
24 መጋቢት 2023
ተሻሽሏል ከ 2 ሰአት በፊት
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ ፖለቲከኞች መካከል ቀዳሚው የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንትነት ከተሰናበቱ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስሩ የአማካሪነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
በህወሓት መሪዎች መካከል በተፈጠረው የተካረረ አለመግባባት በጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪነት ለመቀጠል ያልቻሉት አቶ ጌታቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ተሹመዋል።
በትግራይ ከተካሄደው አውዳሚ የሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ከፍተኛ የህወሓት አመራር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሾም ሲሾም አቶ ጌታቸው የመጀመሪያው ናቸው።
ይህ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሰጠው ሹመት ይፋ የሆነው ለአቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥልጣናቸውን ለጄነራል ታደሰ ወረደ ካስረከቡ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው።
አቶ ጌታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ልዩ አማካሪያቸው ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ አሁን የተሰጣቸው የአማካሪነት ሹመት ሁለተኛቸው ነው።
አቶ ጌታቸው በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል ውስጥ በኃላፊነት በቆዩባቸው ዓመታት በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ ሃሳባቸውን በመግለጽ እና በመከራከር ከሚታወቁ ጥቂት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።
በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ ከመጣ በኋላ በነበሩት ባለፉት አምስት ዓመታት በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እና በግንባሩ ዋና መሥራች ህወሓት መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ፤ አቶ ጌታቸው በተፈጠረው የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ጎልተው ወጥተዋል።
በተለይ ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ወቅት በትግራይ አመራሮች በኩል የሚነሱ ሃሳቦችን በክልሉ ባሉ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመደበኛነት እየቀረቡ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይም በተደጋጋሚ ብቅ እያሉ የህወሓት አንደበት ሆነው ቆይተዋል።
ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በተካሄደው ድርድር ወቅት ግንባር ቀደም ተደራዳሪ እና በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት፣ አሁን ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ማን ናቸው?
- “በእርግጠኝነት በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ እቀጥላለሁ” – ጌታቸው ረዳ10 ሚያዚያ 2025
- ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ “ከሀገር ሉዐላዊነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እንዲቆሙ የማድረግ” ኃላፊነት ተጣለባቸው8 ሚያዚያ 2025
- ጌታቸው ረዳ እና ህወሓት በጽኑ የተፈተኑበት ሁለት ዓመታት ፍጻሜ?8 ሚያዚያ 2025
ትምህርት እና የመጽሐፍት ፍቅር
አቶ ጌታቸው ረዳ አላማጣ ውስጥ ሰኔ 1967 ዓ.ም. ነው የተወለዱት። የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው በትውልድ ከተማቸው የተማሩ ሲሆን ለታናሽ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው አርአያ መሆናቸው ይነገራል።
አቶ ጌታቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የመማር እና የማንበብ ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው፣ ከእኩዮቻቸው እና ከዘመዶቻቸው ጋር ለመማር እና ለመጫወት ጊዜ የነበራቸው ቢሆንም፣ የማንበብ ፍቅራቸው ከፍተኛ ስለነበረ ሰፊውን ጊዜያቸውን ያጠፉ የነበረው ከመጽሐፍት ጋር እንደነበረ ታናሽ ወንድማቸው ይናገራሉ።
በተለይም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ ከትምህርታዊ መጻሕፍት ባሻገር በእንግሊዝኛ የተፃፉ አዳዲስ እና ቆየት ያሉ መጻሕፍትን በማንበብ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያጠፉ ነበር።
ከእነዚህም መጻሕፍት መካከል የኒቼ፣ የካርል ማርክስ፣ የሌኒን እና ሌሎችም ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩ ሥራዎች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ካነበቧቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት ጀምሮ በእንግሊዝኛ የተፃፉ መጻሕፍትን የሚያነቡት አቶ ጌታቸው አሁንም ከመጽሐፍት ጋር እንደሚውሉ ቤተሰቦቻቸው እና በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ።

አቶ ጌታቸው የሚያነቧቸው መጻሕፍትን ባይመርጡም በዋናነት ግን በፍልስፍና፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ እንዲሁም በዓለም ታሪክ ላይ የሚያተኩሩትን መጻሕፍት ያዘወትራሉ።
አቶ ጌታቸው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸውን ያዳበሩት ከሚያነቧቸው መጻሕፍት እንደሆነ የሚገልጹት ታናሽ ወንድማቸው ዶ/ር ሞላ ረዳ “ የተዋሰውን መጽሐፍ ነገ መልስ ከተባለ ሌሊቱን ሙሉ ተቀምጦ ሲያነብ አየው ነበር” ይላሉ።
የቅርብ ጓደኛቸው እና በመቀለ ዩኒቨርስቲ ባልደረባቸው የነበሩት ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም በጻፈው አንድ ጽሑፍ ስለ አቶ ጌታቸው እና ለንባብ ስላላቸው ፍቅር አስተያየታቸውን አስፍሮ ነበር።
“ጌታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ አብሮን በትግራይ የቀድሞው ቢዝነስ ኮሌጅ ነበር የተቀጠረው። እንግዳ በሆነበት በዚያ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከእኛ ጋር ሲገናኝ አንድ ካፌ ውስጥ ጥግ ይዞ መጽሐፍ እያነበበ ነበር” ይላሉ።
“አዲስ ተመራቂ ከሙያው ጋር ካልሆነ በስተቀር ፍልስፍናን የሚነካ መጽሐፍ ሲያነብ አያጋጥመኝም” የሚሉት አቶ ሙሉወርቅ፣ ጌታቸው ግን ካሉበት የሙያ ዘርፍ ባሻገር በተለያዩ መስኮች የተዘጋጁ መጽሐፍትን እንደሚያነቡ እንዲሁም በመጽሐፍት እና በተለያዩ ሐሳቦች ላይ እንደሚወያዩ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ታዳጊዋ ኢትዮጵያ በመባል በሚታወቀው ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ በ1985 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ አግኝተዋል።
ከመምህርነት ወደ ፖለቲካ
አቶ ጌታቸው ረዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁ በኋላ መቀለ ዩኒቨርሲቲን በመምህርነት ተቀላቅላቅለው በሕግ ትምህርት ክፍል አገልግለዋል።
ከዚያም በኋላ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ አላባማ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ሁለተኛ ዲግሪ ለማግኘት ችለዋል።
ከዚህ በኋላ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ማስተማር የቀጠሉ ቢሆንም፣ ብዙም ሳይቆዩ በ1997 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በኃላፊነት ተመድበው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።
ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በኋላ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ኢህአዴግ ከባድ ፈተና ገጥሞት የነበረ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው ፓርቲያቸው እንደጠላት ሲመለከታቸው በነበሩ የግል ጋዜጦች ላይ የድርጅታቸውን ሃሳብ የሚገልጹ ጽሑፎችን ያወጡ ነበር።
በተለይም በኢህአዴግ ዘመን ከታዩ የፕሬስ ውጤቶች መካከል ከፍተኛ ተነባቢነት በነበራት “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ በፓርቲያቸው ላይ የሚቀርቡ ትችቶችን በመከላከል እና አቋሙን በመግለጽ ያቀርቡ በነበረው ጽሑፍ ይታወቃሉ።
አቶ ጌታቸው ከመምህርነት ሙያ ወጥተው ወደ ፖለቲካ እና የመንግሥት የኃላፊነት ቦታን ከያዙ በኋላ፣ በተለይ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩባቸው ጊዜያት በሁለቱም ከፍተኛ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በኃላፊነት ሠርተዋል።
በዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር እና ዋና ዳይሬክተር፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ልዩ አማካሪ ነበሩ። በተጨማሪም በአላማጣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠው ነበር።
አቶ ጌታቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች እንደሚሉት ምንም እንኳን በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ ቢሆንም፤ ቀለል ያለ ሕይወትን የሚመሩ እና ወደ ፈለጉት ቦታ ያለ አጃቢ በራሳቸው መሄድ እና መቆየትን የሚመርጡ ናቸው።

ለውጡ እና ወደ መቀለ መሄድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕህመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ጉልህ ለውጥ እና ሽግሽግ ሲካሄድ፣በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ ትልቅ ለውጦች መታየት ጀመሩ።
በዚህ ምክንያት ግንባሩን ከመሠረቱት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ዋነኛው የሆነው ህወሓት በብዙ መልኩ ከአዲሱ መንግሥት እና ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ጋር መጣጣም ባለመቻሉ ከኢህአዴግ ራሱን አገለለ።
ይህንንም ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሌሎች የህወሓት ከፍተኛ ፖለቲከኞች እና ባለሥልጣናት ጋር ወደ ትግራይ ተመልሰው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) አማካሪ፣ እንዲሁም የህወሓት እና የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ ሆነው ሠርተዋል።
አቶ ጌታቸው በፖለቲካው እና በሕዝብ ግንኙነቱ ዘርፍ የህወሓት ቁልፍ ሰው መሆናቸውን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አስመስክረዋል። በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ በተደረጉት ድርድሮች ወቅት ከፊት መስመር ላይ እንደነበሩ በግልጽ ታይቷል።
ሰላም ያመጣውን ስምምነት ህወሓትን በመወከል የፈረሙት አቶ ጌታቸው ከፌደራል መንግሥቱ፣ ከአህጉራዊ፣ ከዓለም አቀፋዊ እና ከምዕራባውያን አገራት ጋር በትግራይ በኩል በነበሩ ግንኙነቶች ውስጥ ሁሉ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተደደርን እንዲመሩ በህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰየሙት አቶ ጌታቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ ተሹመው ለሁለት ዓመታት አገለግለዋል።
በትጥቅ ትግል ውስጥ ያልተሳተፉ እና ወጣት የህወሓት አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ከቀደምት የድርጅቱ መሥራች እና አባላት ያልተናነሰ ተጽእኖ በህወሃት ውስጥ ለመፍጠር ችለዋል። በዚህም የድርጅቱ ምክትል ሊቀ መንበር እስከ መሆን ደርሰዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ድርጅቱ በአቶ ጌታቸው እና በደብረጽዮን (ዶ/ር) በሚመሩ ሁለት ክንፎች ተቧድኖ ውዝግብ ውስጥ የገባ ሲሆን፣ አንደኛው ወገን አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች ከእሳቸው ጋር የወገኑ አመራር እና አባላቱን ከህወሓት ማባረሩን ማሳወቁ ይታወሳል።