
ከ 9 ሰአት በፊት
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወታደራዊውን መንግሥት የሚገዳደር ትይዩ መንግሥት መመሥረቱን አስታውቋል።
በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) እና በሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይል መካከል የተከሰተው ግጭት ሁለት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በሱዳን ያለው ሰብዓዊ ቀውስ በዓለም ግዙፉ ነው ተብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሞሐመድ ሀምዳን ‘ሄሜድቲ’ ዳጋሎ እንዳሉት ቡድናቸው “ብቸኛው ለሱዳን የሚበጅ ወደፊትን እየፈጠረ” ያለ ኃይል ነው።
ይህ መግለጫ ይፋ የሆነው የሱዳን ጦርነት ሁለተኛ ዓመትን በማስመልከት በለንደን ከፍተኛ ጉባዔ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።
በዚህ ጉባዔ ላይ የተገኙት የዩናይትድ ኪንግደም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ “የሰላም መንገድ እንዲፈጠር” ጠይቀዋል።
የሱዳን የጦር፤ የፈጥኖ ደራሹ መቀመጫ የሆኑ ከአል-ፋሽር ከተማ ወጣ ብለው የሚገኙ ቦታዎችን በቦምብ ማጥቃቱ ተሰምቷል። ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ዘምዘም የስደተኞች መጠለያን ጥለው እንዲሸሹ አድርጓል።
ሄሜድቲ እንዳሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እየገነባ ያለው “የሕግ የበላይነት” እንጂ በግለሰቦች የሚመራ ሀገር አይደለም።
“እኛ የበላይነት ሳይሆን አንድነት ነው የምንፈልገው። የትኛውም ብሔር፣ ክልል አሊያም ኃይማኖት ከሱዳናዊ ማንነት የበለጠ ቦታ ሊኖረው ይገባል ብለን አናምንም” ይላል በቴሌግራም የለቀቁት መግለጫ።
አክለው መንግሥታቸው በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ሥር ላሉ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ሀገሪቱ ትምህርት እና የጤና አገለግሎትን የመሳሳሉ መሠረታዊያንን እንደሚያሟላ ተናግረዋል።
- የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት በወታደራዊ አቅም በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?15 ሚያዚያ 2025
- በስህተት 45 ዓመታት በዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታል ውስጥ ያሳለፈችው ሴት16 ሚያዚያ 2025
- መንግሥት የኮሪደር ልማትን ለጊዜው እንዲገታና ሰዎችን በግዳጅ እንዳያፈናቅል አምነስቲ አሳሰበ14 ሚያዚያ 2025
አርኤስኤፍ በቅርቡ ባደረሳቸው ጥቃቶች 400 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት “ከታማኝ ምንጮች” መረጃ ማግኘቱን አስታውቋል።
ሁለት ዓመት በሞላው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የሀገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዘር ማጥፋት እና ጅምላ ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ የጦር ወንጀል በማድረስ ይወቀሳሉ።
ሄሜድቲ እና የሱዳን ጦር መሪ ጀኔራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሀን ከአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 15/2023 ጀምሮ ነው በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ያወጁት ጦርነት 150 ሺህ ሰዎችን ሲቀጥፍ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
በቅርቡ በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ አል-ፋሽር በተደረገ ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ከዘምዘም የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተነፋቅለዋል። ዜጎቹ በእግራቸው 70 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ ታዊላ ከተማ ማቅናታቸውን ዓለም አቀፉ የድንበር አልባ ዶክተሮች ማኅበር አስታውቋል።
በርካቶች ታዊላ እስኪደርሱ አንድም ፈሳሽ አለመውሰዳቸው እንዲሁም የተወሰኑ ሕፃናት በውሀ ጥማት ምክንያት መሞታቸው ተዘግቧል።
የሰብዓዊ ተራድዖ ድርጅቶች ምግብና መድኃኒት ማለፍ ባለመቻሉ በአል-ፋሽር አካባቢ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 700 ሺህ ሰዎች ለረሀብ ተጋልጠዋል ይላሉ።
ማክሰኞ በተካሄደው ጉባዔ ዩናይትድ ኪንግደም 120 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ የምግብ እና መድኃኒት እርዳታ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
“በርካቶች በሱዳን ጉዳይ ተስፋ ቆርጠዋል። ይህ ትክክል አይደለም። ሰላማዊ ዜጎች ሲታረዱ፣ ጨቅላዎች ሳይቀሩ ለወሲባዊ ጥቃት ሲጋለጡ፣ እንዲሀም ብዙዎች የረሀብ አደጋ ላይ ሆነው እያየን እንዳላየን መሆን አንችልም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላሚ ተናግረዋል።