
ከ 6 ሰአት በፊት
በዓለም የአገራትን ወታደራዊ አቋም በመመዘን በየዓመቱ ጦር ሠራዊቶችን ደረጃ የሚያወጣው ግሎባል ፋየር ፓወር ኢንዴክስ ተቀባይነት ያለው ዋነኛ የወታደራዊ መረጃ ምንጭ ነው።
ይህ ደረጃ የሚወጣው ከኃያላኑ አገራት አንስቶ እስከ ትንንሽ አገራት ድረስ ያሉትን መረጃዎች ከተለያዩ አስተማማኝ ምንጮች በማሰባሰብ ነው። በዚህ የደረጃ ሠንጠረዥ ውስጥ የሚካተቱት አገራት ወታደራዊ አቅም የሚመዘነው በጦር ኃይል ብዛት እና በታጠቁት የጦር መሳሪያ ብቻ አይደለም።
ይህን ደረጃ ለማውጣት 50 ነጥቦች ያሉት ‘ፓወርኢንዴክስ-ስኮር’ የተሰኘ ዝርዝር መመዘኛዎ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ከእነዚህም መካከል የሕዝብ ብዛት፣ የሠራዊት ቁጥር፣ የጦር መሳሪያ ብዛት እና ዓይነት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የገንዘብ አቅም፣ መልከአምድር እና ሌሎችም ይገመገማሉ።
በዓለም ላይ ኃያል ወታደራዊ አቅም ያላቸው በምጣኔ ሀብት የዳበሩት ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ደቡብ ኮሪያ ከአንድ አስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎቹ ምዕራባውያን እና ሌሎች አገራት በደረጃው ሠንጠረዥ ላይ በተከታይነት ይገኛሉ።
ከአፍሪካ ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ በወታደራዊ ኃይላቸው ቀዳሚዎቹ ሆነው ተመዝግበዋል። እነዚህ አገራት በሕዝብ ብዛት እና በምጣኔ ሀብት በአህጉሪቱ ውስጥ በከፍተኛው ቦታ ላይ የሚገኙ ናቸው።
ግጭት እና ፖለቲካዊ ውጥረት በማይለየው የአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ አምስት ወታደራዊ ኃያላን አገራት መካከል የምትመደብ ሲሆን፣ በምጣኔ ሀብት እና በፖለቲካ በቀጣናው ከፍተኛ ተጽእኖ ያላት አገር ናት።
በዚህ የግሎባል ፋየር ፓወር የአገራት የጦር ኃይሎች ጥንካሬ ሠንጠረዥ ውስጥ የኢትዮጵያ ተጎራባች አገራት የሆኑት ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጂቡቲ ያሉበት ደረጃ ከምን ላይ ይገኛል?
- በ2025 የአፍሪካ አስር ወታደራዊ ኃያል አገራት፣ ኢትዮጵያ ስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?12 ሚያዚያ 2025
- መንግሥት የኮሪደር ልማትን ለጊዜው እንዲገታና ሰዎችን በግዳጅ እንዳያፈናቅል አምነስቲ አሳሰበ14 ሚያዚያ 2025
- ከቁጥር ባሻገር፡ ነዋሪውን ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የሁለት ዓመቱ የአማራ ክልል ግጭት14 ሚያዚያ 2025
ኤርትራ 26ኛ/120ኛ
የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ተዋሳኝ የሆነችው ኤርትራ በዚህ ዓመቱ የግሎባል ፋየር ፓወር ኢንዴክስ ላይ በወታደራዊ አቅም ከ145 አገራት 120ኛ ደረጃ ስትሆን፣ ከአፍሪካ ደግሞ 26ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ከ6.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኤርትራ 120 ሺህ መደበኛ ሠራዊት እና 130 ሺህ ተጠባባቂ ኃይል አላት።
አገሪቱ ለሠራዊቷ 198 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት ትመድባለች። ኤርትራ የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይል አላት።

ሱዳን 9ኛ/73ኛ
ከኢትዮጵያ ጋር በሰሜን ምዕራብ የምትዋሰነው ሱዳን በአሁኑ ወቅት ሁለት ዓመት በሞላው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ በግሎባል ፋየር ፓወር ኢንዴክስ በወታደራዊ ጥንካሬዋ ከዓለም 73ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 9ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አገሪቱ 92 ሺህ መደበኛ ሠራዊት፣ 85 ሺህ ተጠባባቂ ኃይል እና 17 ሺህ ሚሊሻ አላት።
የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይል ያላት ሱዳን ለሠራዊቷ በዓመቱ 342 ሚሊዮን ዶላር በጀት ትመድባለች።

ደቡብ ሱዳን 22ኛ/113ኛ
ከሱዳን ነጻ በመውጣት 15 ዓመት ሊሞላት የተቃረበችው እና በአፍሪካ አዲስ አገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን ጋል ቀዝቀዝ እያለ በቀጠለ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ከኢትዮጵያ ጋር በደቡብ ምዕራብ የምትዋሰን አገርናት።
ደቡብ ሱዳን በወታደራዊ አቅሟ በግሎባል ፋየር ፓወር ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 145 የዓለም አገራት መካከል 113ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ደግሞ 22ኛ ናት።
የሕዝብ ብዛቷ ከ12.7 ሚሊዮን በላይ የሆነችው ደቡብ ሱዳን፣ 185 ሺህ መደበኛ ሠራዊት ሲኖራት ከ175 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት ለምድር ጦር፣ ለአየር እና ለባሕር ኃይሏ በየዓመቱ ትመድባለች።

ኬንያ 11ኛ/83ኛ
ከኢትዮጵያ በስተደቡብ የምትገኘው ኬንያ ጠንካራ የሆነ ምጣኔ ሀብት ካላቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ ስትሆን፣ በዙሪያዋ ካሉ አገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያላት፣ በግዛቷ ውስጥም የታጠቀ አማጺ ኃይል የሌለባት አገር ናት።
የኬንያ ዋነኛው የደኅንነት ስጋት በጎረቤት አገር ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል ሻባብ ነው። በዚህም ምክንያት ሠራዊቷ በዋነኝነት የሚሰማራው ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ ነው።
58 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኬንያ 50 ሺህ መደበኛ ሠራዊት እና 25 ሺህ ሚሊሻ ያላት ሲሆን፣ በግሎባል ፋየር ፓወር ኢንዴክስ ሠንጠረዥ ላይ ከአፍሪካ አገራት መካከል 11ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም በዓለም 83ኛ ላይ ትገኛለች።
የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል ያላት ኬንያ ለሠራዊቷ በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን 307 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በላይ ትመድባለች።

ሶማሊያ 36ኛ/142ኛ
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በመንግሥት አልባነት እና በጦር አበጋዞች መካከል በሚደረግ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ሶማሊያ አሁንም የተረጋጋ እና ጠንካራ መንግሥት የላትም። እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል ሻባብ የሶማሊያን ደካማ መንግሥት እና የሕዝቡን ደኅንነት እየፈተነ ነው።
በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲን እና ኬንያን ጨምሮ ከአፍሪካ አገራት በተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎች የሚጠበቀው የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊቱን ለማጠናከር ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በግሎባል ፋየር ፓወር የደረጃ ሠንጠረዥ ውስጥ ከተካተቱት 145 አገራት መካከል ሶማሊያ ለመቅደም የቻለችው ሦስቱን ብቻ ነው። በዚህም በወታደራዊ አቅሟ ሶማሊያ ከዓለም አገራት 142ኛ ስትሆን ከአፍሪካ ደግሞ 36ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሶማሊያ በእርስ በርስ ጦርነት የተዳከመውን ሠራዊቷን ከ171 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይሏን ለመገንባት እየጣረች ነው።
ከ13 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት 15 ሺህ መደበኛ ሠራዊት አላት።

ጂቡቲ -/-
ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ትንሿ እና በአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ቦታ ላይ የምትገኘው ጂቡቲ በግሎባል ፋየር ፓወር የወታደራዊ ኃይል ምዘና ዝርዝር ውስጥ መረጃዋ አልተካተተም።
ጂቡቲ ወሳኝ የሆነው የባሕር ንግድ እንቅስቃሴ በሚተላለፍበት የኤደን ባሕረ ሰላጤ መግቢያ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በርካታ ኃያላን አገራት ወታደራዊ የጦር ሠፈሮችን በአገሪቱ ውስጥ አቋቁመዋል።
ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በታች ሕዝብ ያላት ጂቡቲ ውስን ቢሆንም የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይል እንዳላት ይታወቃል።
ምንም እንኳን ጂቡቲ በወታደራዊ ኃይል ደረጃው ውስጥ ባትካተትም ካለት የቆዳ ስፋት ትንሽነት እንዲሁም ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር ከሌሎቹ የአፍሪካ ቀንድ አገራት የበለጠ አቅም ይኖራታል ተብሎ አይታሰብም።
ኢትዮጵያ 5ኛ/52ኛ
ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 118 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የግሎባል ፋየር ፓወር ኢንዴክስ መረጃ ያመለክታል።
በምጣኔ ሀብትም ቢሆን ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገራት ትልቋ ናት። ውስጣዊ እና ውጫዊ የደኅንነት ስጋት ያለባት ኢትዮጵያ የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይል ያላት ሲሆን፤ በወታደራዊ አቅሟ በዓለም በ52ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ከአፍሪካ ደግሞ አምስተኛዋ ኃያል አገር ናት።
ከ160 ሺህ በላይ መደበኛ ሠራዊት ያላት ኢትዮጵያ ከ2 ቢሊዮን 97 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ በጀት በመመደብ በዙሪያዋ ካሉት አገራት ሁሉ ከፍተኛውን ገንዘብ ለሠራዊቷ ታውላለች።