ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ

ከ 5 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር በስህተት ኤል-ሳልቫዶር ወደሚገኝ እስር ቤት የላከውን ግለሰብ እንዲመልስ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የትራምፕ አስተዳደር ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ የተባለው ግለሰብ “በአስተዳደራዊ ስህተት” ምክንያት ወደ ኤል ሳልቫዶር መላኩን ቢያምንም የግለሰቡን መመለስ “እንደሚያመቻች እና እንዲያስፈፅም” የተባለውን ውሳኔ ይግባኝ እንደሚጠይቅበት አስታውቋል።

ሐሙስ ዕለት ዘጠኙም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በአንድ ድምፅ የግለሰቡን መመለስ አስተዳደሩ እንዲያስፈፅም አዘዋል።

ትዕዛዙ “መንግሥት የአብሬጎን ኤል ሳልቫዶር ከሚገኝ እስር ቤት መፈታት ‘እንዲያመቻች’ እና ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ሁኔታዎችን እንዲያሳልጥ” ይላል።

ከኤል ሳልቫዶር ተሰዶ ወደ አሜሪካ የመጣው ጋርሲያ ባለፈው ወር በአውሮፕላን ተጭነው ወደ ኤል ሳቫዶሩ አስፈሪ እስር ቤት ሴኮት ከተላኩ ግለሰቦች መካከል ነው።

ይህ እስር ቤት ኤል ሳቫዶር እና አሜሪካ በገቡት ስምምነት መሰረት አደገኛ የሚባሉ የወንበዴ ቡድን አባላት የሚታሰሩበት ነው።

ሐሙስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ካሳለፈ በኋላ የጋርሲያ ጠበቃ ሳይመን ሳንዶቫል-ሞሸንበርግ በሰጡት አስተያየት “የሕግ የበላይነት ተከብሯል” ብለዋል።

“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የታችኛቸው ፍርድ ቤት የወሰነውን መንግሥት ኪልማርን መመለስ አለባት የሚለውን ውሳኔ አፅድቋል።”

የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስገባው አስቸኳይ ይግባኝ የሜሪላንድ ዳኛ የሆኑት ፓውላ ዚኒስ መንግሥት ጋርሲያን እንዲመልስ የማዘዝ ሥልጣን የላቸውም ብሎ ነበር።

አስተዳደሩ አክሎ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የኤል ሳልቫዶር መንግሥት ጋርሲያን እንዲመልስ የማስደረግ ኃይል እንዴለው ገልጿል/

ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኛ ፓውላን ውሳኔ ውድቅ ቢያደርገውም ጉዳዩን እንደሚመለከው አስታውቆ ነው ሐሙስ ውሳኔ ያስተላለፈው።

የትራምፕ አስተዳደር ምንም እንኳ ጋርሲያ “በአስተዳደር ስህተት ምክንያት ነው” ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላከው ቢልም ግለሰቡ ኤምኤስ-13 የተባለው የወንበዴ ቡድን አባል ነው ይላል። የጋርሲያ ጠበቃ ይህን ያስተባብላሉ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞ የትራምፕ አስተዳደር በምን ያክል ጊዜ ጉዳዩን እንደሚያስፈፅም ያሉት ነገር የለም።

የ29 ዓመቱ ጋርሲያ በሕገ ወጥ መንገድ ነው ወደ አሜሪካ የገባው። በአውሮፓውያኑ 2019 ሜሪላንድ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ቢሆንም ወደ ሀገሩ ቢመለስ ሊገደል ይችላል በሚል በወቅቱ ዳኛው ጥበቃ እንዲደረግለት ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

አሜሪካዊት ዜጋ ያገባው ጋርሲያ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 15 ነው በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላከው።