
16 ሚያዚያ 2025, 06:58 EAT
የመማር ችግር ያለባት የኦቲዝም ተጠቂዋ ካሲባ ለ45 ዓመታት በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የአእምሮ ሆስፒታል ውስጥ በስህተት እንድትቆይ መደረጓ መነጋገሪያ ሆኗል።
የሴራሊዮን ተወላጅ መሆኗ የተገለፀው እና ለደኅንነቷ ሲባል በአካባቢው ባለሥልጣናት ካሲባ የሚል ስም የተሰጣት ሴት ለ25 ዓመታት ያህልም ብቻዋን ተለይታ እንድትቆይ ተደርጓል ተብሏል።
ወደ ሕክምና ተቋሙ ከሰባት ዓመቷ ጀምሮ መግባቷ የተገለፀው ካሲባ መናገር የማትችል ሲሆን፣ ስለእሷ የሚናገር ቤተሰብም አልነበራትም።
አንድ የሥነ ልቡና ባለሙያ እሷን ለማስለቀቅ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ እንዴት እንደለፋች ለፋይል ኦን ኢንቨስትጌት ተናግራለች።
የዩኬ ጤና እና ማኅበራዊ ክብካቤ ቢሮ ለቢቢሲ እንደገለጸው ከሆነ ብዙ አካል ጉዳተኞች አሁንም በአእምሮ ሆስፒታሎች እንዲቆዩ መደረጋቸው ተቀባይነት እንደሌለው እና የአእምሮ ጤና ሕግ ላይ የሚደረግ ማሻሻያ ተገቢ ያልሆነ ቆይታን ይከላከላል ብሏል።
ከ2 ሺህ በላይ ኦቲዝም እና የመማር እክል ያለባቸው ሰዎች አሁንም በዩኬ በሚገኙ የአእምሮ ሆስፒታሎች ውስጥ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከል 200 የሚደርሱት ሕጻናት መሆናቸው ተገልጿል።
ምንም ዓይነት የአእምሮ ህመም ስለሌለባቸውም መንግሥት ለዓመታት ብዙዎቹን ወደ ማኅበረሰብ ክብካቤ ማዕከላት ለማዘዋወር ቃል ሲገባ ቆይቷል።
በብሪስቶል አቅራቢያ በሚገኘው እና ዊንተርበርን ቪው በተባለው የግል ሆስፒታል የመማር እክል ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የወንጀል ጥቃት ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ በአውሮፓውያኑ 2011 ይፋ ካደረገ በኋላ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል።
ብሔራዊው የጤና አገለግሎት በ2025-26 የመማር እክል እና ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች በአእምሮ ሕክምና ማዕከላት ላይ ያላቸውን ጥገኝነት 10 በመቶ ለመቀነስ አቅዷል።
በሜንካፕ የበጎ አድራጎት ድርጅት የፖሊሲ እና የሕዝብ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ዳን ስኮር በውሳኔው ደስተኛ አይደሉም።
“በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም በተቋማቱ ውስጥ ናቸው። መውጣት ነበረባቸው። በኅብረተሰቡ ውስጥም ድጋፍ ሊደረግላቸው ቢገባም ቃል የተገባውን አላየንም” ብለዋል።
ዶ/ር ፓትሲ ስቴይት የካሲባን በሆስፒታሉ መቆየት ያወቁት በአውሮፓውያኑ 2013 ጀማሪ ሆነው በተቀጠሩበት ወቅት ነው።
እሷን ነጻ ለማውጣት ዘጠኝ ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።
“እሷ በምትኖርበት ሁኔታ ሌላ ሰው ሲኖር አይቼ አላውቅም። በጣም የሚያስደነግጠው ሁሉም ነገር ሕጋዊ መሆኑ ነው” ሲሉ ዶክተር ስቴይት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሕጋዊ በሚመስለው የሆስፒታል ቆይታዋ ካሲባ “አንዳንድ ጊዜ በቀን ከ23 ሰዓታት በላይ በአንድ ክፍል ተዘግቶባት ትቆይ ነበር” የሚለውን እውነታው እንደሚሸፍን ገልጸዋል።
- የምታጌጥበትን ወርቅ ሸጣ የኦቲዝም ማዕከል የከፈተችው እናት3 የካቲት 2025
- የአእምሮ ዕድገት መዛባት (ኦቲዝም) ያለባቸው መኪና እንዲያሽከረክሩ የሚረዳ ጥናት ለኳታር ያቀረቡት ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ2 ሚያዚያ 2025
- “ከልጄ ጋር ስሆን ደኅንነት አይሰማኝም” ኦቲዝም ያለበት ልጅ እናት2 ሚያዚያ 2025

(የካሲባን ማንነት ለመጠበቅ የሆስፒታሉን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበናል።)
ዶ/ር ስቴይት በሆስፒታሉ አጥር ላይ ያለውን ቀዳዳ እየጠቆሙ፤ ካሲባ ከውጭ የሚሄዱ ሰዎችን ትመለከትበት ነበር ብለዋል።
አሁን በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ካሲባ በአምስት ዓመቷ ከሴራሊዮን በሕገወጥ መንገድ ወደ ዩኬ ተወስዳለች ተብሎ ይታሰባል። ለተወሰነ ጊዜ በልጆች ማዕከል ውስጥ ከኖረች በኋላ ግን በ7 ዓመቷ ወደ ሆስፒታሉ ተዛወረች።
ዶ/ር ስቴይት እንዳሉት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ካሲባን “አደገኛ” እና “ዓይን የምትደነቁል” ሲሉ ገልጸዋታል።
እነዚህን የጥቃት ውንጀላዎች ያስከተለ የሚመስለውን አንድ ክስተት በፋይሏ ውስጥም አገኝተዋል።
ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ካሲባ 19 ዓመቷ እያለ የእሳት አደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል ሲደወል ከነበረችበት ተለቅቃ ነበር።
ካሲባ ተጨንቃ እና ግራ በመጋባት ውስጥ እያለች ሌላ ታካሚም ቀረበች። ታካሚዋን ቧጨረቻት። ዓይኗንን ጎዳቻት።
“ከዚያ በኋላም ‘ዓይን የምትደነቁል እና በሌላ ሰው ላይ ጉዳት የምታደርስ’ በሚል ትጠራለች” ብለዋል ዶክተር ስቴይት።
ነገር ግን “እውነት አይደለም” ይላሉ። በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያለች እና የመማር እክል ያላት ሴት በሆስፒታል ውስጥ ለአስርት ዓመታት ከኖረች ያን ያህል አደገኛ ልትሆን ትችላለች።
ዶ/ር ስቴይት ከወራት ሥራ በኋላ ለካምደን አካባቢ ምክር ቤት ባለ 50 ገጽ ሪፖርት አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ በሰሜን ለንደን የሚገኝ እና ካሲባን ወደ ሆስፒታሉ ያመጣት ነው።
ካሲባ የአእምሮ ህመም እንደሌለባት እና አደገኛ አለመሆኗን የጠቀሰው ሪፖርቱ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመኖርም ብቁ ናት ሲል ደመደመ ብለዋል ዶክተር ስቴይት።
ባለሙያዎች ተሰባስበው “ነጻ አውጪ ኮሚቴ” የሚል የባለሙያዎች ቡድን በአውሮፓውያኑ 2016 አቋቋሙ። ዓላማቸው ካሲባን ነጻ ማውጣት ነበር።
የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ‘ቼንጂንግ አወር ላይቭስ’ የተባለው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሉሲ ዱንስታን፤ የካሲባ ነጻነት ተሟጋች እንዲሆኑ እና ከሆስፒታል ከወጣች ለእሷም ጥሩ እንደሆነ የሚያሳምን ሪፖርት እንዲያዘጋጁ ተመደቡ።
የካሲባን ከሆስፒታል መውጣት የሚወሰነው በፍርድ ቤት ብቻ ሲሆን፣ ይህም የራሳቸውን ውሳኔ ለማሳለፍ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ውሳኔ የሚሰጥ ተቋም ነው።
ዱንስታን ካሲባን ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኙበት ወቅት የሆስፒታሉ ሠራተኞች “ዓይን የምትጓጉጠዋ” ብለው እንዳስተዋወቋቸው ተናግረዋል።
ካሲባን በበሩ ላይ በተዘጋችበት ትንሽ ቀዳዳ መመልከታቸው አስታውሰው ተናግረዋል። “ሶፋ ላይ ተኝታ ነበር። ባዶ ክፍል ነበር። ሕይወቷ ሙሉ በሙሉ ችግር ውስጥ ነበር” ብለዋል።
ዱንስታን ከሆስፒታል መውጣት እንደምትችል ፍርድ ቤት መወሰኑን ለመንገር ደውለው ያዋሯት ካሲባን ካገኙ ስድስት ዓመታት በኋላ ነው።
“አለቀስኩ፣ ደስታ፣ እፎይታ፣ ለእሷ አድናቆት እና ኩራት ተሰማኝ። ስለ እኔ እና እኛ ስላደረግነው ነገር አይደለም። ነገር ግን እሷ አድርጋ ስላሳየቻቸው ነው” ብለዋል።
ካሲባ አሁን ማኅበረሰቡ ጋር መኖር ጀምራለች።
ባለሙያዎች ደጋፍ ያደርጉላታል። ፋሽን እንደምትወድ፣ በቤቷ እንደምትኮራ እና በማኅበራዊ መስተጋብሯ እንደምትደሰት እንክብካቤ የሚያደርጉላት ኃላፊ ተናግረዋል።
“በጣም ጨዋታ አዋቂ ናት። ቆንጆ ናት። ሁለት ሳምንታት ያህል ከቆየች በኋላ መጥታ አቀፈችኝ። ይህ ዓይን ማውጣት አይደለም” ብለዋል።
ፓርላማው እየተመለከተው የሚገኘው የአዕምሮ ጤና ሕግ፤ በእንግሊዝ እና በዌልስ ኦቲዝም እና የመማር እክል ያለባቸው ሰዎች የአእምሮ ጤና ችግር ከሌለባቸው በሕክምና ማዕከል እንዳይቆዩ ያደርጋል።
መንግሥት በኅብረተሰቡ ውስጥ በቂ ድጋፍ እስካልተገኘ ድረስ ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም ብሏል። አሁንም ሰዎች እንዲመረመሩ እስከ 28 ቀናት ድረስ በሆስፒታል እንዲቆዩ ይፈቅዳል።
በካምደን ምክር ቤት የአዋቂዎች እና የጤና ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ጄስ ማክግሪጎር በበኩላቸው ካሲባ አብዛኛውን ሕይወቷን በሆስፒታል ውስጥ ማሳለፏ “አሳዛኝ ነው” ብለዋል።
“አዝናለሁ። በዚህ መልኩ ማሳለፍ አልነበረባትም” ብለዋል።
የሚሰጠው እንክብካቤ በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ እንዳልገባ እና አገልግሎቱ በእንክብካቤ ጥራት ኮሚሽን የላቀ ደረጃ ተሰጥቶታል ሲሉ የካሲባን ማንነት ለመጠበቅ በሚል ስማቸው የማይጠቀስ የብሔራዊ ጤና አገለግሎት የአእምሮ ጤና የበላይ ጠባቂ አስታውቀዋል።
ለረዥም ጊዜ መቆየት እንደሚያስፈልገው የተወሰነ ማንኛውም ሰው መኝታ ቤት፣ መታጠቢያ ቤት፣ ሳሎን እና የአትክልት ስፍራ ያለው የራሱ ቤት እንዳለው ለፋይል ኦን ፎር ኢንቨስትጌት ተናግሯል።
ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ለረዥም ጊዜ የቆዩት ሁሉም እንዲወጡ ለማድረግ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር ዕቅድ በማውጣት ሲሠራ መቆየቱን ቢገልጽም፣ የሌሎች ታማሚ ቤተሰቦች በከፈቱት ክስ ይህን እንዳያደርጉ መከልከላቸውን ተናግሯል።