
ከ 4 ሰአት በፊት
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ የአገሪቱ ወታደሮች ሠፊ ስፍራዎችን በመያዝ ባቋቋሙት “የፀጥታ ቀጠናዎች” እንደሚቆዩ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ፣ ቀጠናዎቹ እስራኤላውያንን “ከማንኛውም ጊዜያዊ ወይም ዘላቂ” ጥቃት “ለመከላከል” እንደ ደጀን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።
አክለውም እስራኤል ዳግም በጋዛ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ አጠናክራ ከቀጠለች ከሶስት ሳምንታት ወዲህ፤ በቁጥጥሯ ስር የገባው የፍልስጤም ግዛት “አስር በመቶ” ጨምሯል ሲሉ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሃማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ግፊት ለማድረግ በጋዛ ላይ የተጣለው የሰብዓዊ ርዳታ እገዳ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል ወደ ጋዛ ማንኛውም ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ያስቀመጠችው እገዳ “አስከፊ” መዘዞች እንደሚኖሩት አስጠንቅቋል።
ረቡዕ ዕለት ድንበር የለሽ ሐኪሞች ማኅበር (ኤምኤስኤፍ) የእስራኤል የሰብዓዊ እርዳታ እገዳ ያስከተለውን ተጽእኖ በመግለጽ ጋዛ “የፍልስጤማውያን እና ለእርዳታ የሚመጡ ሰዎች ሁሉ የጅምላ መቃብር ሆናለች” ብሏል።
በጋዛ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ አማንዴ ባዜሮሌ “ጋዛ ውስጥ በጠቅላላው ሕዝብ ላይ የደረሰውን ውድመት እና መፈናቀል በየደቂቃው እያየን ነው” ብለዋል።
በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ጦርነቱ ዳግም ከጀመረበት መጋቢት 18 አንስቶ በጋዛ ከ1,650 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታል ኃላፊዎች ረቡዕ ዕለት እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 24 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ተናግረዋል።
ከሟቾቹ መካከል የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አስር ሰዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው ተብሏል።
ቢቢሲ የእስራኤል ጦር ፈጽሟል ስለተባለው የአየር ጥቃት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
- ሐማስ እስራኤላዊ አሜሪካዊውን ታጋች የያዙ አባላቱ “እንደጠፉበት” አስታወቀ16 ሚያዚያ 2025
- የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምንድን ነው? አሜሪካስ ምን ትፈልጋለች?13 ሚያዚያ 2025
- ጋዛ ‘የግድያ ሜዳ ሆናለች’ ሲሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አሳሰቡ9 ሚያዚያ 2025
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 69 በመቶ የጋዛ ግዛት የእስራኤል ወታደሮች ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጡባቸው መሆናቸውን ተናግሯል።
ወደ 500,000 የሚጠጉ ሰዎች እንደ አዲስ የተፈናቀሉ መሆናቸውን የገለፀው ድርጅቱ፣ የሚሄዱበት ደህነነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በሰሜን እና በደቡብ ወደተለያዩ አካባቢዎች ባደረጋቸው ዘመቻዎች “በመቶዎች የሚቆጠሩ አሸባሪዎችን” መግደሉን አስታውቋል።
ሠራዊቱ ደቡባዊው የራፋህ ከተማን ከአጎራባቿ ካን ዮኒስ የሚለይ አዲስ ወታደራዊ ቀጠና የመሰረተ ሲሆን፣ 30 በመቶውን የጋዛን ክፍል “የደህንነት ቀጠና” ሲል ሰይሟል።
ረቡዕ ዕለት እስራኤል ካትዝ መንግሥታቸው ቀዳሚ ትኩረቱ በሃማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙትን “ሁሉንም ታጋቾች ለማስለቀቅ የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ” መሆኑን ገልጸው፣ “በመቀጠል ደግሞ ሃማስን ለማሸነፍ የሚያስችል መደላድል መፍጠር ነው” ብለዋል ።
አክለውም “ከዚህ በፊት ሲደረግ ከነበረው በተለየ የመከላከያ ሠራዊቱ ባጸዳቸው እና በቁጥጥሩ ስር ካዋላቸው አካባቢዎች እየወጣ አይደለም” ብለዋል።
“የእስራኤል ጦር በጋዛ ውስጥ በጠላት እና በማኅበረሰቦቻችን [እስራኤላውያን] መካከል ለሚከሰቱ ጊዜያዊ ወይንም ዘላቂ ሁኔታዎች እንደ ደጀን ሆኖ ለማገልገል፣በሊባኖስና ሶሪያ እንዳደረግነው፣ በፀጥታ ቀጠና ውስጥ ይቆያል።”
ሃማስ በማንኛውም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ የእስራኤል ጦር ከጋዛ መውጣት እንዳለበት አሳስቧል።
ረቡዕ ዕለት ሮይተርስ የዜና ወኪል ቡድኑ “ጦርነቱን ለማስቆም፣ ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ ለመውጣት፣ የተጣለውን የሰብዓዊ እርዳታ እገዳ ለማንሳት እና መልሶ ግንባታን ለመጀመር እውነተኛ ዋስትና የማይሰጥ ማንኛውም ስምምነት የፖለቲካ ወጥመድ ይሆናል” ማለቱን ዘግቧል።
የበርካታ ታጋቾች ቤተሰቦች የሚወክለው ‘ዘ ሆስቴጅ ኤንድ ሚሲንግ ፋሚሊስ ፎረም ኢን እስራኤል’ የካትዝ እቅድን “ቅዠት” ብሎታል።
“ከሁሉም ነገር በፊት ታጋቾች እንደሚለቀቁ ቃል ገብተው ነበር። በተግባር ግን እስራኤል ከታጋቾቹ ከማስለቀቅ ይልቅ ግዛቶችን ለመያዝ እየመረጠች ነው” ብሏል።
“አንድ ግልጽ እና ተግባራዊ መፍትሄ አለ።ጦርነቱን አቁሞም ቢሆን ታጋቾችን ለማስለቀቅ መስማማት” ሲልም በመግለጫው ላይ ተናግሯል።
በቅርቡ የእስራኤል ተጠባባቂ ኃይሎች እና የቀድሞ ወታደሮች በፈረሙት ግልጽ ደብዳቤ ላይ መንግሥታቸው ሃማስን ከመዋጋት በፊት ታጋቾችን ማስለቀቅ እንዲያስቀድም ጠይቀዋል።
ካትዝ እስራኤል በጋዛ ማንኛውም የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ የጣለችውን እገዳ እንደምትቀጥልበት ግልጽ አድርገዋል።

እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከመጋቢት 2 ጀምሮ ወደ ጋዛ ማንኛውም ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዳይገቡ አግዳለች።
“የእስራኤል ፖሊሲ ግልፅ ነው። ምንም ዓይነት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ አይገባም. . . ” ብለዋል።
የተመድ ተቋማት የእስራኤል መንግሥት በተኩስ አቁም ወቅት 25,000 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ጋዛ በመግባታቸው ምንም ዓይነት የእርዳታ እጥረት የለም ማለቱን ተቃውመዋል።
አክለውም እገዳው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋትን ሊጥስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ አጋሮች ለተፈናቃዮች መጠለያነት የሚያገለግል ድንኳን አለመኖሩን እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየጨመረ መምጣቱን በመግለጽ በመጋቢት ወር ተጨማሪ ምግብ የሚያገኙ ሕጻናት ቁጥር ከሁለት ሶስተኛ በላይ ቀንሷል ብለዋል።
ባለፈው ጥር ወር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት 33 ታጋቾች ሲለቀቁ 1900 ፍልስጤማዊያን እስረኞች ወደ ጋዛ እንዲመለሱ ተደርገዋል።
በተጨማሪም እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል።
ነገር ግን የሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ሳይጠናቀቅ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ድጋሚ በወርሃ መጋቢት ጀምራለች።
እስራኤል ባለፈው መጋቢት ድጋሚ በጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት 1630 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ባለፉት 18 ወራት 51 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።
በጥር 19 በጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ከ1.9 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው ተመልሰው ነበር።
አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን ማክሰኞ ዕለት ለቢቢሲ ሃማስ በሕይወት ካሉት የእስራኤል ታጋቾች መካከል ግማሹን እንዲለቅ እና ትጥቅ እንዲፈታ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ለማድረግ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሃሬትዝ ጋዜጣ እንደተናገሩት እስራኤል እስካሁን ድረስ ከሃማስ ይፋዊ ምላሽ አላገኘችም።