Amhara Media Corporation/ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 

“ሕግን መነሻና መዳረሻ አድርገን ማንነታችንን ለማጽናት እየሠራን ነው” አቶ አሸተ ደምለው

ሁመራ: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ባለፉት የነጻነት ዓመታት ከወሰን እና ማንነት ጉዳይ አንጻር በተከናወኑ ተግባራት ላይ በሁመራ ከተማ የግምገማ እና የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ሕግን መነሻ እና መዳረሻ በማድረግ የሕዝቡን ማንነት በማጽናት እና ወሰኑንም በመጠበቅ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ የመላው አማራ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።

ቀጣናው አጎራባች ሀገራትን የሚያዋስን መኾኑን ያነሱት አሥተዳዳሪው የዚህን አካባቢ ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድና ተገቢውን መፍትሔ መስጠት ከኢትዮጵያ አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል መኾኑን አመላክተዋል።

የማንነት አጀንዳችን የእውነት እና የፍትሕ ጥያቄ ነው፣ ጥያቄው እንዴት ይፈታ ሲባልም ሕግ የመፍትሔው አካል ይኾናል፣ በመኾኑም ሕግን ይዘን እና ታሪክ አጣቅሰን እየታገልን ነው ብለዋል።

ባለፉት የነጻነት ዓመታት ቀላል የማይባሉ ተግባራትን ማከናወናችን ቢታወቅም የቤት ሥራችን አልተቋጨም ነው ያሉት።

ሕዝባችን አማራዊነቱን አረጋግጦ እየኖረ ነው ያሉት አቶ አሸተ ነገር ግን ነጻነቱ ሕጋዊ ሰውነት ባለማግኘቱ ከዚህ በፊት ካከናወንናቸው ተግባራት ያልተናነሱ ተግባራትን ለማከናወን ሁላችንም ቁርጠኛ መኾን ይገባናል ብለዋል።

በእጃችን የገባን ነጻነት ማስቀጠል የሁላችን ድርሻ ነው፣ ሕዝቡ በልጆቹ እየተመራ እና እየተዳደረ ነው፣ ከሀገራዊ ጥቅሞች እኩል መሳተፍ የሚያስችሉትን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ለመጠቀም ደግሞ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት ስላለብን በጀት እና መሰል መብቶችን ለማረጋገጥ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

ሌላውን ብንረሳ እንኳ በማይካድራ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አንዘነጋውም፤ ይሄንን ጭፍጨፋ የፈጸመው ኀይል ተመልሶ ቢመጣ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከእኛ እኩል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይረዳል ብለዋል።

ለዚህ ማሳያ ይህ ኀይል ከሰሞኑ ሱዳን ወስጥ በሚኖሩ ወገኖች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ማረጋገጫ መኾኑን ነው ያነሱት።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የጸጥታ መምሪያ ኀላፊ እና ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ትግላችን ምክንያታዊ እና ሰብአዊ ነው ብለዋል። የነጻነት እና የማንነት ጥያቄው እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሊረዳው የሚችል እና የሚገባ ፍትሐዊ ጥያቄ መኾኑን ነው የተናገሩት።

በግምገማው እና በውይይቱ ባለፉት ዓመታት ሕዝብ ያገኛቸውን ድሎች፣ የገጠሙትን ተግዳሮቶች እና ወደፊት ምን መሥራት አለብን የሚሉ ጥያቄአችንን ዳር ለማድረስ ግብዓት አግኝተናል ነው ያሉት።

ዞኑ የራሱ መዋቅር እንዲኖረው መደረጉ፣ በራሱ ልጆች መተዳደሩ፣ ሕዝቡ በባሕሉ እና በቋንቋው ሀዘን እና ደስታውን መግለጽ መቻሉ በለውጡ መንግሥት ያገኘው እና ከነጻነት በኋላ የተጎናጸፈው ድል ነው ብለዋል።

ሕዝቡ በመሰለው እና በወደደው ቋንቋ መናገር፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራት እና መደራጀት መቻሉ የማንነት ጥያቄው ካስገኛቸው ፍሬዎች መካከል ናቸው ነው ያሉት።

ከባርነት የወጣው ሕዝባችን ዛሬ የነጻነት አየር እየተነፈሰ ነው ያሉት ኮሎኔሉ ይሄንን ነጻነት መቋጨት ግን ከቀሪ ተግባራቶቻችን መካከል ዋነኛው መኾኑን ኹላችንም እንረዳለን ብለዋል።

የጤና አገልግሎት በመስጠት፣ ትምህርት በማስተማር፣ ሕዝብን ያሳተፈ የመሠረተ ልማት ግንባታ በማከናወን ሕዝብን ባለ ውስን ሀብት እያገለገሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ የተሻለ አገልግሎት ማግኘት የሚገባው ሕዝባችን በበጀት አለመኖር ምክንያት መስተጓጎሎች እየገጠመው መኾኑ ከነጻነት በኋላ ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል ይጠቀሳል ብለዋል።

ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የወሰን እና ማንነት ጥያቄአችን ተገቢውን ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ በቀጣይ በምናከናውናቸው ብርቱ ተግባራት ላይ ከሁሉም ባለድርሻ አካል ጋር መግባባት ችለናል ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሕዝቡ ነጻነቱን በአግባቡ እየተጠቀመበት መኾኑን ገልጸዋል። ለእያንዳንዷ እንቅስቃሴያችን ቅድሞ ኹኔታዎችን አስቀምጦ ተግባርን መፈጸም፣ጥያቄዎችንን ባጭር ጊዜ ለመቋጨት ያስችለናል ነው ያሉት። የዞኑ ሕዝብ ሰላም ፈላጊ ነው፤ ማንነታችን የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!