የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም

ከ 5 ሰአት በፊት

ከአሜሪካ ግዛቶች ሁሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅሰው እንዲሁም የግዙፍ ፋብሪካዎች እና እርሻዎች መገኛ የሆነችው የካሊፎርኒያ ግዛት፤ የዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ በመቃወም ክስ መሰረተች።

የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ በመቃወም ክስ መመስረታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በዓለም አቀፍ አገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ በመቃወም ለመጀመርያ ጊዜ በተመሰረተው የግዛቲቱ ክስ፤ ትራምፕ ይህንን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ የተጠቀሙትን ሕግ ተቃውሟል።

ካሊፎርኒያ ከየትኛውም የአሜሪካ ግዛቶች በመቅደም በዓለም አምስተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ግዛት ነች።

በግዛቲቱ ውስጥ ግዙፍ የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች እና ሰፋፊ እርሻዎች ይገኛሉ።

ታሪፉ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የሚስተዋለውን አለመመጣጠን ይፈታል ሲል የሚከራከረው ኋይት ሃውስ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎ “የአሜሪካን ኢንዱስትሪዎችን እየጎዳ ያለውን ብሄራዊ ድንገተኛ አደጋ” መፍትሄ ለመስጠት መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኩሽ ዴሳይ “ጋቪን ኒውሶም በካሊፎርኒያ የተንሰራፋውን ወንጀል፣ የቤት እጦት እና አልቀመስ ያለ ኑሮ ላይ ከማተኮር ይልቅ አገራችንን እየጎዳ ያለውን የንግድ ጉድለት. . . ለመፍታት ፕሬዚደንት ትራምፕን የሚያደርጉትን ታሪካዊ ጥረት ለመግታት ጊዜውን እያጠፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ኒውሶም እና የግዛቲቱ አቃቤ ሕግ ሮብ ቦንታ ክስ መመስረታቸውን ይፋ ያደረጉት በካሊፎርኒያ የአልሞንድ እርሻ መካከል ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

የዓለማችን 82 በመቶ አልመንድን የምታመርተው የካሊፎርኒያ ግዛት፣ አርቲኮክ፣ የወይራ ፍሬ፣ ዋልነት እና የዘቢብ ብቸኛ አምራች ነች።

የካሊፎርኒያ ግዛት አስተደዳሪ የሆኑት ኒውሶም፣ ዶናልድ ትራምፕ በጣሉት ታሪፍ የተነሳ ግዛቲቱ “ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ተጎድታለች” በማለት ተከራክረዋል።

ከጥር ወር ጀምሮ በዶናልድ ትራምፕ ላይ 15 ክሶችን የመሰረተችው የካሊፎርኒያ ግዛት፣ አሁን ደግሞ በአብዛኛዎቹ የዓለም አገራት ላይ 10 በመቶ እና በቻይና ላይ 145 በመቶ የተጣለውን ታሪፍ ተቃውማ ክስ በመመስረት የመጀመርያዋ ሆናለች።

አስተዳዳሪው “ይህ የእኛ መረዳት ነው። ለዚህም ነው በ40 ሚሊዮን አሜሪካውያን ስም በመሆን ራሳችንን ከፊት ያስቀደምነው” ብለዋል።

የካሊፎርኒያ ግዛት የመሰረተችው ክስ ትራምፕ በዓለም አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል የተጠቀሙት ‘ኢንተርናሽናል ኢመርጀንሲ ኢኮኖሚክ ፖወርስ አክት’ የተሰኘ ሕግ፣ ለእንዲህ ዓይነት ታሪፍ ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም፣ ሥልጣኑም የአሜሪካ ኮንግረስ ነው በሚል ይሞግታል።

የክሱ ዝርዝር ላይ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባይደን አስተዳደር የተማሪዎችን ዕዳ ለመሰረዝ የሚያደርገውን እርምጃ ለማገድ የባይደንን ፕሬዝዳንታዊ ሥልጣን ይለጥጣል በሚል ያሳለፈውን ውሳኔ በተደጋጋሚ ጠቅሷል።።

ኒውሶም ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ወጥነት ያለው አሰራር ካለ ይህ ክስ [ለግዛቲቱ] መቋጫ ነው” ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ሕግ በየትኛውም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ታሪፍ ለመጣል ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም።

ካሊፎርኒያ በትራምፕ አስተዳደር የተጣለውን ታሪፍ በመቃወም ክስ የመሰረተች የመጀመሪያዋ ግዛት ሆናለች።

ከዚህ በፊት በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም የሲቪል መብቶች እንዲከበሩ የሚሟገቱ ቡድኖች በተመሳሳይ የትራምፕን እርምጃ በመቃወም ክስ መስርተዋል።

ትራምፕ በጥር ወር ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በዓለም አገራት ላይ የተለያየ ታሪፍ ጥለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ላይ የተጣለው ታሪፍ ሸማቾች የአሜሪካ ምርቶችን እንዲገዙ ያበረታታል፤ የሚሰበሰበውን የታክስ መጠን እንዲጨምር እንዲሁም በአገሪቱ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

ተቺዎቻቸው ግን ፋብሪካዎችን ወደ አሜሪካ ማምጣት ከባድ እና አሥርተ ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል በመጥቀስ፣ እስከዚያው ድረስ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚወድቅ ጠቅሰው ተከራክረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እርምጃ ለመውሰድ ይፋ ካደረጉ በኋላ ውሳኔያቸውን ሲያዘገዩ ታይተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ 60 በሚጠጉ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ከጣሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ ከፖለቲከኞች ከፍተኛ ተቃውሞን ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ከቻይና ውጪ በሌሎቹ አገራት ላይ እርምጃው ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ወስነዋል።