
ከ 3 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፤ የሴቶች እኩልነትን በተመለከቱ ሕጎች ላይ ሴት የሚለው ክፍል የሚመለከተው በተፈጥሯዊ ፆታቸው (biological sex) ሴት የሆኑ ሰዎች ነው ሲሉ በሙሉ ድምጽ ወሰኑ።
ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ረጅም ጊዜ ለፈጀው እና ፆታን መሰረት ያደረጉ መብቶች በስኮትላንድ፣እንግሊዝ እና ዌልስ የሚኖራቸውን አፈጻጸምን በተመለከተ ትልቅ አንድምታ ሊያመጣ የሚችለውን የሕግ ክርክር የቋጨ ነው።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ፤ “ፎር ውሜን ስኮትላድ” የተሰኘው ተሟጋች ቡድን ያቀረበውን መከራከሪያ የሚደግፍ ነው።
ተሟጋች ቡድኑ፤ የስኮትላንድ መንግሥትን በመክሰስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ያመጣው፤ፆታን መሰረት ያደረጉ ከለላዎች መተግበር ያለባቸው በውልደት ሴት ለሆኑ ሰዎች ብቻ እንደሆነ በመከራከር ነው።
ዳኛ ሎርድ ሆጅ፤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አንድ ወገን በሌላኛው ላይ የተቀናጀው ድል ተደርጎ እንዳይወሰድ ያሳሰቡ ሲሆን ሕጉ አሁንም ቢሆን ጾታቸውን በቀየሩ ሰዎች ላይ መድልዎ እንዳይፈጸም ከለላ እንደሚሰጥ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የስኮትላንድ መንግሥት፤ የፆታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያላቸው ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች በተፈጥሮ ሴት ለሆኑ ሴቶች የሚሰጠው ከለላ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በፍርድ ቤት ተከራክሯል።
የፍርድ ቤት ክርክሩ እአአ 2018 የተጀመረው የስኮትላንድ ፓርላማ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የስርዓተ ፆታ ሚዛናዊነትን ለማረጋገጥ ማውጣቱን ተከትሎ ነው።
ፎር ውሜን ስኮትላድ፤ሚኒስትሮች በሕጉ ውስጥ በተቀመጠው ኮታ ውስጥ ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎችን አካትተዋል የሚል ቅሬታ አቅርበዋል።
ጉዳዩ ለበርካታ ጊዜያት በስኮትላድ ፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግበት ነበር።
በ2022 በስኮትላድ የተደረገውን የመጨረሻው ክርክር ላይ የፆታ ትርጓሜ “በተፈጥሯዊ ወይም በውልደት በሚገኝ ፆታ እንደማይገደብ” በመወሰኑ የአገሪቱ መንግሥት አሸንፎ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ አቤቱታ የቀረበለት እአአ በ2010 የወጣውን እና በመላው ብሪታንያ የሚተገበረውን የእኩልነት ሕግ በተመለከተ ተገቢውን የሕግ ትርጓሜ እንዲሰጥ ነበር።
ዳኛው ሆጅ፤ ዋነኛው ጥያቄ “ሴት” እና “ፆታ” የሚሉ ቃላት በሕጉ ላይ እንዴት ተተረጎሙ የሚለው እንደነበር ተናግረዋል።

- የኤርትራው ተቃዋሚ ብርጌድ ንሓመዱ፤ የአዲስ አበባ ቢሮውን ለወታደራዊ “ማዕከላዊ ጽህፈት ቤትነት” የመጠቀም ዕቅድ እንዳለው አስታወቀከ 5 ሰአት በፊት
- ከሁለት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ዳግም ለሁለት የመከፈል አደጋ የተጋረጠባት ሱዳንከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ ወደ ኤል ሳልቫዶር አደገኛ እስር ቤት በስህተት የተላከውን ግለሰብ እንደማትመልስ አስታወቀችከ 3 ሰአት በፊት
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ፤ “የዚህ ፍርድ ቤት የጋራ ውሳኔ፤ በ2010 የእኩልነት ሕግ ላይ የሚገኙት ሴት እና ፆታ የሚሉ ቃላት የሚያመለክቱት ተፈጥሯዊ ሴት እና ተፈጥሯዊ ፆታን ነው” ሲሉ ውሳኔውን አስታውቀዋል።
“ነገር ግን ይህንን ውሳኔ በኅብረተሰባችን ውስጥ የሚገኙ አንድ ወይም ሌሎች ቡድኖች በሌሎች ኪሳራ ላይ የተቀዳጁት ድል ተደርጎ እንዳይወሰድ እንመክራለን” ብለዋል።
ዳኛው አክለውም፤ ሕጉ ፆታቸውን ለቀየሩ ሰዎች “ከለላ የሚሰጠው ፆታ መቀየር ጥበቃ ያለው መገለጫ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ያገኙትን ፆታ መሰረት በማድረግ ከሚፈጸም ማንኛውም ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ መድልዎ እንዲሁም ጥቃት ጭምር ነው” በማለት ተናግረዋል።
የስኮትላንድ መንግሥትን በመክሰስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ያመጡት ተሟጋቾች ከውሳኔው በኋላ ተቃቅፈው ደስታቸውን ሲገልጹ፤ በርካቶቹም ሲያነቡ ታይተዋል።
የእኩልነት ህጉ፤ “ፆታ” እና “ፆታ ቅየራን” ጨምሮ በተለያዩ የሰው ልጆች መገለጫዎች ላይ መድልዎ እንዳይፈጸም ከለላ ይሰጣል።
በለንደን የሚገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በሕጉ ላይ “ፆታ” የሚለውን ቃል በተመለከተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ የተጠየቁት፤ የቃሉ ፍቺ ተፈጥሯዊ ፆታ ወይስ ሕጋዊ ነው የሚለውን እንዲበይኑ ነበር።
“ሕጋዊ” የሚባለው እአአ በ2004 በወጣው የፆታ እውቅና ሕግ መሰረት ፆታው “የምስክር ወረቀት” ያለው ነው።
የስኮትላንድ መንግሥት በ2004 በወጣው ሕግ መሰረት፤ ሰዎች ፆታቸውን ሲቀይሩ የሚያገኙት እውቅና “ለሁሉም ጉዳይ” የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክሯል።
ፎር ውሜን ስኮትላድ የተባለው ተሟጋች ቡድን ደግሞ ወንድ እና ሴት የሚሉት ቃላት መተርጎም ያለባቸው “በመሰረታዊ ግንዛቤ” (common sense) እንደሆነ የሚከራከሩ ሲሆን ፆታ “የማይለወጥ ተፈጥሯዊ ሁኔታ” እንደሆነም ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
የተሟጋች ቡድኑ መስራች ሱዛን ስሚዝ ከውሳኔው በኋላ ከፍርድ ቤቱ ወጥተው ባደረጉት ንግግር “ዛሬ ዳኞች ጉዳዩን በተመለከተ እኛ ሁሌም የምናምንበትን ነገር፤ ሴቶች በተፈሯዊ ፆታቸው ከለላ እንዳላቸው ተናግረዋል” ብለዋል።
“ፆታ እውነታ ነው፤ አሁን ሴቶች ለሴቶች ተብለው በተዘጋጁ እና የሴቶች በሆኑ አገልግሎቶች እና ቦታዎች ላይ ደህንነት ይሰማቸዋል። ለዚህ ውሳኔም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እጅጉን እናመሰግናለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስትር ጆን ስዌኒ፤ የስኮትላንድ መንግሥት ውሳኔውን እንደተቀበለው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸውን በጻፉት መልዕክት አስታውቀዋል።
ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች ግን ውሳኔው ባገኙት ፆታ መድልዎ እንዳይደርስባቸውን የሚያደርገውን ከለላ የሚሸረሽር እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
“ስኮቲሽ ትራንስ” የተባለው ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች መብት ተሟጋች ሥራ አስኪያጅ ቪክ ቫለንቲን፤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ “መደንገጣቸውን” ገልጸዋል።
ውሳኔው “ሕጉ፤ የፆታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ያላቸውን ፆታቸውን የቀየሩ ወንዶች እና ሴቶች በተመለከተ ለ20 ዓመታት የነበረውን ግንዛቤ የሚቀለብስ ነው” ብለዋል።
“ይህ ውሳኔ ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች ከሴቶች እና ወንዶች ቦታ እና አገልግሎቶች ሊገለሉ የሚችሉባቸው ጊዜያት እንደሚኖሩ የሚጠቁም ይመስላል” ሲሉ አክለዋል።