
10 ሚያዚያ 2025
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው የህወሓት ክንፍ መካከል ያለው መጠዛጠዝ በነባሮቹ የፓርቲው አመራሮች የበላይነት የተቋጨ ይመስላል።
ከሁለት ዓመት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ቆይታ በኋላ ማክሰኞ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. አቶ ጌታቸው ረዳ ሥልጣኑን ለምክትላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ አስረክበዋል።
ቀጣይ መዳረሻቸው በግልጽ ያልታወቀው የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው፤ ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም. ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ አቅራቢ ዋሂጋ ማውራ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
በዚህ ቃለ መጠይቅ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሲመሩት ስለነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ስላጋጠሙት ተግዳሮቶች ተናግረዋል። ስለ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ያላቸውን ግምገማ አጋርተዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንቱ ለየትኛዎቹ ጉዳዮች ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ እና ሊያጋጥማቸው ስለሚችሉ ተግዳሮቶችም ገልጸዋል።
ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ እና ትግራይ ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት አቶ ጌታቸው ስለ ወደፊት ተሳትፏቸውም ተናግረዋል። እነሆ ቃለ መጠይቁን…

ቢቢሲ- የሁለት ዓመት የሥልጣን ዘመንዎን መለስ ብለው ሲያዩት ቁልፍ ተብለው የሚጠቀሱ ስኬቶችዎ ምን ነበሩ?
አቶ ጌታቸው ረዳ – በድጋሚ ልንገባበት እንችል የነበረው ጦርነት ተመልሶ እንዳያገረሽ ማድረጋችን እንዲሁም ለለውጥ ያለን ተነሳሽነት እና የሰላም ጉጉትን መጥቀስ እችላለሁ። ማለት የምችለው ይህንን ነው።
ቢቢሲ- በስልጣን ዘመንዎ የሚጸጽቶት ነገር አለ? ምናልባት ያመለጡ እድሎች?
አቶ ጌታቸው ረዳ – አዎ። ጸጸት ማለት፤ ቀደም ብለን ልናከናውን እንችል የነበራቸው እና ማድረግ የነበሩብን [ጉዳዮች ነበሩ]። ለምሳሌ፣ የተፈናቃዮችን መመለስ። እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ውስጥ ያለው ለማይጠቅም ሥልጣን የሚደረግ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ይህንን እንዳንፈጽም አዳጋች አድርጎታል። የሚጸጽተኝ ዋነኛው ተጠያቂ እኔ ስለሆንኩ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ያለንበት ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ ያደረገው መጓተት አካል ነበርኩ።
ቢቢሲ- ሥልጣን እንዲለቅቁ ምክንያት የሆነው ዋነኛው ጉዳይ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? ውስጣዊ ፖለቲካ ነው? ወይስ የተፎካካሪ ቡድኖች ናቸው?
አቶ ጌታቸው ረዳ – እየውልህ፤ የፖለቲካ አመራሩ ሂደቱን እና የእኔን አመራር ለማበላሸት ሁሉንም ዓይነት ጥረት ሲያደርግ ነበር። ነገር ግን የፖለቲካ አመራሩ ብቻ አይደለም። ወታደራዊ አመራሩም በሆነ ደረጃ የዚህ አካል ነበር። ዋነኛ ተጠያቂ ባላደርገውም ውስጣዊው የፓርቲ ሽኩቻ መኖርም በአንድ ዓመት ውስጥ ልናሳካ ይገባ የነበሩ እና ማከናወን የነበሩበትን ነገሮችን እንዳንፈጽም አድርጎናል። በሕግ አንጻር ሲታይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን በተቋቀመ በሁለት ዓመት ውስጥ ያበቃል። ስልጣኑን ለማስቀጠል የሚሰጥ ውሳኔም በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ማለፍ አለበት።
ስለዚህ በዚህ ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ማንኛውም ጉዳይ የውስጣዊ የፓርቲ ሽኩቻ እና የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ አለመተግበር ውጤት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፤ የፌደራል መንግሥት የአመራር ለውጥ መደረግ እንዳለበት ከተሰማው፤ ይህንን ማድረጋቸው ምክንያታዊ ይመስለኛል። የእኔ መልቀቅ የብዙ ምክንያቶች ውጤት ነው፤ ከሁሉም ዋነኛው ግን የትግራይ ሕዝብ ሕይወት እንዲከብድ ያደረገው የፓርቲ ውስጣዊ ሽኩቻ ነው።
ቢቢሲ -ከሥልጣን የለቀቁት በፈቃደነኝነት ነው ወይ ፓርቲው መጥቶ ለቀጣዩ ምዕራፍ ሲባል እንዲወርዱ ጠይቆዎት ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ – አይደለም፤ የምን ፓርቲ? በህወሓት ውስጥ ያለው አንጃ ይንን ሂደት ሲያበላሽ ነበር። ሁሉንም ዓይነት የጀርባ ድርድር ሲያከናውኑ ነበር። ለፌደራል መንግሥት ይህንንም፣ ያንንም ሲያቀርቡ ነበር። የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የመሾም ሥልጣን ያላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አይሆንም እያሉ ነበር።
አሁን ግን፤ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌላ አማራጭ ማየታችን ተገቢ ይሆን እንደሆነ ጠይቀውኝ ነበር። እኔ፤ ሥልጣኑን ተጠቅሜ ለምሳሌ እንደ የተፈናቃዮች መመለስ ባሉ ስራዎች ላይ ያከናወንኩት ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ ሥልጣን ይዞ የመቀጠል ፍላጎት ያለኝ ሰው አይደለሁም።
ስለዚህ ለእኔ ጉዳዩ፤ [የጊዜያዊ አስተዳደሩ] የሥልጣን ዘመን ሲጠናቀቅ አይቀሬ የነበረ ነው። እኔ በፕሬዝዳንትነት እንድቀጥል ለማድረግ ልዩ የሆነ አሰራር መኖር ነበረበት ማለት ነው። ነገር ግን ለዚያ ሥልጣን ሲታገሉ የነበሩ ማንኛውም አካላት አሁን ካለንበት ቅርቃር ለማስወጣት የሚችል ፈጣን መውጫ መንገድ ገና አላቀረቡም።
- መንግሥት የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ “በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል” መመሪያ መስጠቱን አስታወቀ9 ሚያዚያ 2025
- ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ “ከሀገር ሉዐላዊነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እንዲቆሙ የማድረግ” ኃላፊነት ተጣለባቸው8 ሚያዚያ 2025
- የክልል ጊዜያዊ አስተዳደሮች የቆይታ ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት ማራዘም የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ1 ሚያዚያ 2025

ቢቢሲ – ስለ አዲሱ ፕሬዝዳንት ይንገሩን። የእርሳቸው ሹመት ለትግራይ ክልል ምን ማለት ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- በዚህ ጉዳይ ላይ መናገር የምፈልገው ትንሽ ነው። የማውቀው ነገር፤ የእኔ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደነበረ እና በአስተዳደሬ ውስጥ ለሚገኙ ዋነኛ ጉዳዮች ኃላፊነት እንደሚወስድ ሰው እኔ የተውኳቸው ነገሮች ይዞ ይቀጥላል ብዬ እንደምጠብቅ ነው።
በብዙዎቹ ውድቀቶች ላይ ከሌሎች ሰዎች በተለየ ከእኔ እኩል ተጠያቂ ነበር። ስለዚህ እኔ ከተውኩበት ቀጥሎ እና መከናወን ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እጠብቃለሁ። እርግጥ ነው፤ የፓርቲውን ችግር ለመፍታት አስማታዊ መፍትሔ ማምጣት ስላለበት ስራው ተቆጥሮ ተሰጥቶታል።
ፓርቲው፤ [ፕሬዝዳንቱን] እንደሾመው ያስባል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ራሱ እንደሾመው ይናገራል። እንደ አለመታደል፤ ያጋጥመዋል ብዬ የማስበው አንዱ ተግዳሮት አሁንም ሥልጣኑን ጠቅልሎ ለመያዝ ከሚፈልገው የህወሓት አንጃ የሚመጣው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የሥልጣን ጥማት ነው።
ይህንን የመጋፈጥ አቅሙ እና ክህሎቱ ይኖረዋል ወይ የሚለው ጉዳይ የሚታይ ይሆናል። እኔ እንደሚገባኝ ግን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁሉንም ልምድ አግኝቷል።
ስለዚህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቃል ኩዳኑን መጠበቅ አለመቻሉ የእርሱም ዋነኛ ውድቀት ነው። ይህንን ማስተካከል አለበት።
ቢቢሲ -ጊዜያዊ አስተዳደሩ ራሱን እዚህ ሁኔታ ውስጥ አግኝቶታል። እርስዎ የተወሰነውን ኃላፊነት እንደሚወስዱ፣ ነገር ግን ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ብዙውን እንደሚሸከሙ ተናግረዋል። ስለዚህ ለምን ሥልጣኑን ለእርሳቸው መስጠት አስፈለገ? የችግሩ አካል ከነበሩ ለምን ይመራሉ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- ይህ የእኔ ውሳኔ አይደለም። ፕሬዝዳንት እንድሾም ብጠየቅ፤ እየለቀቀ ያለ ፕሬዝዳንት ተተኪውን እንዲሾም ማድረግ ትክክል አይሆንም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን ምክክር፤ ያንን ሥልጣን ሲጎመዡ ከነበሩ ከሁሉም ሰዎች የተሻለው እርሱ እንደሆነ ሊያሳምኑኝ ሞክረዋል። ስለዚህ የመጨረሻው ውሳኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።
አሁን መናገር የምችለው ስራው ተቆጥሮ የተሰጠው ታደሰ፤ ስራውን በሚገባ እንዲሰራ፣ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች አስቀያሚ ፖለቲካ ውስጥ ውስብስቡን ጉዞ እንዲያደርግ እንዲሁም ክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ ችግሮች ክምር እንዲፈታ ተስፋ እንደማደርግ ነው። ከሁሉም በላይ በተፈናቃዮች መመለስ እና የትግራይ ሕገ መንግስታዊ ግዛቶች መመለስ ላይ ትኩረት [እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ]።
ቢቢሲ- ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር የማውራት እድሉን አግኝተው ነበር? ምን ምክር ሰጧቸው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- [ምክር] አልተጠየኩም ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ የካበተ ልምድ ላለው ሰውም ምክር የማቅረብ ፍላጎትም አልነበረኝም።
ቢቢሲ-ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንድናቸው ብለው ያስባሉ? በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ትልቁ ውድቀትዎ ተፈናቃዮችን መመለስ አለመቻልዎ እንደሆነ ገልጸዋል። አዲሱ አመራር ምን ዓይነት አስቸኳይ እርምጃዎችን ይውሰድ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- [የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት] አሁን ላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ተብለው የተዘረዘሩ ጉዳዮችን የያዘ ስምምነት ላይ ፈርሟል። ለእኔ ግን በጣም አሳሳቢው ነገር የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ የመተግበር ጉዳይ ነው።
ትጥቅ መፍታት እና መልሶ መቋቋምም አንዱ ጉዳይ ነው። የተፈናቃዮች መመለስ ግን ምናልባትም ከሁሉም እጅግ አስፈላጊው ነገር ሊሆን ነው። ይህ ለመቆጣጠር እጅጉን ያዳገተን ጉዳይ ነው። በዚህ ደስተኛ ያልሆነው እና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ አዳኝ አድርጎ የሚስለው የህወሓት አንጃ ይህንን የሚያከናውንበት እድል ይሰጠው እንደሆነ የምናየው ይሆናል።
ቢቢሲ- መለስ ብለው ሲያዩት በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ምንም ስህተት ሰርተዋል? የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ምን የተሻለ መስራት ነበረብዎት?
አቶ ጌታቸው ረዳ- [የስምምነቱን አፈጻጸም] በተደራጀ መልኩ መምራት ነበረብን። ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ማድረግ ነበረብን። ድርድር ምን እንደሆነ እንኳ ከማያውቁ አምስት የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከመጣበቅ ይልቅ ሲቪል ማኅበረሰቡን ማሳተፍ ነበረብን።
ሰፊ ፍላጎቱ በሕዝቡ በሰላም መመለስ እንጂ፤ የተፈናቃዮችን ጉዳይ የአስቀያሚ ፖለቲካ መጫወቻው የማድረግ ፍላጎት የሌለውን የወጣቱን እንቅስቃሴ እንደ አጠቃላይ ማሳተፍ ነበረብን። ዋነኛ ስህተት ብዬ የምጠቅሰው ይህንን ነው።

ቢቢሲ-የትግራይን ሕዝብ በሚገባው መልኩ አላገለገልኩትም የሚል ስሜት ያለዎት ይመስላል። ይህ ትክክለኛ አገላለጽ ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- የትግራይን ሕዝብ በአግባቡ ያላገለገለ አመራር አካል ነበርኩ ብዬ መናገር እችላለሁ። እኔ ግን በዚህ አልኩራራም። አሜሪካውያን እንደሚሉት እውነት ከሆነ መኩራራት አይደለም።
ብቸኛ ትኩረታችንን ስልጣን ላይ ማድረጋችን ስህተታችን እንደሆነ ለማሳየት የምችለውን በሙሉ አድረጌያለሁ። ነባሩን ሁኔታ ለመገዳደር የሚያስችል በጣም ንቁ እና በጣም የተደራጀ እንቅስቃሴ እንዲመራ ማገዝ እንደቻልኩ አስባለሁ። ይህ ስሜን ለመጥቀስ የሚያስችለኝ ነፍስ አድን ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ- የእርስዎ ወደፊት ምን ይመስላል? ቀጣዩ ምንድን ነው? በፖለቲካ ተሳትፎዎ ይቀጥላሉ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- አዎ፤ አንዴ እዚህ ጉዳይ ውስጥ ከገባን እና አንዴ ለትግራይ ሕዝብ አዲስ መንገድ መጠቆም ከጀመርን፤ ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። እንዲሁ ተነስቼ እንቅስቃሴውን መተው አልችልም።
የትኛውም ቦታ ብሆን በእርግጠኝነት በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ። እቅዴ በዚህ ሁኔታ መቆየት እና ለትግራይ ሕዝብ ኑሮ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።
ቢቢሲ- በሥልጣን ዘመንዎ የመጨረሻዎቹ ቀናት እና ወራት ኤርትራ የተፎካካሪዎ አመራር አጋር እንደሆነች ሲከስሱ ነበር። በኤርትራ እና በተፎካካሪው አመራር ላይ ለሚያቀርቡት ይህ ውንጀላ ምን ማስረጃ ያቀረባሉ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- እንደ የሕግ ፍርድ ቤት ማስረጃ መጠየቅ የጋዜጠኛ ኃላፊነት መሆኑን አላውቅም። ግን ይህንን ልነግርህ እችላለሁ።
ቢቢሲ- ለንግግርዎ ግን ማብራሪያ ማቅረብ አለብዎ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- ማብራሪያዬን አቅርባለሁ። ስም ልጠቅስልህ አልችልም። ይህንን ግን አውቃለሁ፤ በእኔ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ሰዎች የተወሰኑት በሕጋዊ፣ የተወሰኑት ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ ከኤርትራ ጋር ለመገናኘት ሲሞክሩ ነበር።
የግመሉን ጀርባ የሰበረው የመጨረሻ ሰበዝ [የመጣው] ግን ደስተኛ ያልሆኑ የህወሓት አካላት ውስጥ ነው፤ ሁሉም የህወሓት አንጃ አመራር ማለቴ አይደለም። ግምገማቸው ምንም ይሁን ምን፤ በህወሓት ውስጥ ያሉ የተወሰኑ አካላት በጋራ ጠላታቸው ለማበር ላይ ይህንን እድል መጠቀም ጀመሩ። ስም ልሰጥህ አልችልም ነገር ግን የተፈጠረው ይህ እንደሆነ ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ አለኝ።

ቢቢሲ- በሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የኋላ ታሪክ ላይ ያነሱትን ስጋት በተመለከተ አለመካከትዎን በአግባቡ መረዳት እፈልጋለሁ። አዲሱ ፕሬዝዳንት ከቀደመው አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች አካል ለመሆናቸው ማስረጃው ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- የእኔ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበር። የራሱን የስራ ዝርዝር መፈጸም አልቻለም። [ኃላፊነቱን] መወጣት ላለመቻሉ ታደሰን ብቻ እየወቀስኩ አይደለም። እኔ እርሱም በተመለከተ ምንም አላደረግኩም። እርሱን ማንሳት አልያም መተካት [አለመቻል] የእኔ ውድቀት ነው። ብዙ ማስረጃ አለኝ፤ ዛሬ ጠዋትም ይህንኑ ተናግሯል።
የእኔ ምክትል ነበር እናም ለጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊነት ነበረበት፤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት ነበረበት። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ የእርሱ የስራ ዝርዝር በውድቀት የተሞላ ነው። የእርሱ ውድቀቶች ግን የእኔም ውድቀቶች ናቸው።
ቢቢሲ- ከፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ሲቀበል እንደነበረ አልተናገረም? አንዳንዶች እንደሚናገሩት እንደ መሪ የጠቀሳካቸው ጉዳዮች የሚወድቁት በአንተ ትክሻ ላይ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ- ሞኝ አትሁን።
ቢቢሲ- ጥያቄ ብቻ እየጠቅኩ ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- አይደለም፤ ይህ አይነቱ ትዕዛዝ. . . ታውቃለህ፤ የትግራይ ፖለቲካ አስቸጋሪ ነው። ይቅርታ ለተጠቀምኩት…
ቢቢሲ- ይቅርታ አያስፈልግም፤ ይቀጥሉ
አቶ ጌታቸው ረዳ- የትግራይ ፖለቲካ በጣም አስቸጋሪ ነው። ራሱን፤ በራሱ የሚመራ አካል አድርጎ የሚቆጥር የሚመስል የተደራጀ ሠራዊት ያለበት ብቸኛ ክልል የእኛ ነው። የፕሪቶሪያ ስምምነት ይህንን ያልተለመደ ሁኔታ እንዲፈታ ይጠበቅ ነበር።
ታደሰ ግን እንደ ሠራዊቱ አዛዥ፤ የተወሰኑትን የእኔን ውሳኔዎች መቃረን እንደሚችል ያስባል። አንተ ባለህበት የዓለም ክፍል ለሚገኙ ሰዎች ይህንን ለመረዳት በጣም ከባድ ነው። ታውቃለህ፤ ፕሬዝዳንቱ ውሳኔ የሚያሳልፍበት እና ውሳኔም በምክትሉ በቁም ነገር የሚወሰድበት ሁኔታ አልነበረም።
ይህ አንዱ የችግሩ አካል ነበር። እርግጥ ነው፤ አንዳንዶቹ የእኔ ውሳኔዎች ተፈጽመዋል። አሁንም ግን፤ ለስኬቶቹ ኃላፊነት እንደምወስደው ሁሉ ለውድቀቶቹም ተጠያቂነቱን እወስዳለሁ።
በእኛ ጉዳይ ፖለቲካውን ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው በስልጣን ላይ ያልሆነ ፓርቲ ሁሉንም ጠቅልሎ ለመውሰድ፤ የመንግሥት ሀብትምን ለመቆጣጠር የሚሞክር መሆኑ ነው። በመንግሥት ስር መሆን የነበረበት ሰራዊት ደግሞ በራሱን የሚቆጥረው ራሱን እንደቻለ አካል ነው። ትንሽ የተወሳሰበ ነው። ለመረዳት ያስቸግራል።