ባራክ ኦባማ እና ሚሼል ኦባማ ለወራት የፍቺ አሉባልታዎችን አስተናግደዋል።
የምስሉ መግለጫ,ባራክ ኦባማ እና ሚሼል ኦባማ ለወራት የፍቺ አሉባልታዎችን አስተናግደዋል።

ከ 3 ሰአት በፊት

ሚሽል ኦባማ እና የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ትዳር አደጋ ላይ ሊሆን ይችላል ስለመባሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት የዶናልድ ትራምፕን በዓለ ሲመት እና የጂሚ ካርተርን የቀብር ስነ ስርዓትን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚገኙባቸው ሁነቶች ላይ ባለቤታቸውን አጅበው አለመገኘታቸው ከባራክ ኦባማ ጋር ስለመለያያታቸው አሉባልታዎችን አቀጣጥሏል።

እነዚህን ሁነቶች በግልፅ ሳይጠቅሱ ለአንድ ፖድካስት እንደ “ትልቅ ሴት” ቀጠሯቸውን ለመቆጣጠር አሁን ምቹ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሰዎች ለራሴ “ውሳኔ እየወሰንኩ” እንደሆነ ከማመን ይልቅ “ባለቤቴ እና እኔ ልንፋታ መሆኑን ገምተዋል” በማለት በሕዝባዊ ሁነቶች ላይ አለመገኘታቸው የምርጫ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ከአንዳንድ የስራ ግዴታዎች ወደ ኋላ በማለታቸው የጥፋተኝነት ስሜት እንደተሰማቸውም አልደበቁም።

“እንደ ሴት ሰዎችን ላለማስቀየም የምንጨነቅ ይመስለኛል። ነገሩ ይሄው ነው” ብለዋል።

“በዚህ ዓመት ሰዎች ለራሴ ምርጫ እየመረጥኩ እንደሆነ እንኳ ሊገነዘቡ ባለመቻላቸው እኔ እና ባለቤቴ ወደ ፍቺ እየሄድን እንደሆነ አስበዋል።”

“አንድ ትልቅ ሴት ለራሷ ውሳኔዎችን እየወሰነች አይደለም? ማኅበረሰቡ ይህን ነው እያደረገን ያለው” ሲሉ ማኅበረሰቡ ከሴቶች ከሚጠበቀው እና ከሚያስበው በማፈንገጣቸው የተፈጠረ አሉባልታ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚሼል ኦባማ አክለውም በፖድካስቱ፤ “ማድረግ ያለብኝን ሳይሆን ለእኔ የሚበጀኝን ነው ለማድረግ የመረጥኩት። ሌሎች ሰዎች አንዳደርገው የሚፈልጉትን አይደለም ያደረግኩት” ብለዋል።

በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም በዓለ ሲመት ላይ አለመገኘታቸው ያልተለመደ እና ከአገሪቱ የሥልጣን ርክክብ ባህል ያፈነገጠ ሆኖ ታይቷል።

ሚሼል ኦባማ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራት እጩ ተፎካካሪዋ ካማላ ሀሪስን በመደገፍም በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።

ለራሳቸው ጊዜ እየሰጡ ያሉት የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤቷ ንግግሮችን ማድረግ እና እንደ ሴቶች ትምሕርት ባሉ መርሃ-ግብሮች ላይ መሳተፋቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ጥቅምት ጥንዶቹ 32ተኛ ዓመት የጋብቻ ክብረ በዓላቸውን አክብረዋል።

ሚሼል ኦባማ ከዚህ ቀደም በባለቤታቸው የፖለቲካ ሕይወት እና በዋይት ሀውስ በነበራቸው ቆይታ የትዳራቸውን ውጣ ውረድ በሚመለከት “ቢካሚንግ” በተባለው ግለ ታሪካቸው በስፋት አትተዋል።

የባለቤታቸው ባራክ ኦባማ የፖለቲካ ግብ ብቸኝነት እና ድካም እንዲሰማቸው ማድረጉን በመፅሐፋቸው ገልፀዋል።