የደምቢ ዶሎ አጋች ማን ነበር? (ክፍል አንድ) (አሁንገና ዓለማየሁ)

April 6, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

የደምቢ ዶሎውን እገታ በተመለከተ ብዙ ነገር እየተባለ ቢሆንም የወንጀሉን ዓላማ በመግለጥ ወንጀለኛው ማን እንደነበር የሚያጋልጥ ጽሑፍ እስካሁን አላየንም። (የማንበብ ትእግስት የሌላችሁ የእገታውን እኩይ ምክንያት ወደሚያትተው ወደ ክፍል ሁለት ንባብ እንድትሄዱ ትጠቆማላችሁ)

የእነዚህን ልጆች እገታ እንደተከታተለ፣ እገታቸውን በአደባባይ ሰልፎች እንዳጋለጠ፣ ተደጋጋሚ ጽሑፍና ግጥሞችን ለመታሰቢያቸው እንደጻፈ አንድ ሰው፣ የእገታው ባለቤት ማን ይመስልሃል? ብለው ወዳጆቼ ለሚጠይቁኝ ጥያቄ ያለኝን ምላሽ ነው የማካፍላችሁ። ለባለሙያዎችና ተመራማሪዎች መነሻ ሃሳብ ይሆናቸዋል በሚል የተጻፈ ነው።

ብርቱካን የተባለችው በኢቢኤስ የቀረበች ወጣት ለጽሑፍ መነሻ ትሁን እንጂ ልጂቷ በደንቢ ዶሎ በመጀመሪያው ዙር ከታገቱት 17 ልጆች ወይም ሁለት አመት ቆይቶ በሁለተኛ ዙር ከታገቱት 10 ልጆች ወይም በሌላ ቦታ ከታገቱት እልፍ ሴቶች መካከል ትሁን አትሁን ሳይሆን ቁም ነገሩ የዚህ የደምቢ ዶሎ እገታ ወንጀል መነሳትን አስታከን ስለ ደምቢ ዶሎ የአማራ ተማሪዎች እገታ እንድንወያይ ምክንያት ስለሆነችን ነው።

የደምቢ ዶሎን እገታ ስንከታተል መረጃዎች ሁሉ ተሰብስበው አቢይ አህመድ ቢሮ እንደተቆለፈባቸው እናውቃለን። ስለ እገታዎቹ ሁነኛ መረጃ ያለውም ንጉሡ ጥላሁን ዘንድ እንደነበረም ይሄንንም መረጃ ለአቢይ እንዳስተላለፈ እናውቃለን። እገታውን ካቀነባብረው ኃይል በተጨማሪ ለማለት ነው።

እገታው ጭካኔ የተሞላበትም ቢሆን ከተለመደና ተራ የዘረፋ ወንጀል ከሆነው የሸኔ የገንዘብ አምጡ እገታ መለየቱን ማንም የሚያስተውለው ነው። ሸኔ የፖለቲካ እገታ አይፈጽምም ለማለት አይደለም።

እገታው ፖለቲካዊ ዐላማ የነበረው ነበር። ሰሞኑን እገታውን ኮሬ ነጌኛ ነው ያካሄደው፣ በፊት ደግሞ ኦነግ ነው፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ የነአቢይ ሸኔ ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የነጃዋር ሸኔ ነው የሚሉ መላ ምቶች ተሰምተዋል። ሸኔ አማራን ከኦሮሞ ክልል የሚያጸዳ ማሽን እንደመሆኑ የአማራ የኮሌጅ ተማሪዎችን ከኦሮሞ ክልል ተነቅለው እንዲወጡ የሽብር ተግባር መፈጸሙ ተጠባቂ ነው። ከደምቢ ዶሎዎቹ ታጋቾች ሌሎች በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተማሪዎች ከየሄዱበት ኮሌጆች ጠፍተው ወደ ቤተሰብ እንዲመለሱ የተደረገበትን የቅድመ ኮቪድ ሽብር ማን ይረሳል? ዛሬ በብርቱካን ምክንያት ጉዳዩ አደባባይ ስለወጣ እንጂ በመቶዎች በሚቆጠሩ የጸበል ቦታዎች የሚንከራተቱት እነዚያን አእላፍ ልጆች ቤት ይቁጠራቸው። እኔ እንኳን የማውቃቸው የቤተሰብ አባላት አሉ፣ እስከዛሬም ጸበል ለጸበል የሚደክሙ።

በዚያን ወቅት ትልቁ የፖለቲካ ዓላማ ምን ነበር? ይህንን ወንጀል ለመፈጸም በእንግሊዝኛ ሞቲቭ፣ ኦፖርቹኒቲ፣ እና ዌፐን (ሚንስ) እንደሚባለው መግደያ ምክንያት (ተነሳሽነት)፣ የመግደል እድልና የመግደያ መሣሪያው የነበረው ማን ነበር ብለን እንመራመር። የአቢይ፣ የሽሜ፣ የጃዋር፣ የጃል መሮ ሸኔዎች ሁሉም ይህን ሁሉ ያሟላሉ። ይሁንና የነአቢይን ሸኔ ከተመለከትን በዚያን ጊዜ እነ አቢይ ገና ለምርጫ ዝግጅት የሚያደርጉበት ዘመን ስለነበረ የመግደያ ምክንያቱን እጅግ ደካማ ያደርገዋል። በወንጀል ምርመራ ኤክስፐርትነት ሳያስፈልገን ነጥቦችን በማገጣጠም የወንጀሉን ፈጻሚ እናገኘዋለን። ወንጀርሉ አማራን አፍኖ ገንዘብ ከሚጠየቅበት የሸኔ የተለመደ የእገታ ወንጀል የተለየ ስለነበረ ብቻም አይደለም።

በዚያን ወቅት የልጆቹ አጋቾች ከቤተሰብ ሲደወል ያቀርቡት የነበረውን ጥያቄ ብንመለከት ጥያቄያቸው የአማራ ክልል ሕዝብ በነቂስ በአቢይ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጣ ይደረግ የሚል ነበር። የቢቢሲና የዘሐበሻን የወቅቱ ዘገባዎች ይመለከቷል። ይህ የወንጀሉን ምክንያት እንድናውቅ ይረዳናል። አቢይ የአማራ ክልል ሕዝብ በተቃውሞ ቢሰለፍበት በኦሮሚያ መጠነኛ የማይባል ድጋፍ እንደሚያገኝ ይታወቃል። ቢሆንም ለዚህ ተጨማሪ ድጋፍ ሲል በአማራ ክልል የነበረውን ከፍተኛ ተቀባይነት ዜሮ በሚያስገባው መልኩ ይሄዳል ተብሎ አይታመንም። ለጃል መሮው ሸኔ ወይም ኦነጦ ደግሞ ይህ የአማራ ክልል ተቃውሞ ለፖለቲካው ይጠቅመዋል ተብሎም አይታሰብም።

ታድያ ለማን ነው የደምቢ ዶሎ እገታ በተፈጸመበት በዚያ ወቃት ‘አቢይ አህመድን እና አማራን ማለያየት’ ትልቅ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የነበረው? ብለን እንጠይቅ።

እስካሁን የመግደያ ምክንያት፣ እድልና መሣሪያ ከነበራቸው ወንጀለኞች የስም ተራ ያልጠቀስነው ሕወሃትን ነው። ሕወሃት እነዚህ የወንጀሉ 3 ዐበይት መመርመሪያ መለኪያዎችን ታሟላ ነበር ወይ? መልሱ አዎ ነው። ሕወሃት በኦሮሞ ክልል፣ በወለጋ በተለይ በደምቢ ዶሎ በሸኔም ውስጥ ሆነ በኮሌጅና በኅብረተሰቡ ሰፊ ኃይል እንዳላት ይታወቃል። በ77 ድርቅ ጊዜ በወለጋ ከሰፈሩ የትግራይ ልጆች እጅግ ብዙ የሕወሃት አባላት ሸኔን መቀላቀላቸው ይታወቃል። በሰላይነት የሚሠሩም በዚያው በኦሮሞ መካከል ተወልደው ያደጉ ሺዎች እንዳሏት ይታወቃል። ከትግሬ ነገድ ውጭም ብዙ የኦሮሞ ተላላኪዎች የነበሯትና ያላት ድርጅት ናት። መሣሪያውም ሆነ እድሉ ነበራት። ከላይ ካሉት ሌሎች ወንጀለኞች ሕወሃትን ለየት የሚያደርጋት ግን የወንጀል ምክንያቱ ነው።

ወቅቱ ምን ነበር?

ሕወሃትና አቢይ አህመድ ለእርስ በእርስ ጦርነት ሰፊ ዝግጅት የሚያደርጉበት ወቅት ነበር። ሕወሃት ደግሞ ከምሥረታዋ የሚታወቅ ባሕርይ አላት። ወደ ፍጥጫ ስትገባ ግዙፉ የቅድመ ዝግጅት አካል አድርጋ የምትጠቀመው ጠላቷን ከሕዝብ የመነጠልን ስትራቴጂ ነው። ሕወሃት ማንንም ከሕዝብ የመነጠል ሥራ አስቀድማ ሳትሰራ ጦርነት ገጥማ አታውቅም። አንድ ግለሰብ እንኳን ቢሆን። የስኬቷ አንዱም ምስጤር ይኸው ነበር (ከአቢይ አህመድ በስተቀር በሕወሃት ረጅምና በስኬት የደመቀ የትግል ጉዞ ድል ያደረጋት አልነበረም። ጀብሃን፣ ትነግን፣ ኢዲዮን፣ ኢሕአፓን፣ ደርግን፣ ሻዕቢያን ደምስሳለች)። ጠላትን ከሕዝብ መነጠል አስቀድማ በትጋት የምትሠራው የቅድመ ጦርነት ዝጅግቷ ግዙፍ አካል ነው። አቢይ አህመድን ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ከነበረው ከአማራ ክልል ሕዝብ የሚነጥለው ዘመቻ ሳታካሂድ ወደ ጦርነት ልትገባ አትችልም።

ለዚህም ነው በእገታው ታሪካዊ ሰዐት ላይ ቆመን ወንጀሉን ለመፈጸም ትልቁ የወንጀል ምክንያት የነበራት ሕወሃት ነበረች ለማለት የምንችለው። እስኪ ደግሞ ወደ መረጃው እንሂድ።

ልጆቹ በተደጋጋሚ ወደ ቤተሰብ የመደወል እድል ባገኙ ጊዜ ይሉ የነበሩት “በክልሉ ጸረ መንግሥት ሰልፍ እንዲወጣ አድርጉልን” ነበር። እርግጥም በአማራ ክልል እስከመንደርና ቀበሌ ድረስ ክልል አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ተወጥቷል። ከጦርነቱ ጥቂት ጊዜያት በፊት። (ሰልፉና ጦርነቱ በዚያው በፈረንጆች 2020 እንደነበር ልብ ይሏል።) ድብልቅልቅ ላለው የተቃውሞ ሰልፍ አንዱና ዋናው መግፍኤም ይኸው እገታ ነበር።

ነገሩ በቡዳ ቤት ሰላቢ ገባ ሆነና አቢይ አህመድም የጦርነት ዝግጅትና ከበባውን ባጠናቀቀ ወቅት የነሱን ስትራቴጂ በላያቸው ገልብጦ ባደራጀው ሸኔ በኩል አማሮችን በወለጋ አርዶና ጨፍጭፎ በሸኔና በሕወሃት በማላከክ በፓርላማ አስለቅሶ ፕሮፓጋንዳውን ቀልብሶ የተሳካ ዘመቻ አከናውኖባቸዋል።

አሁን ጥያቄው መሆን ያለበት አቢይ አህመድ ማስረጃዎቹን ሁሉ ከሰበሰበ በኋላ ለምን ደበቃቸው? የሚለው ነው። ማስረጃው ሕወሃትን የሚጎዳ ከሆነ ለምን አውጥቶ እነሱን ለማጥቂያ አልተጠቀመውም? የሚለው ጥያቄ ማለት ነው። የዚህን ትክክለኛ መልስ ለማግኘት ያስቸግራል። እንደኔ ጊዜው ገና ስለሆነ ይመስለኛል። አንዳንድ ነጥቦችን ስናገጣጥም አቢይ አህመድ በኦሮሚያ የሚደረገውን የአማሮች ጭፍጨፋ (የእስካሁኑን ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት ሊፈጽሙ የተዘጋጁትን ከአሥርና ሃያ ሚልዮን በላይ አማራና ኦርቶዶክስ  የሚጨፈጭፉበትን ማለቴ ነው) በነዚህ በኦሮሚያ ተወላጅ ትግሬዎችና በኦርቶዶክስ ኦሮሞዎች ላይ የማላከክ ትልቅ ዝግጅት ያለው ይመስለኛል። ከምሥጢራዊ የኦህዴድ/ኦነጋውያን ስብሰባ የወጡ የድምጽ ቅጂዎች በኦሮሚያ ተወላጅ ተጋሩ የሸኔ አባላት ላይ የታቀደውን ይፋ ማድረጋቸውን እናስታውስ።  የአብይን ጄኖሳይዳዊ ትልም ይበልጥ ለማብራራት አቢይ የሚከተለው ፍኖተ ካርታ የፖል ካጋሜን ሩዋንዳዊ መንገድ ነው። የጄኖሳይዱ ዋና አስፈጻሚ የባእዳን ተላላኪ የሆነው ካጋሜ ጄኖሳይዱን ካስፈጸመ በኋላ እንደ አቢይ አይነት የእርቅ ምናምንቴ ኮሚሽን አቋቁሞ በወንጀሉ ተጠያቂ ሳይሆን ለሰላሣ አመታት በሥልጣን የዘለቀበትን መንገድ ማለቴ ነው።

አቢይ እነ ሽመልስ አብዲሳ፣ አዳነች አቤቤና ሌሎች መሠረተ ሸዋ ኦርቶዶክስ ኦሮሞዎችን በዚህ በአማራ ጄኖሳይድ ተጠያቂ አድርጎ ለእርድም፣ ለፍርድም ወይም ለኮሚሽናዊ ይቅርታም እነሱን ጭዳ ካደረገ በኋላ ያዘጋጀውን የወሃቢ መስመር ወደፊት በማምጣት ሙሉ ቁጥጥር ለማድረግ እንደተዘጋጀ ከበቂ በላይ ፍንጮች አሉ። ለዚህም ያለ ጊዜው ፈንድተው የነበሩ የነአንጋሳ ኢብራሂምን በሽመልስ ካቢኔ ላይ የተደረጉ ንግግሮች፣ ዛሬ በምክትልነት የቢሮ ኃላፊነት ቦታዎችን የያዙ የነገ ተተኪዎችን ማንነት በመፈተሽና የብልጽግና የክልል ቢሮዎችን ሙሉ በሙሉ እነ ማን እንደተቆጣጠሩ በማየት ሥዕሉን ለማግኘት ይቻላል። በዐቢይ አህመድ ፕሮጄክት ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎቹ እነ አህመዲን ጀበል ሲሆኑ ዴዴብ ተሳታፊዎቹ ደግሞ እነ ለማ መገርሳ፣ እነ ሽመልስ አብዲሳ፣ እነ አዳነች አቤቤ፣ እነ መረራ ጉዲና፣ እነ በቀለ ገርባ፣ እነ አዲሱ አረጋ፣ እነ ታከለ ኡማ ናቸው። እነዚህ የራሳቸውን ማኅበረሰብ ያስከበቡ፣ ያስወረሩ፣ ያስደፈሩ፣ ያስዘረፉ ጅሎች በአቢይ ፍኖተ ካርታ መሠረት ኤክስፓየሪ ዴታቸው ሩቅ አይደለም። ዋና ተፈላጊነታቸው አማራውን በተመለከተ በወንጀል ጓንቲነት እና ቱለማን በተመለከተ ደግሞ ከብቦ ለማድቀቅ ብቻ ነው።

በክፍል ሁለት እንገኛኝ።

በክፍል ሦስት የአጋቹን ማንነት በወንጀሉ ምክንያት መነሻነት መርምረን ጆሮን ጭው የሚያደርገውን እዚህ ያልተጠቀሰ የወንጀል ዓላማ እንገልጣለን።

በቸር ይግጠመን

የደምቢ ዶሎ አጋች ማን ነበር? (ክፍል ሁለት) (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

April 9, 2025

 ነፃ አስተያየቶች

በክፍል አንድ የእገታውን ወንጀል አስመልክተን ወንጀሉን ፈጸሙት ከሚባሉት መካከል (ዐቢይ አህመድ፣ ሸኔ፣ ኦነግ፣ ሕወሃት) ወንጀል ፈጻሚው የትኛው አካል ሊሆን እንደሚችል የወንጀል ምክንያትን በመመርመር ሕወሃት ላይ ጣት ጠቁመናል። ወንጀሉ እንደተፈጸመ አቢይ አህመድ ማስረጃዎቹን ሁሉ ወዲያው ከሰበሰበ በኋላ ለምን ደበቃቸው? ሕወሃትስ ወንጀሉን ከፈጸመችው አቢይ ለምን ሕወሃትን ለማጋለጥ አልተጠቀመበትም? ብለን ጠይቀን ነበር። ክፍል አንድን ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ _____________

በዚህ በደምቢዶሎው እገታ ዘመን ብዙ ወንጀሎች በሸኔ (መግሥታዊም ጫካዊም) መዋቅር ሲፈጸሙ የነበሩ ቢሆንም የሕወሃት የሽብር መዋቅርም  ስዩም መስፍን እና አባይ ጸሐዬ አስቀድመው በቴሌቪዥን ቃል በገቡት መሠረት እጅግ ብዙ የሽብር ጭፍጨፋዎች ያካሄድ እንደነበር ለማወቅ ይቻላል። ለምሳሌ የጂጂጋው የአማሮችና የተዋሕዶ ምእመናን ጭፍጨፋ በሕወሃት ወኪሎች የተቀነባበረና የታገዘ ነበር። በመተከልም ጭፍጨፋ በወቅቱ እንደተጋለጠው ከሸኔ በተጨማሪ የሕወሃት ኃይሎችም እጅ ረጅም ነበር። ሕወሃትና ሸኔ በከሚሴና አጣዬም ይፋዊ ግንባር ፈጥረው አማራን ጨፍጭፈዋል።

በመጨረሻም የቡርቱካን ዶክመንተሪ በኢቢኤስ ያለ አቢይ አህመድ ፈቃድ ወይም እውቅና ተዘጋጅቶ እንደማይተላለፍ እምነቴ ነው። ይህ ከሆነ አቢይ ይህንን ለምን አደረገ? የአቢይን ሥልጣን እያሰጋ የመጣ አዲስ ክስተት ምንድን ነው? እንደኔ ግምት ከጥቂት ወራት ወዲህ አቢይ የሕወሃት፣ ሻዕቢያና አማራ ግንባር ሊፈጠርብኝ ይችላል የሚል ሥጋት እያቃዠው ነው። ጌታቸው ረዳም በአደባባይ እንደመሰከረው ከፋኖና ከኤርትራ ጋር ተባብሮ አቢይን ለማስወገድ የሚፈልግ የሕወሃት ግዙፍ ክፍል አለ።  ስለዚህ አቢይ አህመድ አማራና ሕወሃትን ለማቆራረጥ ቆልፎ ካስቀመጣቸው መረጃዎች ጎምቱ ጎምቱዎቹን ለቁርጥ ቀን ሊጠቀም ይችላል። ከነዚህ ውስጥ የደምቢ ዶሎው እገታ አንዱ ነው። ምናልባት ትክክለኛውን መረጃ በማውጣት 1. የሕወሃቶችን ተሳትፎ ለማሳየት ወይም 2. አስቀድሞ ለነሱው አሳይቶ ለመደራደር ሊጠቀምበት ይችላል። የብርቱካን ዶክመንታሪም መሠራቱ ይቺን ነገር በምልክትነት ብልጭ ሲያደርግላቸው ይሆናል።

ለዚህ ማጠናከሪያ የሚሆነን ይህ የሕወሃትና የፋኖ ትብብር ወሬ መናፈስ በጀመረበት የዛሬ 3 ወር አካባቢ ማንም ሳይጠራው ወንጀሉ ከተረሳ አምስት አመታት በኋላ ብርሃኑ ጂሎ የደምቢ ዶሎ እገታን ወሬ አንስቶ አጋቹ ጃል ጫላ ወይም በሌላ ስሙ አሸናፊ ጎንደሬው ነው ያለበትና ቀሺም ውሸቱ የተጋለጠበት ቪድዮ ነው። የቁጩው ማርሻል “አሸናፊ ጎንደሬው የአብን አባል እና ሸኔ ውስጥ አስርገው ያስገቡት አማራ ነው” ሲል ሲሳይ አጌና እንኳን በቅጥፈቱ ተገርሞ “ጎንደሬ ያስገባሉ ኦነጎች?” ብሎ ሲጠይቀው ምርኮኛው ጄኔራል ተደናግጦ ደምቢ ዶሎ ተወልዶ ያደገ አማራ ነው ቋንቋውን ያውቃል አላለም! አሸናፊ ጎንደሬው እየተባለ እዚያው ተወልዶ ያደገ ሰው ጃል ጫላ ተብሎ እዚያው ደምቢ ዶሎ የሸኔ አባል ሆኖ ሠርጎ ገብ ሆኖ ሲሠራ አይታያችሁም? ማነው ጂሉ? ብርሃኑ ጂሎ ወይስ ሸኔ? ወይስ የደምቢ ዶሎ ሕዝብ?

ቁም ነገሩ ግን ኦህዴዶች ይቺን የደምቢ ዶሎን ወንጀል ማንሳትና ወደ አጀንዳነት ማምጣት የፈለጉበት ወቅት መሆኑ ነው። ለምን? ብለን እንጠይቃለን። በሌላ አተያይ ብርሃኑ ጂሎም እኛ እንደምንገምተው ጂል ሳይሆን ምናልባት “ጃል ጫላ፣ አሸናፊ ጎንደሬው የሚባል፣ አብን በሸኔ ውስጥ አስርጎ ያስገባው” ወዘተ ሲል በአሽሙር ማስተላለፍ የፈለገው “ጃል እግሌ፣ ጎይቶም ትግሬው የሚባል፣ ሕወሃት በሸኔ ውስጥ አስርጎ ያስገባው፣ ኦሮሚያ ውስጥ ተወልዶ ያደገ፣ ቋንቋውን የሚናገር ሰው ነበር” የሚለውን ቢሆንስ? ሕወሃትን እረፊ ለማለት አለዚያም ሳንዱቅ ውስጥ የቆለፉበትን መረጃ ሲለቁ አሃ! እንድንል። ለማንኛውም ወንጀለኞቹ በቀጥታ እነሱ (ኦነጋውያኑ) ከነበሩ የተረሳና የተዘነጋውን የደምቢ ዶሎ እገታ ወንጀል በብርሃኑ ጂሎ መሪነት እንዲህ ባላጦፉት ነበር።

ለኦህዴዶች/ኦነጋውያን ከሥልጣናቸው በላይ ምንም ነገር የለም። ያንን ሥልጣን ለማስጠበቅ ያስፈልጋል ያሉትን እርምጃ ደግሞ ከሁሉም ነገር የበለጠ ትኩረት ይሰጡታል። ስለዚህም የሥልጣን ስጋት የሚባለውን ለማስወገድ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው ይሰራሉ፣ ከማንም ጋር ቢሆን ይተባበራሉ። እነሱ ተባብረው እንደጣሉ፣ ሌሎች ተባብረው እንድሚጥሏቸው ስለሚረዱ የሌሎችን ትብብር ለማክሸፍ/ለማምከን የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። አማራና ትግሬን በሚመለከት ወልቃይት ብቻ አስተማማኝ ሽብልቅ ነው ብለው ተኝተው አያድሩም።  እናም የትብብር ብልጭታ ወሬ ሁሉ ሲያቃዣቸው የሚዳድር ጉዳይ ነው።

ሌላም መላምት አለ። ኦዎ ኢቢኤስ የኤርትራውያን ንብረት ስለሆነ ዐቢይ ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ሲሻክር ኤቢሲዎች ድራማውን ዐቢይን ለመጉዳት የሠሩት ነው የሚል ውሃ የማይቋጥር መላምትም ይደመጣል። ኢቢኤስ ስንት ሠርጎ ገብ የሀገር ማፍረስና የባሕል ሽርሸራ ሥራ የሚሠራበትን ወርቃማና ትርፋማ እድል በሚያስመልጠው መልኩ አንድ የአማራ ታጋች ምስኪን ታሪክ የአማራን ሕዝብ ቀስቅሶ ዐቢይ አህመድን የሚያስወግድ ጦስ ይሆናል ብሎ ተማምኖ ሊቆምር አይችልም። ሊሆን የሚችለው ግን ኢቢኤስን ለመውረስ ወይም ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አቢይ ኢቤኤስ ውስጥ ካሉ የደህንነት አባላት ጋር ተጣምሮ የሠራው ወይም የተሳተፈበት ሥራ ነው። እንዲህ ዓይነት ሐሰተኛ መረጃን ሆን ብሎ በማሰራጨት ቁልፍ ግለሰቦችን ወይም ተቋማትን ከተአማኒነት ውጭ የማድረግ ልምድ አለውና። በቶሎሳ ኢብሳ ላይ ያደረገውን ሴራ ልብ ይሏል። የመቁሰል አደጋ እንደደረሰበት ለነቶሎሳ ሐሰተኛ መረጃ ከሰጠና እነሱም መረጃውን ከለቀቁት በኋላ በዚያው እለት በቲቪ ብቅ ብሎ በመታየቱ ለአመታት የገነቡትን እና ወያኔን አፈር ያስጋጡበትን ተአማኒነታቸውን ዱቄት ያደርገበትን ክሥተት ማለቴ ነው።

ቪድዮውን ከመጀመሪያውም ባለቤት ሆነው አልሰሩትም ቢባል እንኳን እነ አቢይና እነ ተመስገን ጥሩነህ የቪድዮውን መሠራት አስቀድመው እንደሚያውቁ ለሕዝብ ሳይለቀቅ በፊት እንዳዩትም ምንም አልጠራጠርም። ለዚህም አንዱ ማስረጃ ኦህዴዶችና ኦነጋውያን ጭምር ቪድዮውን አስቀድመው ያዩት መሆኑ ነው።  በወቅቱ የነጃዋርን ልጥፎች ብቻ ሳይሆን ሳይጠራ የለፈለፈውን የደምቢ ዶሎ ዮኒቨርሲቲንም ኡኡታ መታዘብ ይቻላል። የኢቢኤሱ የብርቱካን ሙሉ ቪድዮ ደምቢ ዶሎን የሚጠቅስ ክፍል ቢኖርበትም በመጨረሻ ደረጃ ተቆርጦ በኢቢኤስ ለሕዝብ የተለቀቀው ቪድዮ ግን ደምቢ ዶሎ የሚለውን ቆርጦ ያወጣ እትም ነበር። ሕዝቡ ያየውን የተቆረጠ ቪድዮ ብቻ ከተመለከቱና አስቀድመው ሙሉውን ቪድዮ ካላዩ በስተቀር ኦህዴዶችና ኦነጋውያን ቪድዮው ገና እንደተለቀቀ ሳይጠሩ ከተፍ ብለው ደምቢ ዶሎ! ደምቢ ዶሎ! የሚሉበት ምክንያት አይኖራቸውም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ማስተባበያውን የኢቢሲ (ኢቲቪ/ፋና ወዘተ) ቪድዮም ጭምር አስቀድመው እንዳዩት ለማወቅ የነጃዌን ከማስተባበያው በፊት የተለቀቁ ልጥፎች መለስ ብሎ ማየቱ በቂ መረጃ ይሰጣል።

መንግሥት መረጃን በሚያፍንበት፣ ፍትሕን ለማዛባት ሆን ብሎ የተደናገሩ፣ የተጣረሱና የተሳከሩ ወሬዎችን በሚነዛበት፣ ፍትሕ ፈላጊዎችና ተቆርቋሪዎች የሆኑ ሰዎች የሚታወቁትን ነጠብጣቦች ገጣጥመው፣ መላ ምቶችን እየሰነዘሩ፣ ጊዜው ሲፈቅድ እነዚህን በትክክለኛ መረጃ እያጠናከሩ የሆነ ቀን ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ አለባቸው። ተቋሞቹ በወንጀል ሲጠመዱ ዜጎች ደግሞ ወንጀሉን በጋራ ለማጋለጥ፣ ከሥር መሠረቱም ለመድረስ መሞከር ግዴታቸው ነው። ለዚያ የሚያግዝ ይሆናል በሚል ተስፋ የተጻፈ ጽሑፍ ነው።

በክፍል ሦስት እንገናኝ።  የአጋቹን ማንነት በወንጀሉ ምክንያት መነሻነት መርምረን ጆሮን ጭው የሚያደርገውን እዚህ ያልተጠቀሰ የወንጀል ዓላማ እንገልጣለን።

በቸር ይግጠመን።