የ40 ዓመቱ ተጠርጣሪ ከመስከረም 2021 እስከ ሐምሌ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ 12 ሴቶችን እና ሦስት ወንዶችን ገድሏል ተብሏል።

ከ 2 ሰአት በፊት

ጀርመን ውስጥ አንድ የጽኑ ህሙማን ዶክተር የተለያዩ መድኃኒቶችን በመጠቀም 15 ታካሚዎቹን በመግደል ወንጀል ተከሰሰ።

የበርሊን ዐቃቤ ሕግ የ40 ዓመቱ የሕክምና ባለሙያ ወንጀሉን ለመደበቅ ሲል የአንዳንድ ተጎጂዎችን ቤት አቃጥሏል ሲል በክሱ ላይ አመልክቷል።

ከአውሮፓውያኑ መስከረም 2021 እስከ ሐምሌ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ምንም እንኳ የሟቾቹ ቁጥር እንደሚጨምር ዐቃቤያነ ሕጎቹ ቢያምኑም፣ 12 ሴቶችን እና ሦስት ወንዶችን መግደሉ ተመልክቷል።

በጀርመን የግለሰቦችን መብት ለመጠበቅ በተደነገገ ሕግ መሠረት የዶክተሩ ስም ይፋ ባይደረግም፣ ተጠርጣሪው ክሱን እንዳልተቀበለ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው ላይ ተናግሯል።

ዶክተሩ ከታካሚዎቹ እውቅና እና ፈቃድ ውጪ ማደንዘዣ እና የጡንቻ ህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ሰጥቷል ተብሏል።

የጡንቻ ህመምን ለማስታገስ የሚሰጠው መድኃኒት “የመተንፈሻ አካላት ጡንቻዎች እንዳይሠሩ በማድረግ በደቂቃዎች ውስጥ መተንፈስ በመከልከል ለሞት ዳርጓቸዋል” ሲል የዐቃቤ ሕግ ቢሮ በመግለጫው ገልጿል።

የሕክምና ባለሙያው በበርካታ የጀርመን ግዛቶች ውስጥ መሥራቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የሞቱት ሰዎች ዕድሜ ከ25 እስከ 94 ነው ተብሏል።

ተጠርጣሪው በአምስት የተለያዩ ጊዜያት ወንጀሉን ለመደበቅ ሲል በሕክምና ጉዳት አድርሶባቸዋል ተብለው የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ቤት አቃጥሏል ተብሏል።

ተጠርጣሪው በሐምሌ ወር 2024 በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ታካሚዎችን መግደሉም ተገልጿል።

ከሞቱት ግለሰቦች መካከል አንዱ በማዕከላዊ በርሊን ነዋሪ የሆኑ የ75 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ ሌላ በበርሊን አቅራቢያ የሚኖሩ የ76 ዓመት አዛውንት ሴት በዚያው ዕለት “ከጥቂት ሰዓታት በኋላ” መገደላቸው ተመዝግቧል።

ዐቃቤ ሕግ ዶክተሩ የአዛውንቷን ቤት ለማቃጠል ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል ብሏል።

“የግድያው ሙከራ አለመሳካቱን ሲመለከት ለአዛውንቷ ዘመድ በአፓርታማዋ ፊት ለፊት ቆሜያለሁ፤ መጥሪያውን ብደውልም ማንም ምላሽ የሰጠ የለም ሲል አሳውቋል” ብሏል።

ዶክተሩ በነሐሴ 2024 በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በእርሱ እንክብካቤ ውስጥ ያሉ አራት ሰዎችን መግደሉ ተጠርጥሯል።

ነገር ግን በምርመራ ወቅት ሌሎች አጠራጣሪ ሞቶች በመገኘታቸው ምርመራ ለማድረግ የሟቾቹን አስከሬን ለማውጣት ቁፋሮ ለማድረግ ታቅዷል።

የ40 ዓመቱ ተጠርጣሪ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከሕክምና ሙያ “የዕድሜ ልክ እገዳ” እንዲሁም “እስር” ይጠብቀዋል ተብሏል።

የሕክምና ባለሙያው አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል።