
ከ 8 ሰአት በፊት
ሐማስ እስራኤል ጋዛ ውስጥ ከፈጸመችው ጥቃት በኋላ እስራኤላዊ አሜሪካዊ ታጋች ይዘው ከሚገኙ የቡድኑ አባላት ጋር ያለው “ግንኙነት መቋረጡን” አስታወቀ።
በሐማስ የታገተው የ21 ዓመቱ የእስራኤል ወታደር ኢዳን አሌክሳንደር በቅርቡ ሐማስ በለቀቀው ቪድዮ ላይ ታይቶ ነበር።
እስራኤል አዲስ በረቀቀው የ45 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በመጀመሪያው ቀን እንዲለቀቅ ብትጠይቅም ሐማስ ረቂቁን ውድቅ አድርጎታል።
ሐማስ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ታጋቹን ከያዙ የቡድኑ አባላት ጋር ያለው ግንኙነት ከመቼ ጀምሮ መቋረጡን አላስታወቀም። ታጋቹ ስለመጥፋቱም ማስረጃ አላቀረበም።
እስራኤል በተደጋጋሚ ታጋቾች የሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ጥቃት እንደማታደርስ ትናገራለች።
“በነበሩበት ቦታ ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት ወታደር ኢዳን አሌክሳንደርን የያዙ የቡድናችን አባላት የት እንደሚገኙ ማወቅ አልቻልንም” ሲሉ የሐማስ ቃል አቀባይ አቡ ኦቤይዳ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
“የት እንደሚገኙ ለማወቅ ጥረታችን ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃቱ ፈጽሞ አግቶ ከወሰዳቸው 251 ታጋቾች መካከል 59 የሚሆኑት ያልተመለሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 24 ታጋቾች በሕይወት እንደሚገኙ ይታመናል።
በጋዛ ከሚገኙ ታጋቾች መካከል አምስት የሚሆኑት የአሜሪካ ዜጋ ናቸው። አሌክሳንደር ከአምስቱ መካከል በሕይወት የቀረ ብቸኛው ታጋች እንደሆነ እስራኤል ታምናለች።
- የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት በወታደራዊ አቅም በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?15 ሚያዚያ 2025
- የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትይዩ መንግሥት መመሥረቱን አወጀከ 9 ሰአት በፊት
- በስህተት 45 ዓመታት በዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታል ውስጥ ያሳለፈችው ሴት16 ሚያዚያ 2025
ሐማስ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በለቀቀው የቪድዮ መግለጫ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት ከቀጠለች ታጋቾች በሬሳ ሳጥን ነው የሚመለሱት ሲል ለታጋች ቤተሰቦች መልዕክት አስተላልፏል።
ባለፈው ቅዳሜ ሐማስ ባሠራጨው ቪድዮ አሌክሳንደር በሕይወት እንደሚገኝ ያመለከተ ሲሆን፣ ታጋቹ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መፍትሔ እንዲፈልጉ ተማፅኗል።
እስራኤል በቅርቡ ባረቀቀችው የ45 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት “በመጀመሪያው ሳምንት አሌክሳንደርን ጨምሮ ግማሽ ታጋቾች እንዲለቀቁ” ሐሳብ ማቅረቧን የሐማስ ባለሥልጣን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ እንዳሉት “የሰላም ምልክት” እንዲሆን አሌክሳንደር የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተጀመረ በመጀመሪያው ቀን እንዲለቀቅ ተጠይቋል።
ባለፈው ጥር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት 33 ታጋቾች ሲለቀቁ 1900 ፍልስጤማዊያን እስረኞች ወደ ጋዛ እንዲመለሱ ተደርገዋል። በተጨማሪም እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል።
ነገር ግን የሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ሳይጠናቀቅ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ድጋሚ በወርሃ መጋቢት ጀምራለች።
ቴል አቪቭ ተወልዶ በአሜሪካዋ ኒው ጀርዚ ያደገው አሌክሳንደር በእስራኤል ጦር እያገለገለ ሳለ ነው ከድንበር አካባቢ በሐማስ ታግቶ የተወሰደው።
አባቱ ከአሜሪካው ኒውስኔሽን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ለልጃቸው አለመለቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን ወቅሰዋል።
ሐማስ፤ እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ ሙሉ በሙሉ ነቅላ የምትወጣ ከሆነ እና ጦርነቱንም የምታቆም ከሆነ ሁሉንም ታጋቾች ለመልቀቅ ተስማምቷል።
እስራኤል ባለፈው መጋቢት ድጋሚ በጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት 1630 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ባለፉት 18 ወራት 51 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።