Mengistu Musie

የምክክር ኮሚሽን ባሕርዳር ምን ያረጋል?

ሰላም አለ የሚል ማሳያ ይሆን?

================

ዛሬ እንዳዲስ እንዳይሆንብን እንጅ ቀደም ብሎ የኢሕአፓ አመራር የምክክር ኮሚሽን የመንግስት አጀንዳ እያራመደ በመሆኑ የለንበትም ብሎ መግለጫ ሲያወጣ እና ሲያውጅ አይን ጨፍነው የተከራከሩ እና ኮናኞች ነበሩ። በውነቱ እኔ እንኳን የማውቃቸው የምቀርባቸው ወዳጆቻችን ሳይቀር ከዘመድ የምንሰማውን እና የቅርብ ቤተሰቦች እያለፉ ያሉበትን የሲኦል ኑሮ ሊረዱኝ ባለመቻላቸው የአንድ ሐገር ሰወች ከተለያየ አለም የመጣን እስኪመስል አንዱ የሌላው ወገኑን ሰቆቃ መረዳት በማይችልበት ሁኔታ ነው ያለነው።

ዛሬ የአማራ ፋኖ መሪወች ይህን ድራማ ኮንነው መግለጫ ማውጣታቸው አግባብ ያለው እና በእርግጥም “በሰው ቁስል እንጨት ቢሰዱበት አያምም” እንዲሉ ከላይ እስከታች መልካም ጫማ እና ያማረበት አልባሳት ያጠለቁ ተላላኪወች በከባድ ወታደራዊ ከበባ የምትጠበቀዋ ባሕርዳር መሄድ እና ሰላም እንዳለ ለማሳየት ሰራን ማለት ከምሁራን የሚጠበቅ አይደለም።

ይህ የምክክር ኮሚሽን ተብየው ባሕርዳር መሄድ የአረመኔውን ተልእኮ መቀበል እና መፈጸም እንጅ 90% የአማራ መሬት አልገዛም ያለ ግን ሰላም ተነፍጎት ሌት ተቀን በድሮን እና በመድፍ የሚደበደብ ሕዝብ ነው።

አንድ የዚህ አይነት ኮሚሽን መጠነ ሰፊ ወንጀል በተሰራበት ሐገር ደግሞም ወንጀሉን ፈጻሚ መንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ እና የዚያን መንግስት ተቀብሎ ከሆነ የሚሰራ እና የሚንቀሳቀስ ይህም ተቋም የወንጀሉ አባሪ እና ተባባሪ እንጅ ነጻ ልሆን አይችልም።

ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ኮሚሽኖች ሁሌም እንደምሳሌ እና ሞዴል የምናየው በዓንገሊካን ቢሾም ዲዝሞንድ ቱቱ የተመራው መጀመሪያ አፓርታይድን የታገለ ሲታሰር ሲፈታ የኖረ ታጋይ አዛውንቶች የተሰባሰቡበት። ስለ ሰበአዊ መብር፤ ስለሰላም፤ ስለአፓርታይድ ዘረኛ አገዛዝ መወገድ ብሎም የክፍለዘመን ወንጀል መልስ እንዲያገኝ በድፍረት የሰራ ኮሚሽን የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ ነጻ ካወጡት የአፍሪካን ኔሽናል ኮንግረስ (ANC) እና ታጋይ ድርጅቶች ጎን ወገናዊ አቋም ይዞ የተከራከረ በደቡብ አፍሪካ ሕዝብ አይን የሞራል የበላይነቱን ያስጠበቀ አካል ነበር።

ጎበዝ መተቸት ቀላል ነው። ምንም እሩቅ ያለን ሰወች እንዲህ አይነት አስተያየት ብንሰጥም ቤተዘመድ የስጋችን ክፋዮች ስቃይ ውስጥ በመኖራቸው የዚያ ስቃያቸው ሰቀቀን በየቀኑ በምንሰማው በቀጥታ በምናገኘው አብሮን ያለ ከተጎጅወቹ በላይ የዓእምሮ እረፍት ያጣን እንዳለን ማእቅ ያስፈልጋል።

ማጠቃለያው የምክክር ኮሚሽን ተብየው አፋኝ ገዳዩን ስርአት አጋዥ ሆኖ መውጣቱ ሕዝብን ያሳዘነ እንጅ ከሕዝብ ጎን ያልቆመ የስርአቱ ቅጣይ ነው።