አና አሌክሳንድሮቭ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሳለች

ከ 8 ሰአት በፊት

የሴይንት ፒተርስበርግ ነዋሪ የሆነችው የፀጉር ሥራ ባለሙያ ስለ ሩሲያ ጦር የሐሰት መረጃ አሰራጭታለች በሚል ክስ አምስት ዓመት ከሁለት ወር እስር ተፈረደባት።

አና አሌክሳንድሮቭ ስምንት የፀረ ጦርነት መልዕክቶችን በማኅበራዊ የትስስር ገፅ ማጋራቷን የካደች ሲሆን፤ ክሱ ከጎረቤቷ ጋር ባላት የመሬት ውዝግብ ምክንያት የመጣ ነው ብላለች።

አና ለልጇ በዩክሬን ያለውን ጦርነት የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በመላኳ ለዐቃቢ ሕግ ቅሬታ ማቅረባቸውን ጎረቤቷ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፀጉር ሥራ ባለሙያዋ አና የ47 ዓመት የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፤ መጀመሪያ የታሰረችው እ.አ.አ ኅዳር 2023 ነበር።

የእስሯም ምክንያት ቪኮንታክቴ በተባለው የሩሲያ ማኅበራዊ የትስስር ገፅ ስምንት ልጥፎችን በሁለት ሐሰተኛ አካውንቶች በማጋራት ተጠርጥራ ነው።

ጠበቃዋ ባለፈው መስከረም መዝገቡ በመሬት የተነሳ ተራ ግጭት ሆኖ መጀመሩን ተናግረዋል።

“አንደኛው ወገን ወደ ፖሊስ ሄዶ መፍትሄ አላገኘም። በኋላም ‘ጦሩ ላይ ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት’ የሚለው ክስ መጣ” ብለዋል።

ሩሲያ የዩክሬን ወረራ በተጀመረ በሳምታት ውስጥ የጦር ኃይሎችን ማጣጣል እና ሆን ብሎ ስለ ጦሩ የሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ወንጀል እንዲሆን አድርጋለች።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ክሬምሊን በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን እና ተቺዎችን እንዲሁም ገለልተኛ መገናኛ ብዙኸን ባለሙያዎችን በማሰር አፈናውን አጠናክሮ መቀጠሉ ይነገራል።

ማክሰኞ ዕለት በሞስኮ አራት ጋዜጠኞች “ከፅንፈኛ ድርጅቶች” ጋር በመስራት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው አምስት ዓመት ከመንፈቅ እስር ተፈርዶባቸዋል።

ጋዜጠኞቹ ስራቸውን እንደ ጋዜጠኛ መስራታቸውን ቢወተውቱም ፍርድ ቤቱ ግን የፕሬዝዳንት ፑቲን ቀንደኛ ተቀንቃኝ በነበሩት አሌክሲ ኔቫልኒ የፀረ ሙስና ድርጅት ጥቅም ላይ የዋለ ዘገባ ማዘጋጀታቸውን ገልጿል።

ኔቫልኒ ባለፈው ዓመት እስር ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ሩሲያ በተቃዋሚዎች ላይ ያወጣቻቸው ሕጎች ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል እንደ ወጥመድ መያዛቸው ይነሳል።

በአገሪቱ ውግዘት እስር ቤት የሚወረውር ጥፋት ሲሆን፤ ሩሲያዊያን በባልደረቦቻቸው እና በሚያውቋቸው ሰዎች ላይ ለባሥልጣናት መረጃ ይሰጣሉ።

ይህም በሶቪየት ሕብረት ዘመን ልጅ አባቱን በመካድ እርምጃ የወሰደውን ልጅ ያነገሰውን ወቅት የሚያስታውስ ተብሎለታል።