ሪፋት ሬድዋን ከመገደሉ በፊት ጥቃቱን በምስል ቀርፆ አስቀምጧል።
የምስሉ መግለጫ,ሪፋት ሬድዋን ከመገደሉ በፊት ጥቃቱን በምስል ቀርፆ አስቀምጧል።

ከ 5 ሰአት በፊት

በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉ 15 የፍልስጤም የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ልጃቸው አንዱ የሆነው ሃጃ ኡም መሐመድ “ሪፋት ሲገደል ልቤ እና ነፍሴ አብረውት ሞቱ” ይላሉ።

የ23 ዓመቱ ሪፋት ሬድዋን ለአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ከፍልስጤም ቀይ ጨረቃ አምቡላንስ ጋር ሲጓዝ ነበር ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቃት የደረሰበት።

“በተለይም አካባቢው ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ለአምቡላንስ ክፍት በመሆኑ ይገደላል ብዬ አስቤ አላውቅም” በማለት ያክላሉ።

እስራኤል አምቡላንሶቹ በጨለማ የግንባር እና የአደጋ መብራት ሳያበሩ በመጠጋታቸው “በጥርጣሬ” ወታደሮቿ ተኩስ መክፈታቸውን ተናግራለች።

በሪፋት የተቀረፀ እና ከህልፈቱ በኋላ ስልኩ ውስጥ የተገኘው ተንቀሳቃሽ ምሥል የቆሰሉ ሰዎችን ለማከም የስልክ ጥሪ ሲደርሳቸው የተሽከርካሪዎቹ መብራት በርቶ እንደነበር ያሳያል።

“እናቴ ይቅር በይኝ. . . ይህ ሰዎችን ለመርዳት የመረጥኩት መንገድ ነው” ሲል ሪፋት ከመገደሉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሲናገር ይደመጣል።

ኡም መሐመድ ልጃቸው ይቅርታ የጠየቀው በድጋሚ እንደማያገኙት በማወቁ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ሪፋት ሁሌም ከቤት ለሥራ ሲወጣ ለፈጣሪ አደራ እሰጠዋለሁ” የሚሉት እናት፤ “በመላው ጋዛ ከሰሜን እስከ ደቡብ የተጓዘ ጀግና ነበር” ይላሉ።

ሪፋት ሐማስ ጥቅምት 2023 ያልተጠበቀ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ከከፈተ እና ይህን ተከትሎ እስራኤል ከጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ ነበር ለፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በጎ ፈቃደኛ ሆኖ መሥራት የጀመረው።

ኡም መሐመድ እንደሚሉት ልጃቸው የሰብዓዊነት ሥራን ይወድ ነበር።

“ቁስለኞችንም ለሕክምና በራፋ ድንበር ወደ ግብፅ ወስዷል” ይላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ኡም መሐመድ ሪፋት ሕይወቱ ያለፈ ቀን ብዙ ሰዎችን ለሞት የዳረጉ ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ ከአንቡላንስ ጋር መጓዙን ያብራራሉ።

“ከእነርሱ [ከሟቾቹ] ውስጥ አንዱ እንደሚሆን አላወቅኩም ነበር” ይላሉ።

የሪፋት እና የባልደረቦቹ አስከሬን እስኪገኝ ድረስ አንድ ሳምንት ፈጅቷል።

“ኢድ አልፈጥርን ከሪፋት ጋር በማክበር ፈንታ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማካሄድ ከቀይ መስቀል ጋር አስከሬኑን ከናስር ሆስፒታል ለማምጣት ሄድን” ሲሉም ያስታውሳሉ።

ኡም መሐመድ ልጃቸው “ፍፁም ቆንጆ” ሰው እና እህት እና ወንድሞቹ ካገቡ በኋላ የቤተሰቡ ብቸኛ አጋዥ እንደነበር ይናገራሉ።

ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ከተገኘ በኋላ እስራኤም አምቡላንሶቹ መብራት አላበሩም ነበር የሚለውን የወታደሮችን ሪፖርት በሚመለከት የሰጠችው የመጀመሪያ ምላሽ የተሳሳተ መሆኑን አሳውቃለች።

ወታደሮቹ ሪፋትን ጨምሮ 15ቱን የሕክምና ባለሙያዎችን አስከሬን ከአውሬዎች ለመከላከል በሚል በአሸዋ መቅበራቸውን አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ተናግረዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአካባቢው ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ ማዘጋጀት ባለመቻላቸው አስከሬኑ ጥቃቱ ከደረሰ ከሳምንት በኋላ ተገኝቷል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ቡድን አስከሬኑን ሲያገኝ ድርጊቱን የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምሥል የያዘውን የሪፋትን ስልክ ጨምሮ ማግኘቱ ታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱ ላይ “ጥልቅ ምርመራ” እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

ቀይ ጨረቃ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግን ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ከጥቃቱ የተረፈው ብቸኛው የሕክምና ባለሙያ ሙንተር አቤድ እርሱ እና ባልደረቦቹ ላይ ያለማስጠንቀቂያ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ይናገራል።

“ከተሽከርካሪው ኋላ ወለል ላይ ሆኜ ወድቄ ነበር። ከባልደረቦቼ የሲቃ ድምፅ ውጪ ምንም ድምፅ አልሰማሁም” ሲል ስለ ክስተቱ ተናግሯል።

 ከጥቃቱ ብቸኛ የተረፈው ሙንተር አቤድ
የምስሉ መግለጫ,ከጥቃቱ ብቸኛ የተረፈው ሙንተር አቤድ

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር ባለሙያዎች የነበሩበት ስፍራ በእስራኤል ጦር “ቀይ ቀጣና” ተብሎ ያልተመደበ አደገኛ አካባቢ በመሆኑ፤ በቦታው ለመንቀሳቀስ ቅድመ ቅንጅት አያስፈልግም ብሏል።

ማኅበሩ የመጀመሪያ ደረጃ የፎረንሲክ ምርመራ ሪፖርት የሕክምና ባለሙያዎቹ “በሰውነታቸው የላይ ክፍል በደረሰባቸው ደጋጋሚ የጥይት ድብደባ” መገደላቸውን እንደሚያሳይ የገለፀ ሲሆን፤ ይህም “ሆን ተብሎ የተፈፀመ ግድያ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ” መሆኑን ገልጿል።

ከሟቾቹ መካከል የሐማስ ባለሥልጣናት ይገኙበታል የሚለውን የእስራኤል ክስንም ማኅበሩ ማስረጃ የሌለው ሲል አጣጥሎታል።

ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ፤ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።

በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከዚህ ጥቃት በኋላ ከ50 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በእስራኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል።

ባለፈው ጥር ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መጋቢት ላይ ተጥሷል። በአሁኑ ውቅት በጋዛ 58 ታጋቾች ያሉ ሲሆኑ፤ ከመካከላቸውም 24ቱ በሕይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።