ፕሬዝንደት ቪክተር ኦርባን
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝንደት ቪክተር ኦርባን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያዎቹን አወድሰዋል

ከ 4 ሰአት በፊት

የሀንጋሪ ፓርላማ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን እና የጥምር ዜጋ ባለቤቶችን መብት የሚገድቡ ሕጎችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች አድርጓል።

መንግሥት ማሻሻያዎቹ የተደረጉት የሕፃናትን አካላዊ እና ሞራላዊ ዕድገት ለመጠበቅ ነው ብሏል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በአደባባይ መሰባሰብ አይችሉም።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፓርላማው ውጭ ተገኝተው ተቃውሞ አሰምተዋል። የመብት ተሟጋች ቡድኖች ውሳኔው ሀንጋሪ “ነፃነት ወደሌለው መንግሥት ማቅናቷን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን ባለፈው መጋቢት ተቺዎቻቸውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “የፋሲካ ሰሞን ፅዳት” እናደርጋለን ብለው ነበር።

የገዢው ፊዴዝ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ 140 የሕዝብ እንደራሴዎች ድጋፋቸውን ሲገልፁ 21 ተቃውሞ ተሰምቷል።

በአዲሱ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ መሠረት የጥምር ዜጋ ባለቤት የሆኑ ሀንጋሪያዊያን ለሀገሪቱ ደኅንነት አደጋ ናቸው ተብሎ ከታሰበ ዜግነታቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ።

ገዢው ፓርቲ እንደሚለው አዲሱ ሕግ ዒላማ ያደረገው “አጠራጣሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ገንዘብ የሚገዛቸው ፖለቲከኞችን እና ራሳቸውን ነፃ ብለው የሚጠሩ ሚድያዎችን” በገንዘብ የሚደግፉ ሰዎችን ነው ብሏል።

አንዳንዶች ሕጉ የወጣው ሃንጋሪያዊ-አሜሪዊው ባለሀብት ጆርጅ ሶሮስን ዒላማ ለማድረግ ነው ይላሉ።

ፕሬዝደንት ቪክተር ኦርባን በተደጋጋሚ ጆርጅ ሶሮስን ሲወቅሱ ይሰማሉ።

ባለፈው ወር ሕፃናት ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ቦታዎች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ሰልፍ ማድረግ እንዳይችሉ የሚያግድ ሕግ መውጣቱ ይታወሳል።

ኦርባን ይህን ሕግ “ዘመናይ ርዕዮተ ዓለም ልጆቻችንን አደጋ ላይ እንዲጥልብን አንፈልግም” በማለት አድናቆት ችረው ነበር።

የተቃዋሚው ሙመንተም ፓርቲ አባል እና የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት ዴቪድ ቤዶ “ይህ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ብቻ ሳይሆን የትኛውንም የተቃውሞ ሰልፍ የሚመለከት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ይህ ገና ጅማሮው ነው። ወደፊት ሌሎች በርካታ ሕጎች በፓርላማው ሲፅድቁ ማየታችን አይቀርም። ይህ ለዲሞክራሲ እና ለየትኛውም የሕግ የበላይነት አደጋ ነው” ሲሉ አክለዋል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ዞልታን ኮቫችስ በኤክስ ገፃቸው በፃፉት መልዕክት የሕግ መንግሥት ማሻሻያዎቹን ተከላክለዋል።

“በተለይ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ሰልፍን በተመለከተ ይህ ሕግ ሕፃናት ከርዕዮተ ዓለማዊ ተፅዕኖ ውጭ እንዲሆኑ ከለላ ይሰጣል” ብለዋል።

የቪክተር ኦርባን ፓርቲ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ሥልጣን ላይ ቆይቷል።

ነገር ግን አዲሱ ማዕከላይ ቀኝ ዘመም የሆነው ቲስዛ ፓርቲ በሀንጋሪያዊን ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ይመስላል።

ፓርቲው የቀድሞው የፊዴዝ ፓርቲ አባል በነበሩት ፒተር ማግያር የተቋቋመ ሲሆን ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር ይሻል።