
ከ 2 ሰአት በፊት
በደቡብ አፍሪካ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየሰበኩ የነበሩ አሜሪካዊ ፓስተር በታጠቀ ቡድን ታፍነው መወሰዳቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ።
ጆሽ ሱሌቫን የተባሉት ፓስተር በኢስት ኬፕ ግዛት በሚገኘው ጋብራ ከተማ ባለው ሐሙስ ዕለት ፌሎሺፕ ባፕቲስት ቸርች ኢን ማዘርዌል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስብከት ላይ ሳሉ ነው ታፍነው የተወሰዱት።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ካፕቴን አንድሬ ቤቴጅ “አራት የታጠቁ እና ጭምብል ያጠለቁ ወንዶች ናቸው ፓስተሩን አፍነው የወሰዷቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ከቤተ ክርስቲያኑ ከመሸሻቸው በፊት ሁለት ስልክ ሰርቀዋል። ከዚያም የ45 ዓመቱን ፓስተር መኪና ተጠቅመው ሸሽተዋል።
ፖሊስ መኪናውን ቢያገኝም ፓስተሩ ግን ወዴት እንደተወሰዱ አላወቀም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ፓስተሩ በደቡብ አፍሪካ በታጣቂዎች ታፍነው እንደተወሰዱ ማወቁን ለቢቢሲ ገልጿል።
መሥሪያ ቤቱ ጨምሮም “የአሜሪካዊውን ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ነው” ብሏል።
የፖሊስ ቃል አቀባዩ እንዳሉት ጉዳዩ ለደቡብ አፍሪካ ልዩ የፖሊስ ኃይል ተሰጥቷል።
ሀውክስ የተባለው የአገሪቱ ልዩ የፖሊስ ክፍል በአደገኛ የወንጀል ቡድኖች እና ከፍተኛ ሙስናን የሚመረምር ነው።
የሀውክስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል አቬሌ ፉምባ “ፖሊስ ግለሰቡን ለማግኘት ሁሉንም አማራጭ እየተመለከተ ነው” ብለዋል።
- በ2025 የአፍሪካ አስር ወታደራዊ ኃያል አገራት፣ ኢትዮጵያ ስንተኛ ላይ ትገኛለች?ከ 3 ሰአት በፊት
- የዓለም ገበያ በተቃወሰበት በአሁኑ ወቅት ገንዘብን በወርቅ ላይ ማዋል የሚያዋጣ አማራጭ ነው?ከ 3 ሰአት በፊት
- የንግድ ጦርነት፡ ቻይና አሜሪካ ላይ የጣለችውን ቀረጥ ወደ 125 በመቶ አሳደገች11 ሚያዚያ 2025
የፓስተሩ ቤተሰብ ቃል አቀባይ ጀርሚ ሆል እንዳለው፣ ፓስተሩ ከባለቤታቸው እና ከልጆቹ ጋር ቤተ ክርስቲያን ነበር።
አፍነው የወሰዷቸው ታጣቂዎች “ስሙን ያውቁት ነበር” ብሏል።
የፓስተሩ እናት ቶንያ ሞርቶን ሪንከር በክስተቱ ልባቸው መሰበሩን በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።
“ምዕመናኑ እና የአሜሪካ ኤምባሲ ሊያገኘው እየሞከረ ነው” ብለዋል።
ከእገታው በኋላ ገንዘብ እንዳልተጠየቀ ኒውስ24 የተባለው መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ፓስተሩ “ቤተ ክርስቲያን የሚያስፋፋ ሚሽነሪ” በማለት በድረ ገጹ ላይ ጽፈዋል።
ወደ ደቡብ አፍሪካ ከቤተሰባቸው ጋር ያቀኑት በአውሮፓውያኑ 2018 ሲሆን፣ በዦሳ ቋንቋ አገልግሎት የሚሰጥ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት ነበር ዓላማቸው።
ባለፉት ዓመታት በደቡብ አፍሪካ እገታ በ264 በመቶ መጨመሩን የፖሊስ መረጃ ያሳያል።
ከቀናት በፊት አንድ ቻይናዊ በጋብራ ከተማ ታግቷል።
