ተቋርጦ” የቆየው ይህ ሂደት በመጋቢት ወር መጀመሪያ እንደገና እንደሚጀመር አስታውቆ ነበር። ሆኖም ይህ ሂደት በተባለለት ጊዜ ሳይካሄድ መቅረቱን፤ ተሰናባቹ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

አቶ ጌታቸው በዚሁ መግለጫቸው ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ማብራሪያ የሰጡበት የተፈናቃዮች ጉዳይም፤ በስልጣን ርክክቡ ወቅት በተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ተካትቷል። የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ሂደት፤ የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር “በጅምር ያለው እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር” የማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]