የአሜሪካ እና የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማዎች

ከ 6 ሰአት በፊት

አሜሪካ በኤርትራ የሚገኘው ኤምባሲዋን ጨምራ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ጽሕፈት ቤቶቿን ልትዘጋ መሆኑን ሮይተርስ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰነድን ጠቅሶ ዘገበ።

የትራምፕ አስተዳደር አብዛኞቹ በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ ቢያንስ 27 የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችን የሚዘጋ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ኤርትራ አንዷ ናት።

በውሳኔው መሠረት ይዘጋሉ የተባሉት አስሩ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በኤርትራ፣ በግሪናዳ፣ በሌሶቶ፣ በማዕካላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሉክዘንበርግ፣ በሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ በጋምቢያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በማልታ እና በማልዲቭስ የሚገኙ መሆናቸውን ሮይተርስ የተመለከተው ሰነድ ያመለክታል።

ኤርትራ ለረዥም ዓመታት ከአሜሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተቀዛቀዘ ከመሆኑ በተጨማሪ አሥመራ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚመራው በአምባሳደር ሳይሆን በጉዳይ አስፈጻሚ ደረጃ ነው።

ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላ በአውሮፓውያኑ 1993 አሜሪካ ኤምባሲዋን በአሥመራ የከፈተች ሲሆን፣ አሜሪካ በኤርትራ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝን ስትተች ቆይታለች። ይህም የሁለቱ አገራትን ግንኙነት አቀዛቅዞት ቆይቷል።

ለውጭ የእርዳታ ድርጅቶች ዝግ የሆነችው ኤርትራ በአውሮፓውያኑ 2005 የአሜሪካ የእርዳታ ተቋም የሆነውን ዩኤስኤአይዲን ከአገሯ እንዲወጣ ማድረጓ ይታወሳል።

በሁለቱ አገራት መካከል በነበረው የዲፕሎማሲ አለመግባባት ምክንያት የአሜሪካ ኤምባሲ ከአሥመራ ይሰጥ የነበረውን የቪዛ አገልግሎት አቋርጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ሲወርድ በኤርትራ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻልን አሳይቶ ነበር።

ነገር ግን ኤርትራ ሠራዊቷን ወደ ትግራይ በማሰማራት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ሆና በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ በመሳተፏ አሜሪካ ተቃውሞ ከማሰማት አልፋ በኤርትራ ባለሥልጣናት እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

አሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኤርትራ የሚገኘውን ኤምባሲውን ለመዝጋት የያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በርቀት ወይም በሦስተኛ ወገን እንዲሆን ያደርጋል።

በተጨማሪም ከሚዘጉት 17 የአሜሪካ ቆንስላዎች መካከል ከ12 የሚበልጡት በአውሮፓ የሚገኙ ናቸው። ቀሪዎቹ በደቡብ ኮሪያ ቡሳን፣ በደቡብ አፍሪካ ደርባን፣ በኢንዶኔዢያ ሜዳን እና በካሜሩን ዱዋላ የሚገኙ ናቸው።

ከሚዘጉት ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ባሻገር ኤምባሲ እና በርካታ ቆንስላዎችን በመያዝ ግዙፍ የዲፕሎማቲክ ሥራ በሚከናወንባቸው እንዳ ጃፓን እና ካናዳ ያሉትን ተልዕኮዎች በማዋሃድ መጠናቸውን የመቀነስም ሐሳብ አለ።

በተጨማሪም ሰነዱ ከፍተኛ ወጪ በማስወጣት ውድ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ የተመደበባቸው ናቸው ያላቸውን በሞቃዲሾ ሶማሊያ እና በኢራቅ ያሉ የዲፕሎማቲክ አባላትን መጠን የመቀነስ ሐሳብም መቅረቡን አመልክቷል።

ትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት ከተመለሱ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ መስኮች ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር አይጣጣሙም ኣላቸውን ተቋማት በመዝጋት እና እርዳታዎችን በማቋረጥ ላይ ይገኛል።

በዚህም የትራምፕ የቅርብ ሰው በመሆኑት ማርኮ ሩቢዮ የሚመራው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጀት አስከ ግማሽ የሚደርሰው እንደሚቀነስ ሮይተርስ የተመለከተውን የመሥሪያ ቤቱን ሰነድ ጠቅሶ አመልክቷል።

በዚህም ሳቢያ በበርካታ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችን የመዝጋት ሐሳብ እንዳለ ተገልጿል። ይዘጋሉ ከተባሉት የአሜሪካ የዲፕሎማቲክ ተቋማት መካከል አስሩ ኤምባሲዎች ሲሆኑ ቀሩት ቆንስላዎች መሆናቸው ታውቋል።

የአሜሪካ መንግሥት ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ከሚያወጣው ገንዘብ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለመቀነስ አቅዶ የበጀት ጥያቄውን ለአገሪቱ ምክር ቤት ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ እና የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት በተያዘው ዕቅድ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

ሮይተርስ የተመለከተው የበጀት መጠየቂያ ሰነድ እንደሚያሳየው በጀቱ በአሁኑ ወቅት ካለው 54.4 ቢሊዮን ዶላር ወደ 28.4 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። በተጨማሪም ለውጭ እርዳታ በአሜሪካ የዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤአይዲ) በኩል ይቀርብ የነበረው 38.3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 16.9 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር እንዲካተት የተወሰነበት ግዙፉ የዓለማችን የእርዳታ ተቋማ ዩኤስኤአይዲ በዓለም ዙሪያ የነበሩትን ከአምስት ሺህ በላይ ፕሮግራሞቹን በመዝጋት በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን ማሰናበቱ ይታወቃል።