ትራምፕ እና ዢፒንግ

11 ሚያዚያ 2025

ቻይና ከአሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የጣለችውን ቀረጥ ወደ 125 በመቶ አሳደገች።

በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል።

ከዚህ ቀደም ብሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉትን የታሪፍ ጭማሪን ተከትሎ ቻይና ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ84 በመቶ ታሪፍ መጣሏን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።

ቤይጂንግ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉትን ታሪፍ ወደ 145 በመቶ ከፍ ካደረጉ በኋላ ነው።

የትራምፕ ታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካ የአክሲዮን (ስቶክ) ገበያ እንዲዋዥቅ ምክንያት ሆኗል።

አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ከፍ በማድረግ እርስ በእርስ የታሪፍ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው አስጊ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የአውሮፓ ኅብረትም ከቻይና ጎን በመቆም የአሜሪካን የምጣኔ ሃብት “ጭቆና” እንዲታገል ጠይቀዋል።

“በታሪፍ ጦርነት ማንም አሸናፊ አይሆንም” ብለዋል።

ትራምፕ ግን ከቤይጂንግ ጋር ድርድር በማድረግ “ለሁለቱም አገራት የሚጠቅም” ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተስፋ ያደርጋሉ።

ይህ የንግድ ጦርነት እየተጋጋለ ሄዶ የምጣኔ ሃብት ድቀት ያስከትላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ትራምፕ ከፍተኛ ታሪፍ በተጣለባቸው አገራት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚነት ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ወስነዋል።

60 የሚደርሱ አገራት ላይ የተጣለው ቀረጥ ተፈጻሚ መሆን በጀመረ በሰዓታት ውስጥ ነው ትራምፕ ያልተጠበቀ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ የከፍተኛው ታሪፍ ተፈጻሚነት እንዲዘገይ ውሳኔ ያሳለፉት።

በዚህ መሠረትም፣ ከአገራቱ ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል እና ሁሉም አገራት የሚከፍሉት ዝቅተኛ የሆነውን 10 በመቶ ቀረጥ እንዲሆን ተደርጓል።

የትራምፕ ታሪፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ትልቅ የሚባል ለውጥ ያመጣ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ወርቅ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ተንታኞች እንደሚሉት ቻይና እና አሜሪካ የገፉበት የታሪፍ ጦርነት በሁለቱም አገራት ንግድ ላይ መዋዠቅ ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከሌሎች ፕሬዝዳንት ትራምፕን ከሚነቅፉ አገራት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።

ከስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ከተወያዩ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት እንዲደግፋቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ ሳምንት ካምቦዲያ፣ ቬትናምና ማሌዢያን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሆንግ ኮንግ የአክሲዮን ገበያ ዛሬ 8.5 በመቶ አሽቆልቁሏል።

የአሜሪካ የንግድ ዘርፍ ተወካይ ጄሚሰን ግሬር በበኩላቸው “አሜሪካ የንግድ ዘርፉ ውስጥ የተለያዩ አማራጮችን ማቅረብ አለባት” ብለው ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ መተማመን “አደገኛ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንኮይስ ባርዩ በበኩላቸው ቻይና አሜሪካን በንግድ አጋርነት ልትተካ እንደምትችልና ይህም “አስፈሪ” እንደሆነ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በአንድነት እንዲቆምም ጠይቀዋል።

የአየርላንድ የገንዘብ ሚኒስትር ፓስካል ዶንሆ “በዓለም ገበያ ለውጥ እያየን ነው” ብለዋል።

ከአውሮፓ ኅብረት የፋይናንስ ሚኒስትር ጋር በፖላንድ መዲና ዋርሶው ከተገናኙ በኋላ የአውሮፓ ኅብረትን እና የዩሮን ዋጋ ለማስጠበቅ በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ቀናት የአሜሪካ ዶላር ዋጋ በገበያው ላይ በሦስት ዓመታት ውስጥ ባልታየ መጠን ቀንሷል። ከሌሎች አገራት መገበያያ ገንዘቦች አንጻር ዶላር ዋጋው ቀንሶ ተገኝቷል።