ፕሬዝደንት ናይብ ቡኬሌ እና ፕሬዝደንት ትራምፕ

ከ 6 ሰአት በፊት

የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝደንት የአሜሪካ መንግሥት በሰራው ስህተት ምክንያት ሀገራቸው ወደሚገኝ አደገኛ እስር ቤት የተላከውን ግለሰብ እንደማይመልሱ አስታወቁ።

ፕሬዝደንት ናይብ ቡኬሌ ሰኞ በዋይት ሀውስ ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በተገናኙበት ወቅት ነው ይህን የተናገሩት።

ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ የተባለው የኤል ሳልቫዶር ዜጋ ከሚኖርበት አሜሪካ ከሌሎች ወንጀለኞች ጋር ታፍሶ መወሰዱ ይታወሳል።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር “የግለሰቡን መመለስ እንዲያመቻች” ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

አብሬጎ ጋርሲያ ከቤተሰቦቹ ጋር በሜሪላንድ ይኖር የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2019 በስደት ወደ አሜሪካ ከገባ በኋላ ከለላ እንዲደረግለት በፍርድ ቤት ተወስኖለታል።

የትራምፕ አስተዳደር ግለሰቡን መመለስ አልችልም ሲል ይከራከራል።

አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ “ፈቃደኛ ከሆነ መመለስ የሚችለው የኤል ሳልቫዶር መንግሥት ነው” ይላሉ።

አሜሪካ እና የማዕከላዊ አሜሪካዊቷ ሀገር በገቡት ስምምነት መሠረት አሜሪካ የወንበዴ ቡድን አባላት ናቸው ያለቻቸውን ግለሰቦች ኤል ሳልቫዶር ወደ ሚገኝ እስር ቤት መላክ ትችላለች።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የኤል ሳልቫዶሩን ፕሬዝደንት ቡኬሌ ለዚህ ትብብራቸው አመስግነዋል።

የአብሬጎ ጋርሲያ ጠበቃ እንደሚሉት ግለሰለቡ የወንበዴ ቡድን አባል ባይሆን ከ238 ቬኔዙዌላዊያን እና 23 ሳልቫዶራዊያን ጋር ታፍሶ ተወስዷል።

ሴኮት በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው እስር ቤት በርካታ የወንበዴ ቡድን አባላት እና በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች የሚታሰሩበት ጠንካራ ጥበቃ የሚደረግለት እስር ቤት ነው።

ትራምፕ ከቡኬሌ ጋር በነበራቸው የዋይት ሀውስ ጋዜጣዊ መግለጫ አደገኛ የሚባሉ አሜሪካዊያን ወንጀለኞችን ወደ አል ሳልቫዶር የመላክ ሐሳብ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

“ሁሌም ሕግ መከተል ይኖርብናል። ነገር ግን እዚሁ ሀገራችን ሰዎችን ወደ ባቡር ሀዲድ የሚገፉ፣ አሮጊቶችን በዱላ የሚማቱ ሰይጣኖች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

“እኒህ ሰዎች ከዚህ ሀገር ከምናስወጣቸው ጋር ተደባልቀው ቢሄዱ ደስ ባለኝ። ነገር ግን ሕጉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል” ብለዋል የአሜሪካው ፕሬዝደንት።

ኤምኤስ-13 እና ትሬን ዴ አራሁዋ የተባሉት የወንበዴ ቡድን አባላት በአሜሪካ “የውጭ የሽብር ድርጅቶች” ተብለው ተፈርጀዋል።

የትራምፕ አስተዳደር አብዛኛዎቹ ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላኩት ግለሰቦች የእነዚህ ቡድን አባላት ናቸው ይላሉ።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ “የሆነ ግለሰብ እንደሚለስ ትዕዛዝ ከሰጠ እፈፅማለሁ” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የአብሬጎ ጋርሲያ ባለቤት የሆነችው አሜሪካዊቷ ጄኒፈር ቫዝኬዝ ሱራ “የትራምፕ እና የቡኬሌ አስተዳደሮች በሕይወቱ የፖለቲካ ጨዋታ እየተጫወቱ ነው” ስትል ወቅሳለች።

የትራምፕ አስተዳደር ግለሰቡ ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላከው “በአስተዳደራዊ ስህተት” መሆኑን ቢያምንም ጋርሲያን የማምጣት ሥልጣን እንደሌለው ይናገራል።

ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተገነባው ሴኮት የተባለው እስር ቤት 116 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን 40 ሺህ እስረኞችን እንዲያስተናግድ ነው የተሰራው።

እስር ቤቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ለእስረኞች በሚደረግ ጥበቃ ዙሪያ በርካታ ክሶች ይቀርቡበታል።

የእስር ቤቱ ክፍሎች መስኮት አሊያም ነፋስ ማስተላለፊያ የላቸውም። እስረኞች ፍራሽ አሊያም አንሶላ የሌለው የብረት አልጋ ላይ ነው የሚተኙት።

ለ150 እስረኞች ሁለት ሽንት ቤት ብቻ ነው የተነባው። ውሀ በተመጠ መልኩ በሚለቀቅበት እስር ቤት እስረኞች በቀን ለ30 ደቂቃ ብቻ ወጥተው እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላሉ።