ኪልማር አብሪጎ ጋርሲያ
የምስሉ መግለጫ,አብሪጎ ጋርሲያ በኤል ሳልቫዶር ወደሚገኘው አደገኛ እስር ቤት የተወሰደው መጋቢት 6 2017 ዓ.ም. ነበር

ከ 2 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት (ዋይት ሐውስ) ባለፈው ወር ከሜሪላንድ ወደ ኤል ሳልቫዶር አደገኛ እስር ቤት በስህተት የተወሰደው ግለሰብ እንደማይመለስ አስታወቀ።

የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት፣ የኤል ሳልቫዶር ዜግነት ያለው ኪልማር አብሪጎ ጋርሲያ የኤም ኤስ-13 ወንበዴ ቡድን አባል ነበር የሚለውን ውንጀላ አጠናክረዋል።

የአብሪጎ ጋርሲያ ጠበቆች ግን የወንበዴ ቡድን አባል ነበር የሚለውን ውንጀላ አስተባብለዋል።

ሌቪት የ 29 ዓመቱ አብሪጎ ጋርሲያ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ዜግነት ካላት ባለቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ እንዳይደርስባት ያወጣችውን የእግድ ትዕዛዝ በመጥቀስ የትዳር አጋሩን የሚደበድብ ነበር ብለዋል።

የኤል ሳልቫዶር ዜጋ የሆነው ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ ከሚኖርበት አሜሪካ ከሌሎች ወንጀለኞች ጋር የተወሰደው ከአራት ሳምንት በፊት ነበር።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር “የግለሰቡን መመለስ እንዲያመቻች” ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በተገናኙበት ወቅት የአሜሪካ መንግሥት በፈጸመው ስህተት ምክንያት አገራቸው ወደሚገኝ አደገኛ እስር ቤት የተላከውን ግለሰብ እንደማይመልሱ አስታወቀዋል።

በዚህም የተነሳ በፕሬዝዳንቱ እና የስደተኞችን ጉዳይ በሚመለከቱ የፍትህ አካላት መካከል ያለው ፍጥጫ እየተባባሰ መጥቷል።

ሌቪት ረቡዕ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “እሱ [አብሪጎ ጋርሲያ] ወደ አሜሪካ የሚመለስ ከሆነ በድጋሚ ወዲያውኑ ይባረራል። አሜሪካ ውስጥ ዳግም ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

የፍርድ ቤት ማስረጃዎችን በመጥቀስም ኤምኤስ-13 የተባለ የወንበዴ ቡድን አባል ነበር ሲሉ ወንጅለውታል።

ይኹን እንጂ ቤተሰቦቹ እና ጠበቆቹ የወንበዴ ቡድን አባል ነበር የሚለውን አስተባብለዋል።

በተጨማሪም የፕሬስ ሴክሬታሪዋ በቤት ውስጥ ጥቃትን ይፈጽም እንደነበር በመጥቀስ “ሴትን የሚማታ” ነበር ብለዋል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደ በአውሮፓውያኑ 2021 በትዳር አጋሩ የቀረበ የእግድ ትእዛዝ ዝርዝር መረጃ ይፋ አድርጓል።

በወቅቱ የትዳር አጋሩ በቡጢ እንደመታት፣እንደቧጨራት እና ሸሚዟን መቅደዱን አመልክታ ነበር።

የአብሬጎ ጋርሲያ ባለቤት ጄኒፈር ቫስኬዝ ሱራ ረቡዕ ለኒውስዊክ በወቅቱ የእግድ ትዕዛዙን የፈለገችው “ለጥንቃቄ” እንደነበር ተናግራለች።

አክላም ችግሩን እንደ ቤተሰብ በመመካከር መፍታት መቻላቸውን ተናግራለች።

የአብሬጎ ጋርሲያ ባለቤት የሆነችው አሜሪካዊቷ ጄኒፈር ቫዝኬዝ ሱራ “የትራምፕ እና የቡኬሌ አስተዳደሮች በእሱ ሕይወት ላይ የፖለቲካ ጨዋታ እየተጫወቱ ነው” ስትል ወቅሳለች።

ቢቢሲ አብሬጎ ጋርሲያ ስለቀረበበት በትዳር አጋሩ ላይ ጥቃት የማድረስ ውንጀላ ጠበቃውን አናግሯል።

ጠበቃው በኢሜይል በሰጡት ምላሽ “አንድ ግለሰብ ሕግን ጥሷል ተብሎ ከተጠረጠረ መንግሥትም ሕግ እንዲጥስ ይፈቀድለታል?” ብለዋል።

ሚስተር አብሪጎ ጋርሲያ በኤል ሳልቫዶር ወደሚገኘው አደገኛ እስር ቤት ከበርካታ ኤል ሳልቫዶራውያን እና ቬንዙዌላውያን ጋር በመጋቢት 6/2017 ዓ.ም. ከመባረሩ በፊት በሜሪላንድ ይኖር ነበር።

በሜሪላንድ ግዛት ዳኛ የሆኑት ፓውላ ዢኒስ፣ አብሪጎ ጋርሲያ ከአገር እንዲባረር መደረጉ በ2019 ፍርድ ቤት እንዳይባረር፣ ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግለት የወሰነውን ውሳኔ የሚጥስ ነው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር አብሪጎ ጋርሲያ እንዲለቀቅ “ማመቻቸት” እንዳለበት በማረጋገጡ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በከፊል አጽንቶት ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት፣ ምንም እንኳ ዋይት ሐውስ የግለሰቡን መባረር ስህተት አይደለም ቢልም “የአስተዳደር ስህተት” መፈጸሙን ገልጸዋል።

ኤምኤስ-13 እና ትሬን ዴ አራሁዋ የተባሉት የወንበዴ ቡድን አባላት በአሜሪካ “የውጭ የሽብር ድርጅቶች” ተብለው ተፈርጀዋል።

የትራምፕ አስተዳደር አብዛኞቹ ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላኩት ግለሰቦች የእነዚህ ቡድን አባላት ናቸው ይላሉ።

ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተገነባው በኤልሳልቫዶር የሚገኘው ሴኮት የተባለው እስር ቤት 116 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 40 ሺህ እስረኞችን ያስተናግዳል።

እስር ቤቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ለእስረኞች በሚደረግ ጥበቃ ዙሪያ በርካታ ክሶች ይቀርቡበታል።