
ከ 5 ሰአት በፊት
የዶናልድ ትራምፕን ትዕዛዝ አላስተናግድም ያለው ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ከፌደራል መንግሥት የሚመደብለት ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንዲታገድ ተወሰነ።
ዋይት ሀውስ ሀርቫርድ ማድረግ ያለባቸው ነገሮች ዝርዝር ቢሰጥም ዩኒቨርስቲው አልፈቀደም። ዋይት ሀውስ ዝርዝሩን የላከው “ፀረ ሴማዊነትን ለመታገል” ነው ተብሏል።
የትምህርት ሚኒስትር “የሀርቫርድ ውሳኔ በትምህርት ዘርፉ ያለውን ማንአለብኝነት ያሳያል” ብሏል።
ሀርቫርድ የአስተዳደርና ቅጥር ለውጥ እንዲያደርግ ተጠይቋል። ሆኖም ግን ዋይት ሀውስ “ሊቆጣጠረን እየሞከረ ነው” ሲል ውድቅ አድርጓል።
ትራምፕን አሻፈረኝ ያለ ቀዳሚው ትልቅ ዩኒቨርስቲ ነው።
ትራምፕ ዩኒቨርስቲዎች ለአይሁዳውያን ተማሪዎች ከለላ እየሰጡ አይደለም ብለው ሲተቹ ነበር።
በአሜሪካ ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች የጋዛን ጦርነት በሚቃወሙና እስራኤልን በሚደግፉ ተማሪዎች መካከል ግጭት ሲነሳ ነበር።
የሀርቫርድ ፕሬዝዳንት አለን ጋርበር “በሕግ ክፍላችን በኩል መንግሥት ያቀረበውን ማሻሻያ እንደማንቀበል አስታውቀናል። ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን አሳልፈን አንሰጥም” ብለዋል።
ፀረ ሴማዊነትን ዩኒቨርስቲው እንደማይቀበልና መንግሥት ግን ነገሮችን እያጋነነ መሆኑን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
“አብዛኞቹ ትዕዛዞች የመንግሥትን ቁጥጥር የሚያጠብቁ ናቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ዩኒቨርስቲው የሚያገኘው 2.2 ቢሊዮን ዶላር ድጎማና 60 ሚሊዮን ዶላር የኮንትራት ገንዘብ ተቋርጧል።
- በትራምፕ አስተዳደር ምክንያት የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሥራ ለቀቁ29 መጋቢት 2025
- በአይጦች አማካይነት የሚተላለፈው አደገኛው ሃንታቫይረስ ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት በወታደራዊ አቅም በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?ከ 6 ሰአት በፊት
ሀርቫርድ ከፌደራል መንግሥቱ በጀት ለማግኘት እንዲችል ከዋይት ሀውስ ከተሰጡት 10 ማሻሻያዎች መካከል አንደኛው ለአሜሪካ “አደገኛ” የሆኑ ተማሪዎችን መጠቆም ነው።
“ፀረ ሴማዊነትን የሚያባብሱ” የተባሉ የትምህርት ክፍሎችን አሠራር በገለልተኛ ባለሙያዎች ማስፈተሽም ይገኝበታል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቃውሞ ያደረጉ ተማሪዎችን መቅጣትም ተካቷል።
ከወራት በፊት የትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንቶች በኮንግረስ ቀርበው ቃላቸውን ሲሰጡ የያኔው የሀርቫርድ ፕሬዝዳንት ክላውዲን ጋይ አይሁዳውያን ተማሪዎች እንዲገደሉ የሚጠይቁ ንግግሮች መታለፍ አልነበረባቸውም ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል።
ትራምፕ ወደ 256 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የሀርቫርድን ድጎማ እና በየዓመቱ የሚመደበውን 8.7 ቢሊዮን ዶላር በድጋሚ እንደሚያጤኑ መግለጻቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ 400 ሚሊዮን ዶላር የፌደራል ፈንድ መቋረጡ አይዘነጋም።
ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ብዙም ሳይቆይ ዋይት ሀውስ ያቀረባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች ለመተግበር ተስማምቷል።