መላጣ ሰው

ከ 5 ሰአት በፊት

ፀጉር መሳሳት አሊያም መመለጥ ፆታ፣ ዘር እና ቀለም አይመርጥም። ሁሉም ሰው የፀጉር መሳሳት እና መነቃቀል ሊያጋጥመው ይችላል።

በዘር፣ በጤና መታወክ፣ በዕድሜ መግፋት አሊያም በምንከተለው የሕይወት ዘይቤ አማካኝነት የፀጉር መመለጥ ወይም መነቃቀል ያጋጥማል።

መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት ኤኒታን አጊዲ የፀጉር ዕድገት እና መመለጥ ላይ የሕክምና ምርምር ያደረጉ ባለሙያ ናቸው። ስለፀጉር መመለጥ መንስዔ እና መፍትሔ ተጠይቀው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ማንም ሰው ከፀጉር መመለጥ አያመልጥም። ስለፀጉር እንክብካቤ ብዙ እውቀት ያለኝ እኔ እንኳ ከዚህ ቀደም የፀጉር መሳሳት አጋጥሞኝ ነበር” ይላሉ።

‘ዴርማቶሎጂክ ሰርጀሪ’ የተባለው የአሜሪካ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ መሠረት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 የሆኑ 16 በመቶ ወንዶች የፀጉር መመለጥ ያጋጥማቸዋል።

ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 39 ባሉ ወንዶች ዘንድ ደግሞ 30 በመቶ ሲሆን፣ ከ40 እስከ 49 ካሉ ወንዶች ግማሽ ያህሉ የፀጉር መመለጥ አለባቸው።

የፀጉር መመለጥ በሕክምናው ቋንቋ አሎፔሺያ ተብሎ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ በጣም የሚያሳስባቸው ወንዶች ቢሆኑም፤ በሴቶች ዘንድም የፀጉር መመለጥ ትልቅ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

እንደ ሀርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ከሆነ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ሴቶች የፀጉር መመለጥ ያጋጥማቸዋል።

ፀጉሯን እየተሰራች ያለች ሴት

የፀጉር መመለጥን መቀልበስ ይቻላል?

የቆዳ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንቻል ፓንዝ እንደሚሉት የመጀመሪያው እርምጃ ባለሙያ ማማከር ነው። ምክንያቱም በቀን ተቀን ውሏቸውን ለውጥ የሚያመጡ መላዎችን መጠቀም እንችላለንና።

“በፕሮቲን የበለፀገ ምግብ መመገብ ለፀጉር እድገት እጅግ ጠቃሚ ነው” ይላሉ ባለሙያዋ። “የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካለ ቀድሞ ማስተካከል ያለብን እሱን ነው።”

በርካቶች ፀጉራቸው መሳሳት መጀመሩን ሲመለከቱ እንደ ሚኖክሲዲል ያሉ ኬሚካሎች ያሏቸውን ክሬሞችን አሊያም ካፌይን ያላቸውን ምርቶች ይጠቀማሉ።

ሚኖክሲዲል ብዙውን ጊዜ በፈሳሽ አሊያም በአረፋ መልክ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው። ይህ ኬሚካል ወደ ፀጉር ሥር የሚሄደውን ደም ፍሰት በመጨመር ይታወቃል። ይህ ለፀጉር እድገት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ዶ/ር ፓንዝ እንደሚያስጠነቅቁት ሚኖክሲዲል “የፀጉር መሳሳትን ይከላከል ይሆናል እንጂ አዲስ ፀጉር እንዲበቅል አያግዝም።”

በተለይ ደግሞ ወንዶች ኪቶኮናዞል የተባለውን ኬሚካል ለፀጉር መመለጥ ይጠቀማሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ፎሮፎር ለመከላከል ጥሩ አማራጭ ነው፤ ምክንያቱም ፎሮፎር የፀጉር መመለጥን ሊያባብሰው ይችላል።

ከሚኖክሲዲል በለተየ ኪቶኮናዞል አናታችን ላይ የሚወጡ ፈንገሶችን ለመከላከል የሚረዳ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ኪቶኮናዞል ዲኤችቲ የተባለውን ፀጉር የሚመልጥ ሆርሞን የመቀነስ ኃይል አለው።

“ብዙዎች ፀጉር መመለጥ ማለት የሆነ ነገር በመጠቀም የሚጠፋ እና ፀጉር ተመልሶ የሚበቅል አድርገው ነው የሚያስቡት። እንደዚህ አይደለም፤ የፀጉር መመለጥን ለመቀልበስ ሁሌም እንክብካቤ ማድረግ ያሻል” ይላሉ ዶ/ር ፓንዝ።

ፀጉሯን በመስታወት እያስተካከለች ያለች ሴት

የሕይወት ዘቤን መቀየር

ፀጉርዎ ምን ዓይነት እንደሆነ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው።

የፀጉር ባለሙያዋ አጊዲ አፍሮ በሚባለው ፀጉር ላይ ጥናት አድርገዋል። እሳቸው እንደሚሉት በጣም ጥብቅ ተደርገው የሚሠሩ አሊያም ክብደት ያላቸው ቁጥርጥሮች እና በግለት የሚሠሩ ፀጉሮች በጊዜ ለመመለጥ ሊዳርጉ ይችላሉ።

“እንዴት ነው ፀጉራችንን መሠራት ያለብን የሚለውን ማወቅ ጠቃሚ ነው። ክብደት ያላቸው እና ጥብቅ ያሉ የፀጉር አሠራሮችን ስንጠቀም የፀጉራችን ግንድ ላይ ጫና ልናሳድር እንችላለን” ይላሉ።

የፀጉር ግንድ አሊያም ከስሩ ጋር አጣብቆ የሚይዘው አካል ለፀጉር እድገት ያገለግላል። ጭንቅላታችን አዲስ ቆዳ እንዲያበቅል የሚያግዘውም ይህ ነው።

“በሚከተሉት የፀጉር ‘ስታይል’ ምክንያት ለሁለት ዓይነት የፀጉር መመለጥ የተጋለጡ ደንበኞች አጋጥመውኝ ያውቃሉ።”

ሌሎች ከግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ነገሮች ትምባሆ ማጤስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጭንቀት እና የእንቅልፍ እጦት የፀጉር መመለጥን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ነው።

ዶ/ር ፓንዝ እንደሚመክሩት “ጭንቅላትዎ ቅባታማ ከሆነ ፀጉርዎን በየቀኑ አሊያም በሁለት ቀን አንዴ መታጠብ ሊኖርብዎት ይችላል።”

በተቃራኒው ደረቅ ከሆነ ደግሞ በሳምንት ሦስት ጊዜ መታጠብን ባለሙያዋ ይመከራል ይላሉ።

የፀጉር ንቅለ ተከላ

የፀጉር ንቅለ ተካላ ቀላሉ አማራጭ ነው?

የፀጉር ንቅለ ተከላ በቀዶ ሕክምና ፀጉር መትከል ማለት ነው። በርካቶች ፀጉር በማስተከል መልካቸውን በማሳመር በራስ መተማመናቸውን ከፍ ማድረግ ይሻሉ።

ምንም እንኳ የፀጉር ንቅለ ተከላ ውድ ቢሆንም ውጤታማነቱ የሚያጠራጥር አይደለም ይላሉ ዶ/ር ፓንዝ።

ነገር ግን ይላሉ ባለሙያዋ ከንቅለ ተከላ በኋላ ፀጉራችንን መንከባከብ የምናቆም ከሆነ በአምስት አሊያም በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ትክክለኛው ፀጉራችን ተመልጦ የተተከለው ፀጉር ብቻ ሊቀር ይችላል።

“ንቅለ ተከላ ማለት ወደ ውጭ ስንወጣ ብርድ ሆኖብን ወደ ቤት ተመልሰን ጃኬት መደረብ ማለት ነው. . .”

“ትንሽ ቆይቶ ድጋሚ ሊበርደን ይችላል።”