
Fikre Tolossa
የአሰብ ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያ በአሰብ የመገልገል መብትዋ
*********************************
ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
አሰብ፣ “አሰብ” ከመባሉ በፊት የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱን ስሙ ተርሴስ ነበር። ከ 4000 ዓመታት በፊት ተርሴስ ብላ የሰየመችውም “ተርሴስ” የተባለች የጻድቁ የኢዮብ ልጅ ሚስት የሆነች ሴት ናት። ጻድቁ ኢዮብ በሰይጣን ተፈትኖ ፈተናውን አልፎ እንደገና ልጆች ወልዶ ወንዶች ልጆቹ ሚስቶቻቸውን ይዘው ወደ አፋር አገር ፈልሰው እንደነበር ታሪክ ይዘግባል። ታዲያ ከሴቶቹ አንዷ የባህሩን ወደብ ስታይ ስለወደደችው ስሟን ህያው ለማድረግ “ተርሴስ” አለችው። ከዚያ በኋላ ለ 4000 ዓመታት ተርሴስ የተባለው ስም በመካከለኛው ምስራቅ ሲያስተጋባ ኖረ። “አሰብ” የተባለው ስም ከባህር ጨውነት ጋራ የተያያዘ በኋላ የመጣ ቃል ነው።
“ተርሴስ” የሚለው መጠሪያ ግን ለምስክርነት በብሉይ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታ ተጠቅሷል። እሱም ከአፋሮች ነጋዴነት ጋራ የተያያዘ ነው።
አዎን፣ በመጽሀፍ ቅዱስ “የተርሴስ ነጋዴዎች” ይላቸዋል። የዚህም ምክንያቱ አፋሮች የሚያስደንቁ መርከቦች ሠርተው፣ ብርቅዬ እና ውድ የሆኑ ማእድናትን እና የእርሻ ምርጥ ውጤቶችን፣ እንዲሁም ለማዳ እንስሳትን እየጫኑ በድሮው ዐለም ይነግዱ ስለነበር ነው። ንጉሥ ሰለሞን የዛሬ ሶስት ሺ ዓመት ቤተመቅደሱን ሲገነባ የግባት እቃዎቹን፣ የአፋርን ሉል፣ ወርቅ፣ ፣ ዞጺ (ውድ ጥቁር እንጨት) እንዲሁም እጣን፣ ከርቤ፣ ሰንደል እና የመሳሰሉትን አፋሮች ከተርሴስ ወደብ በመርከባቸው ጭነው ይልኩለት ነበር። እሱም የራሱን መርከቦች እዛው አሳንጾ በዛው አካባቢ ከነበረ ጽዮን ጋብር ከተባለ ወደብ በተጨማሪ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች ያጓጉዝ ነበር።
በስፔን አካባቢ የአለው ተርሴስ የአሰቡን ለማስታወስ ኢትዮጵያውያን በስፔን እና ፖርቱጋል የሰየሙት ነው። እንዴት ቢባል የዛሬ 2030 ዐመት መጋል የተባለው የጂማና የደርዴና ንጉሥ በአፋር መርከብ ተሳፍሮ፣ የአማራን ጦረኛ ይዞ፣ የኦሮሞ ካህናትን ጭኖ እስፔንን እና ፓርትጋልን ለአጭር ጊዜ ቅኝ ገዝቶ የአሰብን ተርሴስ ለማስታወስ የስፔኑን ወደብ ተርሴስ ስለ አለው ነው። ይህን እኔ Promise Fulfilled በተባለው መጽሀፌ ለዐለም ገልጫለሁ። የአማራ እና የኦሮሞ እውነተኛው የዘር ምንጭ የተሰኛው እና የተሰወረውና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ በተባሉትም መጻህፍቴ ጠቅሻቸዋለሁ።።
ተክለጻዲቅ መኩሪያ እንደሚተርኩልን፣ እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለዘመን ድረስ አሰብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሳለች ሱልጣን ኢብራሂም የተባለ የአፋር ባላበት ለአንድ የጣልያን የንግድ መርከብ ኩባንያ ግዜያዊ ማረፊያ ይሆነው ዘንድ የአሰብ ወደብን እንዲ ጠቀመብት ገንዘብ ተቀብሎ ፈቀደለት። ሸጠለት የሚሉም አሉ። ቀስ በቀስ ግን ይህ ኩባንያ መሬቱን እንደራሱ ንብረት ቆጥሮ ለጣልያን መንግስት መላውን ወደብ ሸጠለት። የጣልያን መንግሥትም ይህን ሰበብ አድርጎ ወታደሮች ወደዛ እየላከ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ወደውስጧ መዝለቅ ጀመረ። በላይ በምጽዋ በኩልም ለመግባት ሲሞክር የአጼ ዮሀንስ የጦር አበጋዝ ጀግናው ራስ አሉላ አባ ነጋ ምንም በርትተው በዶግአሊ እና ሌሎች ቦታዎች ድባቅ ቢመቱትም ኤርትራን በመጨረሻ ይዞ አስመራን ለመቆጣጠር በቃ።
በሀያኛው ክፍለ ዘመን ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ወርሮ ተሸንፎ ሲወጣ (በዩኒየኒስት ወይም አንድነት ፓርቲ) አባሎች አነሳሽነት በርከት ያሉ የኤርትራ ሰዎች በፍላጎታቸው መርጠው ከኢትዮጽያ ጋራ በፊዴሬሽን ተቀላቀሉ። በእዚህ ምክንያት ምጽዋና አሰብም ለኢትዮጵያ ተመለሱ። የኢሳያስ አባት አቶ አፈውርቂም ኤርትራ ከኢትዮጽያ ጋራ እንድትዋሀድ በብርቱ ከታገሉት ሰዎች አንዱ ነበሩ። ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ከተቀላቀለች በኋላ አዲስ አበባን ወድደው በአጼ ኋይለሥላሤ ዘመን በመዲናው ውስጥ ይኖሩ ነበር። ኢሳያስም ከልጅነቱ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሯል። ደጃዝማት ሰለሞን አብርሀ የሚባሉ አጎት ነበረው። በአፍቃሬ ኢትዮጵያዊነታቸው እና ታማኝነታቸው በአጼ ኃይለድላሤ የተሾሙ ነበሩ። እና ታዲያ እሳቸው የወሎ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በሆኑበት ዘመን ኢሳያስ እሳቸው ቤት እየኖረ በወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት ውስጥ ይማር ነበር። ከእዚያም አዲስ አበባ በሚገኘው የባላባት ልጆች እና ጎበዝ ተማሪዎች በተማሩበት በጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ ተመርቋል። ከምረቃው በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማር ጀምሮ ሳለ፣ ሽማግሎች እና አንዳንድ መጻህፍት እንደሚመሰክሩልን፣ በኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያን ትዋጋ የነበረችውን ጅብሀ ትግል ለማስቀልበስ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ታምኖ ወደ ኤርትራ በርሀ ተላከ። ተልእኮውንም ለማሳካት የጀብያ ጠላት ከነበረው ከሻብያ ጋር ሆኖ ጀብሀን ለዐመታት ተታግሎ ራሱ መሪ ሆኖ ወጣ። ከዚያም ከኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል የተሰጠውን እምነት እና አደራ ክዶ ፣ የንጉሠነገሥቱ ዋና ተቃዋሚ በመሆን ከሕወሀት ጋራ ተጣምሮ እየተዋጋ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ሊገነጥል ቻለ።
በእዚህ አዛኝ የኢሳያስ ድርጊት የአጼ ኃይለሥላሤም ሆነ የአቶ አፈወርቂ ወይም የደጃዝማች ሰለሞን አብርሀ ኢትዮጵያን ከኤርትራ የማዋድ ጥረት መና ሆኖ ቀረ።
ቀደም ሲል አጼ ኃይለሥላሴ በጊዜያቸው ለአንድነቱ ጉዳይ በጣም ተግተውበት ስለነበረ በወቅቱ እንደዚህ ተብሎ ተዘፍኖላቸው ነበር—
“አባ ጠቅል ሳለ ማንን እፈራለሁ፣
“በኤርትራ ባህር ገብቼ ዋኛለሁ።
‘አባ ጠቅል ኃይሌ የትዮጵያ ምሰሶ፣
” የተዘጋውን በር ከፈተው መልሶ።”
ጣልያን ከኢትዮጵያ እስከተባረረበት ወቅት የአሰብ ወደብን ቢይዝም የኢትዮጵያ አፋሮች፣ ኩናማ እና ብሌኖች እሱን ከመጤፍ ሳይቆጥሩት አሰብ የእነሱ እና የኢትዮጵያ እንደሆነች ያስቡ ነበር።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በፌዴሬሽን አብረው ከሆኑበት እና ባለፉት የቅርብ ዓመታት ኤርትራ እስከ ተገነጠለችበት ወቅት ኢትዮጵያ አሰብን እና ምጽዋን በእኩል ታስተዳድር ነበር። ምጽዋን አዳብራ በባህር ኅይል መርከቦች ሞልታ፣ አሰብን ደግሞ የንግድ መርከቦች አስፍራበት ነበር። ምጽዋ ላይ የነበሩትን የጦር መርከቦች ህወሓት እና ሻቢያ ተመሳጥረው ወደ የመንና ሌሎች የአረብ ሀገራት ወስደው በርካሽ ዋጋ መጣላቸው አይዘነጋም።
በ 1950 ዓ ም፣ ማለትም የዛሬ 67 ዓመት፣ አሰብ በስም ወደብ ይባል እንጂ ከቶም ከእውነተኛ ወደብ የሚቆጠር አልነበረም። ከተማውም በቂ የመጠጥ ውሀ እና የመብራት አገልግሎት አልነበሩትም። አሰብ ተገንብቶ በዐለም አቀፍ ደረጃ ያገለግል ዘንድ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሤ አርቀው በማሰብ በዘመናዊነት እንዲገነባ አዘዙ። የወደቡም ዋና አስተዳደር በመከላከያ ሚኒስቴር ስር ገብቶ የወቅቱ የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት፣ በወንድማማቾቹ በገርማሜ እና በመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት የተረሸኑት አርበኛው ራስ አበበ የመሀንዲሶቹን እቅድ አጸደቁት።
የግንባታውም ብድር የተገኘው ከዩግዝላቪያ መንግሥት ሲሆን የበላይ መሀንዲሶቹም ዩጉዝላቭያኖች ሲሆኑ ከኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ኢንጅነር በቀለ ነበሩ። ለወደቡ ግንባታ የተመደበው ገንዘብ 25 ሚሊዎን ብር ሲሆን ይህም ገንዘብ ለዘመኑ በጣም በርካታ ነበር።
ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ሲጠናቀቅ፣ የአሰብ ወደብ ተስፋፍቶ አስፈላጊዎቹ ቤቶች ሁሉ ተሰርተውለት በዐለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ሆነ። የባህር ትራንዚት እና የጉምሩክም ቢሮዎች ተከፍተውለት ሥራውን በስነስርስዓት ጀመረ። የከተማውም ህዝብም በቂ መብራት እና ውሀ አገኘ።
የኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ኢሳያስ አፈወርቂ እና መለስ ዜናዊ ለ ኢትዮጵያ ህዝብ ሳያማክሩ፣ የሰፊውን የኤርትራውያንንም እውነትኛ ምኞትና ፍላጎት ሳይጠይቁ በግድና በማስፈራራት ከባርነት እና ከነጻነት የቱ ይሻላችኋል፣ ብለው መገንጠልን አስመረጧቸው። እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነገር ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገጠል ከኢሳያስ አፈወርቂ ይልቅ የመለስ ዜናዊ ጥድፍፊያ ነው። ለተባበሩት መንግሥታት ማህበር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ቶሎ ትገንጠልልኝ ብሎ ሲከትብ፣ አጀብ! አጀብ! አገሩን ቶሎ ለማስገንጠል የሚጽፍ መሪ! ብለው የዐለም ፓለቲከኞች ተደመሙ። መለስ ለምን ተጣድፎ ኤርትራን ለማስገንጠል እንደፈለገ ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶች ያቀርባሉ። ከምክንያቶቹ አንዱ እናቱ ኤርትራዊ ስለሆኑ ነው፣ይላሉ። አባቱ አቶ ዜናዊ አባታቸው ደጃዝማች አስረስ ለጣልያን ገብተው ስለነበር በአባታቸው ጥፋት በትግራይ ህዝብ ዘንድ አቶ ዜናዊን በፍቅር ስላላዩአቸው እና ሚስትም አንድርልህም ስለአሉዋቸው ከኤርትራ ሴት ልጅ ፈልገው እስከሚያገቡ ድረስ ስለበደሏቸው መለስ ቂም ይዞ ነው የሚሉም አሉ። ምናልባትም፣ በሩስያ መሪ በዮሴፍ ስታሊን ጽሁፍ በሰፈረው የብሄሮች እስከመገንጠል መብት በሚለውም መርሆ መለስ አምኖበት ይሆናል። (በነገራችን ላይ፣ “መለስ” ከመባሉ አስቀድሞ “ለገስ”፣ ለገሰ ከመባሉም በፊት በልጅነቱ ነጋሲ ይባል እንደነበር የመንደሩ ሰዎች ይናገራሉ።)
ይኸው መለስ በምርጫ ዘጠና ሰባት ሕወሀት በተቃዋሚዎቿ ፓርቲዎች በእነ ቅንጅት በተሸነፈችበት ወቅት መለስ ዜናዊ ለምን ላለመሸነፍ እንደፈለገ ተጠይቆ ነበር። መልሱም የጀመርነውን ሥራ ሳንጨርስ እንዴት ጥለን እንሄዳለን፣ የሚል ነበር። ይህም ኤርትራን በሚገባ ሳላስገነጥል እንዴት ስልጣን እለቃለሁ፣ ማለቱ ነበር።
ኢሳያስ አፈወርቂ ግን ለመገንጠል አልቸኮለም ነበር። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት መሪ እስከሚመስል ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ተመችቶት ነበርና። በመለስ ትእዛዝ ለኤርትራ ካሳ ይሰጣት ተብሎ ኤርትራ በቢሊዎን የሚቆጠር ብሮች አንድ ጊዜ ተችራ ነበር። ያለቀረጥ የችርቻሮ እቃዎች አስገብታ በርካሽ እየሸጠች የመርካቶ ነጋዴዎችን ከንግድ አስወጥታለች። ይግረማችሁ ብላ የኢትዮጵያን ቡና የኤርትራ ቡና ብላ ጆንያ ላይ ጽፋ ለዐለም የቡና ገበያ ለማቅረብም ደፍራ ነበር። አዲስአበባ ይገኝ በነበረው ኤምባሲዋ ውስጥ ተቀናቃኞችዋን ከማሰርም አልፋ እስከ መግደል እንደደረሰችም በወቅቱ ይነገር ነበር። በራሱ ምክንያት እሷ ቶሎ እንድትገነጠል ይሻ የነበረው መለስ ግን በሚስጥር የኢትዮጵያን ብር ቀይሮ ኤርትራ አካብታው የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ከንቱ አስቀረባት። ይህም በመሆኑ ኢሳያስ ተበሳጭቶ “እኔ በጀርባዬ አዝዬ ወያኔን አዲስ አበባ አስገብቼአት ብቻዋን ኢትዮጵያን ልትበላ ካደችኝ” እያለ መናገር ጀመረ። በዚህ ብስጭቱም ሕወሀትን ለመበቀል ብሎ ምድረበዳውን ባድመን ሰበብ አድርጎ ነገር በመፈለግ በትግራይ ትምህርት ቤት ባሉ ህጻናት ላይ ቦምብ ጥሎ ኢትዮጵያን ወረረ። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በእዚህ ድርጊቱ ተቆጥቶ ሆ! ብሎ ዘመተበት። የአትዮጵያም ሰራዊት በሸናፊነት እየተመመ ወደ አሰብ እና አስመራ ሲገሰግስ ይኸው መለስ ዜናዊ አስቆመው። በሕወህት ውስጥ የነበሩ እንደ ስዬ አብርሀ አይነቶች ከተዋጋን አይቀር ለምን አሰብን አንይዝም ብለው ቢቆጡ ሙሰኞች ተብለው ዘብጥያ መወርወራቸው የዛን ጊዜ ትዝታ ነው።
አሁን በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ እና የሕወሀት ጦር ሰራዊት ሲዋጉ የኢሳያስ ጦረኞች ትግራይ ውስጥ ገብተው ህወሓት ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ያባረረቻቸውን ኤርትራውያን በማስታውስ ቂም ይዘው በአያሌው ተበቅለዋቸዋል።።
ኢትዮጵያ ለኤርትራ ብዙ ነገር አመቻችታላት ነበር። ነገር ግን ኢሳያስ አፈወርቂ በቃሉ የሚረጋ ሰው ሆኖ አልተገኘም። በተለያዩ ጊዜያት ስለአሰብ ሲጠየቅ ኢትዮጵያ በነጻ ልትገለገልበት እንደምትችል በአፉ ይገልጻል። በተግባር ግን ፍንክች የአባ ቢላኋ ልጅ ነው። በቅርቡ እንኳን አሁን ከአለው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ አሰብን በጋራ ለመጠቀም ተዋውሎ ኢትዮጵያ በእሷ በኩል ያለውን ወደ አሰብ የሚወስደውን አውራ ጎዳና ብዙ ገንዘብ አፍስሳ አነጠፈች። ኤርትራ ግን የራሷን ድርሻ አልፈጸመችም። ከነጭራሹ የተሰባበረውን እና የፈራረሰውን የአሰብ ወደብ ሁሉ ኢትዮጵያ እንድትገነባላት ትከጅላለች።
የኢሳያስ አፈወርቂ ዋናው ቅዠት ኤርትራን ታይዋን አድርጌ ብዙ ህዝብ የአላትን ኢትዮጵያን የሸቀጤ ማራገፊያ አደርጋታለሁ ማለቱ ነበር። ይህንንም ለመተግበር ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥተናታል። እሷ በጎሳ ጦርነት ተጠምዳ እርስ በእርሷ ስትፋጅ እኛ በሰላም እየኖርን በኢንዱስትሪ እና በኢኮኖሚ ወደፊት እመር! እንላለን፣ ሲል ታብዮ ነበር። ዳሩ ግን ቅዠቱ ተነነበት። ለሀገሩ የረባም ኢንደስትሪ ሳያቋቁም እና የኤኮኖሚ አውታር ሳይዘረጋ ጊዜው መሸበት።
ለማንም በማይበጅ ባድመ በሚባል ምድረበዳ ይገባኛል አሳቦ ኢሳያስ አፈወርቂ ጦርነትን ጭሮ ከኢትዮጵያም ከኤርትራም በኩል መአት ሰው እንዲያልቅ ምክንያት ሆነ። በዚያው በጦርነቱ ወቅትም ከባህር ማዶ መጥተው ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ የነበሩ ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን አለአግባብ ወርሶ አስቀረ። ኢትዮጵያውያን ባለቤቶቹ አዝነው ቀሩ። ፍጹም የውንብድና ሥራ እና ዐይን ያወጣ ዝርፊያ ነበር ኢሳይ የፈጸመው።
ኢሳያስ አፈወርቁ የማይገነዘበው ወይም ሊገነዘብው የማይፈልገው ነገር 120 ሚሊዎን ህዝብ ተሸክማ
በመሬት የተከበበችው ኢትዮጵያ የባህር በር ታገኝ ዘንድ ግድ እንደሚላት ነው። በግድም በውድም በዐለም አቀፍ ህግም ኢትዮጽያ ወደብ እንዲኖራት መፈቀዱ አይቀሬ ነው።
በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኞች ጉዳት እንዳያደርሱ ጸጥታንና እና ደህንነትን ለመጠበቅም ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ያለ በውትድርና ጠንካራ ሀገር የለም። ይህንንም እውነት የአሜሪካ እና የአውሮፓም መንግሥታት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለ እዚህም ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ወደብ የማግኘት መብት እንደአላት ይገነዘባሉ።
ወደ አሰብ ስንመለስ፣ ደርግ በመውደቅ ላይ ሳለ በሰላም ስልጣንን ለመረካከብ ወያኔ እና የደርግ ተወካዮች ለንደን ላይ በአሜሪካ ሸምጋይነት ሲነጋገሩ እንደነበር አይዘነጋም። በእዚህ ሰአት አደራዳሪው ሄርማን ኮህን ደጋግሞ በአደባባይ እንደተናገረው፣ መለስን ለብቻው ጠርቶት አሰብን ለኢትዮጵያ ያዝ፣ ለትንሿ ኤርትራ ምጽዋ ይበቃታል፣ ቢለው አንተን እዚህ ውስጥ ምንም አያገባህም፣ አሰብ የኤርትራ ነው፣ ሲል አፍቃሬ ኤርትራነቱን በቁጣ መሰከረ። በሌላ ጊዜም ስለአሰብ እና ስለኢትዮጵያ ወደብ-አልባነት ሲወራ መለስ ሆዬ “ገበያ ወጥተን የፈለግናቸውን የሌላ ሀገሮች ወደቦች አማርጠን በገንዘባችን እንከራያለን” አለ። ብሎም አልቀረ ከመቶ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ግዛት ከነበረችውና በደርግ ፈዛዛነት ወደ ኢትዮጵያ እጅ ካልተመለስችው ጂቡቲ በሚዘገንን ዋጋ ወደብ ተከራይቶ ኢትዮጵያን አስከሰራት። ስለአሰብ ውሀ ሲወሳ ደግሞ፣ ኤርትራውያኖች ቢሹ ግመላቸውን ያጠጡበት፣ ብሎ ለአፉ ለከት ሳይኖረው አምቧረቀ።
በሕወሀት አሳልፎ ሰጭነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ አሰብን ከመመንተፏ በፊት ግን የንጉሠነገሥቱ እና የደርግ መንግሥታት አሰብ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ የሀቅ እርስት መሆኑን ተገንዝበው አልምተውት ይጠቀሙበት ነበር። እዚህ ላይ መዘከር የሚገባው በቀድሞው የሶቭየት ኅብረት ተራድኦ የተቋቋመው የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ ነው። ይህ ተቋም በዘመኑ ለኢትዮጵያ እጅግ የሚጠቅም፣ በቀን 800 ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ድፍድፍን ያጣራ ነበር። ኤርትራ ይህን የራሷ ስታደርገው ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቋሙ ባለሙያዎች ተበተኑ። ተቋሙም ሥራ ፈቶ ወደ ዝገት ተለወጠ። ራሱን ወደቡንም ኤርትራ ምንም አልፈየደችበት። እሱም አርጅቶ ዋጋ ቢስ ሆነ።
እንግዲህ አሰብ በጉልበት እና በሽፍጥ ከኢትዮጵያ ተነጥቆ ለኤርትራ የተዳረገ የኢትዮጵያ አንጡራ ገንዘብ እና እርስት መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያ፣ ቁጥሩ ከ 120 ሚሊዎን የማያንሰው ህዝቧ አንድ የባህር በር አጥቶ ሲታፈን፣ ሁለት የባህር ወደቦች ከያዘችው፣ ባለ ጥቂት ሚሊዎን ሰዎች ከሆነችው ከኤርትራ ጋራ ተስማምታ በመተዛዘን በቀድሞ እርስትዋ መጠቀም ካልቻለች እና በጉልበት ብታስመልስ ምን ይደንቃል? ምንም ከጦርነት ይልቅ ሰላም ቢመረጥም፣ ሰው በኃይል የተነጠቀውን አንጡራ ሀብቱን በኃይል ማስመለስ የተለመደ የተፈጥሮ ህግ ነው። ከኀይል በፊት ግን ያለመሰልቸት የመግባባት እና የእርቅ ድርድርን ማስቀደም ከወንድማማቾች ሕይወት ጥፋት እና ከጋራ ንብረት ውድመት ይሰውራል። እርቅ ከተገኘም ሁለቱም ህዝቦች በጋራ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
*******************************
March 31, 2025, ካሊፎርንያ
