
ከ 6 ሰአት በፊት
የኦስካር አሸናፊ የሆነው አንጋፋው ተዋናይ ጂን ሃክማን ባለቤት ቤቲ አራካዋ ከሃንታቫይረስ ጋር በተገናኘ የመተንፈሻ አካላት ህመም ሕይወቷ ማለፉን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።
ከዚያም ወዲህ ስለ ሃንታቫይረስ ዓለም ዳግም መነጋገር ጀምሯል።
ሃንታቫይረስ ከአይጦች ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር በሚኖር ንክኪ ምክንያት ጉንፋን መሰል ምልክቶችን እንደሚያስከትል የጤና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
ይህ ምልክት ሲከፋ ደግሞ ለሕይወት አስጊ ለሆነ የሳንባ በሽታ፣ ሃንታቫይረስ ፑልሞናሪ ሲንድሮም (HPS) ሊጋለጥ ይችላሉ።
የሕክምና ባለሙያዎች የታዋቂው ተዋናይ ባለቤት፣ አራካዋ በኤችፒኤስ (HPS) እንደተያዘች ያምናሉ፤ ይህም ለሞቷ መንስኤ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ አይጥ ወለድ ስለሆነው በሽታ ወይንም ሃንታቫይረስ ማወቅ ያለብዎት ነገር ምንድን ነው?
ሃንታቫይረስ ምንድን ነው?
ሃንታቫይረስ በዋነኛነት ወደ ሰዎች የሚተላለፈው ከአይጥ ሽንት፣ ዓይነ ምድር ወይንም ምራቅ መሰል ፈሳሾች የሚነሱ አየር ወለድ ቫይረሶች በመተንፈሻ አካል በኩል ወደ ሰው አካል ሲገቡ ነው።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) እንደገለጸው ቫይረሱ በተለምዶ ከአይጥ ሽንት፣ ዓይነ ምድር ወይም ምራቅ የሚነሳ ሲሆን፣ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሳንባ ሲገባ ኢንፌክሽን ይከሰታል።
ይህ በሽታ አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም በአይጦች ንክሻ ወይም ቡጭሪያ ሊሠራጭም ይችላል።
እንደ ማዮ ክሊኒክ መረጃ በሰሜን አሜሪካ የአጋዘን አይጦች (deer mice) ተብለው የሚታወቁት የተለመዱ የቫይረሱ ተሸካሚዎች ናቸው።
ቫይረሱ ሁለት ከባድ ህመሞችን ሊያስከትል ይችላል።
የመጀመሪያው በአሜሪካ በጣም የተለመደው እና ሃንታቫይረስ የሳንባ ምች ሲንድሮም (Hantavirus Pulmonary Syndrome) ተብሎ የሚታወቀው ነው።
የዚህ ህመም ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ድካም፣ ትኩሳት እና የጡንቻ ህመም ሲሆኑ፣ በመቀጠልም ራስ ምታት፣ ማዞር፣ ብርድ ብርድ ማለት እና የሆድ ህመሞች ይኖሩታል።
በበሽታው የተየዙ ሰዎች ላይ የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ከተከሰተ፣ የመሞት ዕድላችን በግምት 38 በመቶ እንደሆነ ሲዲሲ ይገልጻል።
ሁለተኛው የህመም ምልክት የከፋ እና ኩላሊትን የሚያጠቃው ሲሆን፣ ሄይሞሬጂክ ፊቨር (Haemorrhagic Fever) ከኩላሊት ሥራ መቆም ጋር (Renal syndrome) በአንድነት የሚከሰት ነው።
- ወባን ለመሳሰሉ በፓራሳይት ለሚመጡ በሽታዎች ክትባት ማዘጋጀት ለምን ፈታኝ ሆነ?24 የካቲት 2025
- የሚደክምዎ እና ሰውነትዎ ድንገት የሚዝል ከሆነ ኃይል ለማግኘት የሚረዱ 5 ቀላል መፍትሄዎች22 የካቲት 2025
- በአፋችን ውስጥ የሚገኝ ባክቴሪያ የወደፊት የአእምሮ ጤናችን አመላካች ሊሆን ይችላል?20 የካቲት 2025
በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ያህል የሃንታቫይረስ ሕመሞች ተመዝግበዋል?
ሲዲሲ በአውሮፓውያኑ ከ1993 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ ብቻ 864 የሃንታቫይረስ ህመሞችን መዝግቧል።
አብዛኞቹ ህመሞች እንደ ካሊፎርኒያ፣ ዋሽንግተን፣ አሪዞና፣ ኒው ሜክሲኮ እና ኮሎራዶ ባሉ የአገሪቱ ምዕራባዊ ግዛቶች ገጠራማ አካባቢዎች የተመዘገቡ ናቸው።
ኤጀንሲው በ1993 አሪዞና፣ ኮሎራዶ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ዩታ አካባቢዎች ከባድ የመተንፈሻ አካላት በሽታ በተከሰተበት ወቅት የሃንታቫይረስ በሽታዎችን መከታተል ጀመረ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ወደ 150,000 የሚጠጉ ሄሞሬጂክ ፊቨር፣ ከኩላሊት ሥራ መስተጓጎል (ሬናል ሲንድረም) ጋር ሊኖር እንደሚችል የብሔራዊ ጤና ጥበቃ ተቋማት መረጃ አመልክቷል።
ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚከሰቱት ደግሞ በቻይና ነው።
እንዴት ይከሰታል?
ለሃንታቫይረስ ኢንፌክሽን የተለየ ሕክምና የለም።
ሲዲሲ የበሽታ ምልክቶችን ለማከም ደጋፊ እንክብካቤዎችን ማድረግ ይመክራል።
ከባድ የህመም ምልክት ያለባቸው ሰዎች በሆስፒታሎች የጽኑ ህሙማን ክፍሎች ውስጥ መተኛት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
በጣም ከባድ በሆነ ሁኔታ የታመሙ ግለሰቦች ደግሞ በአፍ እና በአፍንጫቸው ቱቦ ተሰክቶ አስፈላጊው ሕክምና ሊሰጣቸው ይገባል።
ሲዲሲ ለቫይረሱ የሚኖር ተጋላጭነትን ለመቀነስ በቤት ውስጥ ሆነ በሥራ ቦታ ከአይጦች ጋር ያለውን ንክኪ ማስወገድን ይመክራል።
ኤጀንሲው አይጦች ወደ ቤት የሚገቡባቸውን ቀዳዳዎች፣ መሬት ላይም ሆነ በኮርኒስ በኩል ያሉ ክፍተቶችን መድፈን አስፈላጊ መሆኑን ይመክራል።
የአይጥ ዓይነ ምድረም ሆኑ ሌሎች ፈሳሾችን ሲያፀዱ አፍ እና አፍንጫን መሸፈን፣ ጓንት ማድረግ ይመከራል።