የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና የሱዳን ጦር አዛዥ ጄነራል አብድል ፋታህ አል ቡሩሐን
የምስሉ መግለጫ,የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና የሱዳን ጦር አዛዥ ጄነራል አብድል ፋታህ አል ቡሩሐን

ከ 5 ሰአት በፊት

የሱዳን ጦር ሠራዊት ካርቱምን ተቆጣጥሮ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ለማጠናከር እየጣረ ባለበት ጊዜ ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ትይዩ መንግሥት መመሥረቱን ይፋ አድርጓል።

ይህም ለሁለት ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት የታመሰችው ሱዳን ዳግም ለሁለት በመከፈል ስጋት ውስጥ ትገኛለች።

የአገሪቱ ጦር በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር የነበሩ ማዕከላዊ አካባቢዎችን መልሶ የተቆጣጠረ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ደግሞ በምዕራብ ዳርፉር ያለውን ይዞታ አጠናክሯል።

አርኤስኤፍ መቀመጫውን በዳርፉር አድርጎ ዕውቅና ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። ዕውቅናው የጦር መሳሪያ ገበያ ላይ ለመሳተፍም የሚረዳው ይሆናል።

የአገሪቱ ጦር እና አርኤስኤፍ መሣሪያዎችን ለማግኘት እንደ ኢራን፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኤሚሬትስ እና ሩሲያ ባሉ አገራት ላይ ጥገኛ ናቸው።

በጦርነቱ ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት እየጨመረ በመሆኑ የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ ይደረሳል ተብሎ አይጠበቅም።

ሁለት አገር የመሆን ፍራቻ

በጦርነት የምትታመሰው ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነቱ ሦስተኛ ዓመቱን በጀመረበት በዚህ ወቅት ሁለት አገር የመሆን አደጋ ከፊቷ ተጋርጦባታል።

የፈጣኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) እና አጋሮቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውግዘት ቢደርስባቸውም በተቆጣጠሩት አካባቢ ትይዩ መንግሥት መመሥረታቸውን አውጀዋል።

አርኤስኤፍ እና አጋሮቹ የሰዳን መንግሥት መመሥረቻ ቻርተር የሚል ስምምነት ከሳምንታት በፊት ናይሮቢ ላይ ከተፈራረሙ በኋላ አገሪቱ ለሁለት ትከፈላለች የሚለው ስጋት ጨምሯል።

ትይዩ መንግሥቱ በፖርት ሱዳን የሚገኘውን እና በአገሪቱ ጦር የሚመራውን መንግሥት የሚገዳደር ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት አርኤስኤፍ የጦር መሳሪያ ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ለማሳደግ በሚል ዕውቅናውን ይፈልገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአረብ ሊግ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ሃሳቡን ተቃውመው የሱዳንን አንድነት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

አርኤስኤፍ በማዕከላዊ ሱዳን በሚገኙት በጀዚራ፣ በሴናር እና በካርቱም ተከታታይ ኪሳራ ደርሶበታል።

የአገሪቱ ጦር ማዕከላዊ ሱዳንን መልሶ መያዙ ምሥራቅ እና ምዕራብ በሚል “የሊቢያን የሚመስል” መከፋፈል ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

በሱዳን የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ለቅቀው ወደ ተለያዩ የጎረቤት አገራት ተሰድደዋል
የምስሉ መግለጫ,በሱዳን የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ለቅቀው ወደ ተለያዩ የጎረቤት አገራት ተሰድደዋል

ድጋፍ ለማግኘት የሚደረግ ፉክክር

የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ራሳቸውን ለማጠናከር በርካታ የታጣቂ ቡድኖችን መልምለዋል። በዚህም የተነሳ የታጠቁ ቡድኖች በሁለቱም በኩል በእርስ በርስ ጦርነቱ ተሳትፈዋል።

ሠራዊቱን ከሚደግፉ ቡድኖች መካከል የዳርፉር የታጣቂ ጥምረት የሆኑት የአል ባራ ቢን ማሊክ ብርጌድ ሚሊሻ እና የሱዳን ኃይል ሚሊሻ ይገኙባቸዋል።

በምሥራቅ ሱዳን የተመሠረቱት የምሥራቅ ኦርታ ኃይሎች፣ የምሥራቅ ሱዳን ፓርቲዎች ኃይሎች እና የንቅናቄዎች ኅብረት እንዲሁም የምሥራቅ ሱዳን ብሔራዊ የፍትህ እና ልማት ንቅናቄ በተመሳሳይ የአገሪቱን ጦር ተቀላቅለዋል።

በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ‘ፖፑላር ሬዚስታንስ’ በመባል የሚታወቁት የበጎ ፈቃድ ተዋጊዎችም ጦሩን ሲደግፉ ቆይተዋል።

አርኤስኤፍ በሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተነሳ አጋሮችን ለመሳብ መጀመሪያ ላይ ከብዶት ነበር።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ናይሮቢ ላይ ቻርተሩን በፈረመበት ወቅት ግን ሱዳን ፋውንዲንግ አሊያንስ የተባለ ጥምረትን በመመሥረት ትልቅ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል አስመዝግቧል።

አርኤስኤፍ በመጋቢት ወር በደቡብ ኮርዶፋን ከሚንቀሳቀሰው ከሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ጋር ጥምረት መሥርቻለሁ ብሏል።

በሱዳን ግጭት እጃቸውን ያስገቡ የውጭ ኃይሎች

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦርነቱን ለማስቀጠል በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ወታደራዊ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ሆነዋል።

ጦሩ ከግብፅ፣ ከሩሲያ፣ ከኢራን፣ ከቱርክ እና ከኤርትራ ድጋፍ እንደሚያገኝ በሰፊው ይታመናል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ በቻድ፣ በደቡብ ሱዳን እና በኬንያ እንደሚደገፍ ይነገራል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ካይሮ “ለሱዳን ጦር የጦር መሳሪያ አቅርቦትን ጨምሮ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች።”

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥቅምት 2024 የአርኤስኤፍ መሪ የሆኑት ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ግብፅ እና ኢራን ለጦሩ ወታደራዊ ድጋፍ ያደርጋሉ ሲሉ ከስሰዋል።

ኢራን እና ሩሲያም ለሱዳን ጦር ድጋፍ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፣ ኢራን “የጦር መሳሪያዎች እና የድሮን ቁሶችን” በመላክ ድጋፍ አድርጋለች ተብሏል።

ኢራን ለሱዳን ጦር ድጋፍ ማድረግ የጀመረችው አገራቱ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ተከትሎ ነው።

የሱዳን ጦር ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ከሩሲያ ተቀብሏል ተብሏል።

የሱዳን ባለሥልጣናት ከ2024 ጀምሮ ሩሲያን ሞስኮን ደጋግመው የጎበኙ ሲሆን፣ ባላቸው ግንኙነት እና የወደፊት ትብብር ዙሪያ ተወያይተዋል።

ሩሲያ ለሱዳን ጦር የምታደርገው ድጋፍ በሱዳን በኩል ቀይ ባሕር ላይ የጦር ሰፈር ለመመሥረት የሚያስችላትን ቦታ ለማግኘት ከምታደርገው ጥረት ጋር የተያያዘ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በነሐሴ 2024 የሱዳኑ ሌተናል ጄነራል ያሲር አል አታ፣ የሞስኮን የጦር ሰፈር የመመሥረት ፍላጎት በመደገፍ ጦሩ የሩሲያን ፍላጎት አረጋግጧል።

የካቲት ላይ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ዩሱፍ ሩሲያ የባሕር ኃይል ሰፈር ለማቋቋም ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ሱዳን “ስምምነት መፈራረሟን” ይፋ አድርገዋል።

ምንም እንኳ ቴህራን እና ካርቱም ቢያስተባብሉም፣ ኢራንም በሱዳን በኩል የባሕር ኃይል ሰፈር ለማግኘት ፍላጎት እንዳላት ይነገራል።

የእርስ በርስ ጦርነቱ እንዲቆም ቱርክ ደጋግማ ብትጠይቅም፣ የሱዳን ጦር በቅርቡ በካርቱም ላስመዘገበችው ድል ቱርክ ሠራሽ ቲቢ2 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) ተጠቅሟል።

ኤርትራ ከሱዳን ጦር ጋር የተሰለፉ የታጠቁ ቡድኖችን እንዳሠለጠነች የተዘገበ ሲሆን፣ አሥመራ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጣለች።

አንዳንድ የሱዳን ታጣቂ ቡድኖችም ከኤርትራ የጦር መሳሪያ ስለመቀበላቸው አምነዋል።

የአርኤስፍ ዋነኛዋ ደጋፊ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ናት። የባሕረ ሰላጤዋ አገር ውንጀላውን ብታስተባብልም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደገፉ በርካታ ዘገባዎች ግን ይህንን ያረጋግጣሉ።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የጦር መሳሪያ ትሰጥ እንደነበር እና ይህንንም በቻድ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሊቢያ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በኩል ታከናውን እንደነበር ጠቅሰዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በተለይም በዳርፉር በፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ ሆኗል በማለት የአገሪቱ ጦር የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከስሷታል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ክሱን ውድቅ በማድረግ “ሕጋዊ መሠረት የሌለው” ብላለች።

የሱዳን ጦር ደቡብ ሱዳንን “ለአርኤስኤፍ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮችን አቅርባለች” ያለ ሲሆን፣ የቆሰሉትንም በማከም ትረዳለች ሲል ከስሷል።

ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን እና የሊቢያው ብሔራዊ ጦር (ኤል ኤን ኤ) የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

በዘምዘም የስደተኞች መጠለያ ጣብያ የምትገኝ ሱዳናዊት ተፈናቃይ ልጇን ይዛ
የምስሉ መግለጫ,እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ ከሆነ እስከ መጋቢት ድረስ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል

የሱዳን መገናኛ ብዙኃን ክሶች

በርካታ በሱዳን የሚገኙ የግል መገናኛ ብዙኃን በእርስ በርስ ጦርነቱ ውስጥ ጎራ ለይተው ቢቆሙም አንዳንዶቹ ግን ለመርኅ ተገዥ መሆናቸውን አሳይተዋል።

የሱዳን ጦር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን በመቆጣጠሩ የጦሩን የዕለት ተዕለት አንቅስቃሴ በስፋት በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማ ሆኗል።

አብዛኛዎቹ የውጭ ሚዲያዎች፣ ይፋዊ መግለጫዎችን በእነዚህ መገናኛ ብዙኃን በኩል ስለሚያገኙ በውጭ ያለውን ትርክት ለመቆጣጠር አስችሎታል።

ለሱዳን ጦር የወገኑ መገናኛ ብዙኃን በአጠቃላይ የጦሩን ድሎችን በማጉላት፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ኪሳራ በመዘገብ ተጠምደዋል።

በአንጻሩ የአርኤስኤፍ ደጋፊ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የአማፂ ቡድኑን ድል እያጋነኑ የሠራዊቱን ሽንፈት ያሳያሉ።

የሱዳንን ጦር ከሚደግፉ ታዋቂ የግል መገናኛ ብዙኃን መካከል አል-ሱዳኒ ጋዜጣ፣ ታይባ ቲቪ፣ አል-ሞሃጊግ፣ አል-ኡም፣ ባጅ ኒውስ እና አል-ኢንቲባሃ ይገኙባቸዋል።

አርኤስኤፍን ከሚደግፉት መካከል ደግሞ አል-ሀጌጋ ቲቪ፣ አሳይሃ እና ሴና ኦንላይን ጋዜጦች እና መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ያደረገው የኤሬም ኒውስ ይጠቀሳሉ።

ሆላንድ አምስተርዳም የሚገኘው ራዲዮ ዳባንጋ ከአርኤስኤፍ ጋር ግንኙነት ያላቸው የሲቪል ፓርቲዎችን እንደሚደገፍ ይታመናል።

በፓሪስ የሚገኘው ሱዳን ትሪቡን እና ዳርፉር24 ድረ ገጾች ደግሞ ገለልተኛ እንደሆኑ ይቆጠራል።

“አስከፊው ሰብዓዊ ቀውስ”

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የከፋውን ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል ብሏል።

አንዳንድ የሱዳን ክፍሎች ለረሃብ እየተጋለጡ ነው ሲልም አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ሠራዊቱን እና አርኤስኤፍ እርዳታን በማደናቀፍ ከስሷቸዋል።

እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ዘገባ ከሆነ እስከ መጋቢት ድረስ ሱዳን ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለውባታል።

ይህ አሃዝ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እና በኋላ የተፈናቀሉትን ያጠቃልላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግብፅን ጨምሮ 3.8 ሚሊዮን ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል ብሏል።

እነዚህ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ቻድ፣ ሊቢያ እንዲሁም ሱዳንን ወደ ማትዋሰነው ኡጋንዳ ተሰድደዋል።

ግብፅ 1.5 ሚሊዮን ሱዳናውያን ስደተኞችን፣ ደቡብ ሱዳን አንድ ሚሊዮን፣ ቻድ ከ767 ሺህ በላይ፣ ሊቢያ ከ240 ሺህ በላይ፣ ኢትዮጵያ ከ71 ሺህ በላይ፣ ኡጋንዳ ከ70 ሺህ በላይ እና መካከለኛው አፍሪካ ከ41 ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገዱ ነው።

ከሱዳን ሕዝብ ግማሽ ያህሉ፣ ማለትም ቢያንስ 24.6 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ረሃብ ላይ ክትትል የሚያደርገው ‘ዘ ፋሚን ሪቪው ኮሚቲ’ (ኤፍአርሲ)፣ ነሐሴ 2024 ላይ እንደገለጸው ከሆነ “ረሃብ በሰሜን ዳርፉር በሚገኙ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተስፋፍቷል።”

በሱዳን ጦር የሚመራው መንግሥት የረሃብ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ አስተባብሏል።

ጠመንጃ ላይ የተንጠለጠለ የሱዳን ባንዲራ

የጨለመው ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ተስፋ

በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ሸምጋዮች በኩል በርካታ ውይይቶች ቢካሄዱም የሱዳን ጦር፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ከሁሉም የከተማ አካባቢዎች ለቅቀው እንዲወጡ እና ትጥቅ እንዲፈቱ በመጠየቁ ከስምምነት ሊደረስ አልቻለም።

አርኤስኤፍ በበኩሉ የጦሩን ቅድመ ሁኔታዎች የሰላም ጥረቶች ለማደናቀፍ የታለሙ “እንቅፋቶች” ሲል ተቃውሟቸዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በነሐሴ 2024 በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አደራዳሪነት ጄኔቫ ላይ የተሞከረው ሽምግልና ጦሩ ባለመገኘቱ ምክንያት ከከሸፈ በኋላ ውይይቱ ቆሟል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት የሱዳን ጦር እና ደጋፊዎቻቸው እያገኙት ካለው ድል አንጻር ድርድሩ በቅርቡ እንደገና ይቀጥላል ተብሎ አይታሰብም።

ከጄኔቫው ድርድር መክሸፍ በኋላም ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን አጠናክረው በመቀጠላቸው የሰላም ድርድሩ ተስፋ አመንምኖታል።

አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ከተፋላሚ ወገኖች ጋር በተገናኙ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል። ማዕቀቡ ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን እና ሄሜቲን የጨመረ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር በሱዳን ላይ ያለው ፍላጎት አነስተኛ ሲሆን፣ አንዱን ወገን መደገፍ እንደማይፈለግ እና ጦርነቱን ለማስቆም ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ መሆኑ ተነግሯል።

የትራምፕ አስተዳደር በዓለም አቀፍ የታሪፍ ጦርነት እና በሌሎች ቀውሶች ላይ ትኩረት በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅት፣ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች እንደ አፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ባሉ ክልላዊ ተቋማት ተጽዕኖ ሊደረግባቸው እንደማይችል ግልጽ ሆኗል።