
ከ 5 ሰአት በፊት
የኤርትራው የተቃውሞ እንቅስቃሴ “ብርጌድ ንሓመዱ” በአዲስ አበባ ከተማ የከፈተው ቢሮ፤ “በቀጣይ ወታደራዊ ማዕከሎች ሲቋቋሙ፤ማዕከላዊ ፅህፈት ቤት” ሆኖ እንደሚያገለግል ገለጸ።
የተቃውሞ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ “ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ማዕከሎች” ሊኖሩት እንደሚችልም አስታውቋል።
ብርጌድ ንሓመዱን የሚቀላቀሉ ኤርትራውያን “ዋስትና ስለሚያገኙበት መንገድ” ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር “መነጋገሩን” የእንቅስቃሴው አመራር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት ከሥልጣን ለማውረድ የሚንቀሳቀሰው “ብርጌድ ንሓመዱ”፤ በአዲስ አበባ ከተማ “22” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ ህንጻ ላይ የከፈተውን ጽህፈት ቤት ሥራ ያስጀመረው ባለፈው የካቲት አጋማሽ ነበር።
የጽህፈት ቤቱን የምርቃት ሥነ ሥርዓት በሚያሳይ ቪድዮ ላይ፤ የብርጌድ ንሓመዱ አመራሮች የቢሮው መከፈት ለእንቅስቃሴው “እጥፋት” እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
እንቅስቃሴውን ከፊት ሆነው ከሚመሩ ግለሰቦች አንዱ የሆኑት አቶ በየነ ገብረእግዚአብሔር፤ ጽህፈት ቤቱ “ተበታትኖ ለቆየው” የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ “አንድ መገናኛ ማዕከል” እንደሆነ ገልጸዋል።
የጽህፈት ቤቱን መከፈት የተገለጸው ብርጌድ ንሓመዱ ከሌላኛው ተቃዋሚ ድርጅት “የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ” ጋር በመሆን ጥር 19/2017 ዓ.ም. ኤርትራውያን የተገኙበትን ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማ ካካሄደ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ነው።
የብርጌድ ንሓመዱ የዲፕሎማሲ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ በየነ ገብረእግዚአብሔር፤ ከዚህ ቀደም በምዕራባውያን ሀገራት ሲከናወን የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ “ከሌሎች ሀገራት በተለየ [መንገድ] በኢትዮጵያ መጀመሩን” ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የእንቅስቃሴው ተወካዮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ንግግር ማድረጋቸውን የሚገልጹት አቶ በየነ፤ “ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረብነው ጥያቄም በኤርትራ ስር ነቀል ለውጥ እንደምናካሂድ ነው” ብለዋል።

“ብርጌድ ንሓመዱ” ምንድን ነው?
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
“ብርጌድ ንሓመዱ” ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለይም በምዕራባውያን እና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት እየተስፋፋ እና ትኩረት እየሳበ የመጣ የኤርትራውያን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው።
ደጋፊዎቹ በሚያደርጉት ሰማያዊ ቲሸርት የሚለየው ይህ እንቅስቃሴ፤ “ሰማያዊ አብዮት” በሚል መጠሪያው ይታወቃል።
የብርጌድ ንሓመዱ ደጋፊዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት የኤርትራ መንግሥት በተለያዩ ሀገራት የሚያዘጋጃቸውን ክብረ በዓሎች እና ዝግጅቶች በማወክ ነው። አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እስራኤል፣ ካናዳ፣ጀርመን፣ ስዊድን እና ስዊትዘርላንድ የኤርትራ መንግሥትን በሚደግፉ ፌስቲቫሎች ላይ ረብሻ ያጋጠመባቸው ሀገራት ናቸው።
በእነዚህ ረብሻዎች ወቅት የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ እና በተቃዋሚ ኤርትራውያን መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በተደጋጋሚ የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
በዚህ ዓይነቱ አመጽ ላይ የተሳተፉ ኤርትራውያን በተለያዩ ሀገራት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ብርጌድ ንሓመዱን “የሀገር ውስጥ አሸባሪ ድርጅት” በማለት የሰየመው የጀርመን ዐቃቤ ሕግ ደግሞ፤ ይህንን “አሸባሪ ድርጅት በመመሥረት እና አባል በመሆን የተጠረጠሩ” 17 ሰዎችን እያፈላለገ መሆኑን አስታውቋል።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኤርትራውያን ፌስቲቫሎቹን ለማስቆም የተንቀሳቀሱት ሁነቶቹ “የመንግሥት መሳሪያ” በመሆናቸው እንደሆነ በብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ ከሚጠቀሱት ግለሰቦች አንዱ የሆኑት ኪሮስ አስፍሃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እነዚህን ፌስቲቫሎች ሽፋን ተደርጎ የሚሰበሰበው የገንዘብ መዋጮ ለሥርዓቱ ጉልበት ይሰጡት ስለነበር ይህ እንቅስቃሴ ተደረገ” ሲሉ ኤርትራውያኑ ፌስቲቫሎቹን የተቃወሙበትን ምክንያቱ ያስረዳሉ።
የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ “ፌስቲቫሎችን ለማስቆም” በሚል ምክንያት ይጀመር እንጂ የቡድኑ የመጨረሻ ግብ ከ30 ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የቆየውን የኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት “ማስወገድ” ነው።
ከኤርትራ እንደ ሀገር መመሥረት ጀምሮ በሥልጣን ላይ ያለው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት፤ ባለፉት 32 ዓመታት አገር አቀፍ ምርጫ አድርጎ አያውቅም።
ኤርትራ ውስጥ፤ ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚ እና ተርጓሚ የተባሉት የመንግሥት መዋቅሮች በቅጡ ያልተዋቀሩ እንዲሁም የማይሠሩ ሲሆን፣ የሀገሪቱ መንግሥትም በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይከሰሳል።
የኤርትራ መንግሥት፤ ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሃይማኖት መሪዎችን ያለ ክስ ለረጅም ዓመታት በማሰር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ክስ ይቀርብበታል።
ሀገሪቱ ዜጎች ገደብ የሌለው የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚደረጉ መሆኑም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያስወቅሳት ዋነኛ ጉዳይ ነው።
- የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት በወታደራዊ አቅም በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?15 ሚያዚያ 2025
- መንግሥት የኮሪደር ልማትን ለጊዜው እንዲገታና ሰዎችን በግዳጅ እንዳያፈናቅል አምነስቲ አሳሰበ14 ሚያዚያ 2025
- ከቁጥር ባሻገር፡ ነዋሪውን ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የሁለት ዓመቱ የአማራ ክልል ግጭት14 ሚያዚያ 2025

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን “የግዳጅ ሠራተኝነት እና ባርነት” ሲል የሚገልጸውን ይህንን ወታደራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካታ ኤርትራውያን ሀገራቸውን ጥለው ወጥተዋል።
ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት 17 በመቶ የሚሆኑት የተሰደዱባት ኤርትራ፤ ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር ከፍተኛ ጥገኝነት ጠያቂ ዜጋ ያላት ሀገር እንደሆነች የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ግንቦት 2016 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
የብርጌድ ንሓመዱ አመራሩ አቶ በየነ፤ ኤርትራ መንግሥት መዋቅሮች በስደት ላይ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች “ፖለቲካዊ ጥገኝነት እና ሰላም” ላይ “ድንበር የተሻገረ ጭቆና እና ጫና መፍጠር መጀመሩን” በማንሳት ይከስሳሉ።
ይህንን ተከትሎ የተፈጠረው የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ፤ ዋነኛ ግቡ “በኤርትራ ስር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ማካሄድ” እንደሆነ አቶ በየነ ያስረዳሉ።
“ከሥርዓት ለውጡ” በኋላ “በብሔራዊ ጉባኤ በማካሄድ ጊዜያዊ የሽግግር ተቋማትን የመመሥረት” ውጥን መኖሩንም ገልጸዋል።
“መጀመሪያ ሥርዓቱን ከኤርትራ ማስወገድ ነው። ከዚያም በመቀጠል በየደረጃው ወደ ሕግ ሊቀርቡ የሚችሉ [የመንግሥት አመራሮችን] ወደ ሕግ ማቅረብ እንዲሁም ምህረት ሊደረግላቸው የሚገቡትም ምህረት ማድረግ [ይቀጥላል]።
ሀገሪቱ ለማረጋጋት እና ለማሸጋገርም በየደረጃው የሚቀርቡ ሰነዶችም አሉ” ሲሉም እንቅስቃሴው ግቡን ሲያሳካ ሊያከናውን ያቀዳቸውን ተግባራት ጠቅሰዋል።
የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ አመራሮች ግባቸው ‘በሰላማዊ ትግል ይሳካል’ የሚል እምነት የላቸውም። የእንቅስቃሴው ዋነኛ መታገያ ስልት የትጥቅ ትግል እንደሆነ ሁለት የትግሉ አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ አመራሮች የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ የትጥቅ ትግል ለመምረጡ በምክንያትነት የሚጠቅሱት፤ የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ቀደም በሰላማዊ ትግል ለውጥ ለማምጣት ሙከራ ባደረጉ ተቃዋሚዎች ላይ ያደረሰውን ስቃይ እና አፈና ነው።
አቶ በየነ፤ “[የኤርትራ መንግሥት] ለተቃዋሚዎች እና ቅሬታ ላላቸው ዜጎች እውቅና አይሰጥም። የተለየ ሃሳብ ያለው ዜጋ ዕጣ ፈንታው እስር ቤት፣ ጉድጓድ፣መረሸን እና መሰወር ነው።
በዘጠናዎቹ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሞከሩት ዜጎቻችን አሁን ድራሻቸው የለም” ሲሉ ያስረዳሉ።
ኤርትራውያን ዜጎች በሙሉ በግዳጅ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉን እንደ መልካም ዕድል የሚቆጥሩት አቶ በየነ፤ “[አብዛኛው] ኤርትራዊ ከሳዋ የመጣ ስለሆነ፤ ምናልባት አሁን ስላሉት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ካልሆነ በስተቀር አዲስ ወታደራዊ ሥልጠና የሚያስፈልገው ዜጋ አይደለም” ይላሉ።
አቶ በየነ፤ ብርጌድ ንሓመዱ የሚያካሂደው የትጥቅ ትግል “በጅማሬ ላይ” መሆኑን ይናገራሉ። የብርጌድ ንሓመዱን የዲፕሎማሲ ሥራ የሚያስተባብሩት አመራሩ፤ ለእንቅስቃሴው ድጋፍ ለማግኘት “ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከካናዳ እና ስዊዲን ባለሥልጣናት ጋር” ንግግር መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ በየነ፤ የተቃውሞ እንቅስቃሴው የሚያካሂደው የትጥቅ ትግል ከርቀት ሊካሄድ የማይችል መሆኑን በመጥቀስ፤ “ይህ ስር ነቀል ለውጥ የሚባለው በሀገራችን አካባቢ እንደሚሆን የታወቀ ነው” ሲሉ ትግሉ መሠረቱን የሚያደርግበትን ቀጣና ጠቁመዋል።

የብርጌድ ንሓመዱ ትጥቅ ትግል ከኢትዮጵያ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የብርጌድ ንሓመዱ እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች ሊያደርጉ ላሰቡት የትጥቅ ትግል መሠረት የሚሆነው አካባቢ የትኛው እንደሚሆን በግልጽ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ በየነ፤ ከኢትዮጵያ የሚነሳ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ የማድረግ ዕቅድ ይኖር እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ “በኢትዮጵያ ምደባ፣ ዘመቻ (campaign)፣ አደረጃጀት፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ማዕከላት ሊቋቋሙ ይችላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ብርጌድ ንሓመዱ የትጥቅ ትግል ለመጀመር “አባሎቻችን በመመዝገብ እና መደራጀት ላይ” እንደሆኑ የሚናገሩት አመራሩ፤ “ፈቃድ ሲመጣ ወዲያው ወደተባልነው ቦታ እንድንሄድ [ወታደራዊ ማዕከሉን የሚያዝዙ] መሪዎችን እያዘጋጀን እንገኛለን” ብለዋል።
ይህ ፈቃድ የሚመጣው ከየትኛው አካል እንደሆነ ግን አላብራሩም።
የብርጌድ ንሓመዱን እንቅስቃሴ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር “ንግግር ማድረጋቸውን” አቶ በየነ ይናገራሉ።
“ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረብነው ጥያቄ በኤርትራ ስር ነቀል ለውጥ እንደምናካሂድ ነው።
ስለዚህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚባለው ለብቻው የሚታይ አይደለም” ሲሉ በምን ዓይነት መልኩ የእንቅስቃሴው ዓላማ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንዳስረዱ ጠቅሰዋል።
አስተባባሪው፤ ከኢትዮጵያ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ንግግር ተደርጎ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ይህንን ጉዳይ ለመከታተል የተሰየሙ “የወታደራዊ ክንፍ አመራሮች” መኖራቸውን ገልጸው፤ “መቶ በመቶ አለ ወይም የለም ብዬ ልናገር አልችልም” ብለዋል።
ብርጌድ ንሓመዱ፤ በኢትዮጵያ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ “በሌሎች ሀገራት ካለው የተለየ” መሆኑን የሚያነሱት አቶ በየነ፤ ለዚህም ሦስት ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ።
አስተባባሪው፤ ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ ጋር ተያይዞ ያላት የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በምክንያትነት የሚጠቅሱት አንዱ ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ “በኢኮኖሚ እና ፀጥታ ቅርበት ያላቸው” ተጎራባች ሀገራት መሆናቸው እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ “ከ300 ሺህ በላይ” ኤርትራውያን መኖራቸው ብርጌድ ንሓመዱ በተለየ መልኩ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በምክንያትነት የተጠቀሱ ሌላኞቹ ምክንያቶች ናቸው።
አቶ በየነ፤ “ሦስተኛው ዓላማ፤ በምዕራባውያን ሀገራት የተፈጠረው ትግላችን ወደ ሀገሩ አካባቢ ማንቀሳቀስ ነው።
ወደ ጎረቤት ሀገሩ በማምጣት ለለውጡ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ ጠርቶ ሊሰማው በሚችልበት ጎረቤት መፍጠር ነው።
በኢትዮጵያ ስንል በሰመራ፣ በመቀለ ወይም ሑመራ በተለያዩ አከባቢዎች በመቅረብ ትግሉን ማስፋት ነው” ብለዋል።

የብርጌድ ንሓመዱ በኢትዮጵያ መገኘት በኤርትራ እና በአፍሪካ ቀንድ የሚፈጠሩ ለውጦችን በቅርበት ለመከታተል እንደሚጠቅምም ያክላሉ።
እንቅስቃሴው በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት የመክፈቱ አንድ ምክንያት ይህ መሆኑንም ገልጸዋል።
አመራሩ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኤርትራ ኤምባሲ “በመተካት” በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ማከናወን ሌላኛው የቢሮው ተግባር እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህንን በተመለከተ “ከኢትዮጵያ መንግሥት አካላት ጋር ንግግር” መደረጉን ያነሱት አቶ በየነ፤ የብርጌድ ንሓመዱ አባል የሆኑ ስደተኞች “መለያ ወረቀት (ID) እንዲሰጣቸው፣ የተመዘገቡበት ቁጥር እንዲኖራቸው እና ዋስትናቸው እንዲሟላ” ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።
ለእንቅስቃሴው አባላት እንዲሰጥ ንግግር የተደረገበት “የመለያ ወረቀት”፤ የብርጌድ ንሓመዱ አባል የሆነ ኤርትራዊ “ታስሮ ወደ ኤርትራ እንዳይወሰድ” የሚረዳ እንደሆነ አብራርተዋል።
“ስለዚህ ማንኛውም ከኤርትራ በስደት የመጣ እና ‘እየተካሄደ ያለውን ትግል ደግፌ የስደት ሕይወቴን አሳጥራለሁ’ የሚል ዜጋ፤ መጀመሪያ የብርጌድ ንሓመዱ የአባልነት ካርድ ያገኛል፤ ከዚያም በኢትዮጵያ የደኅንነት ዋስትና እንዲኖረው ይደረጋል” ሲሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተደርጓል ያሉትን ንግግር ጠቅሰዋል።
አቶ በየነ እንደሚያስረዱት የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት መከፈት ዓላማ ስደተኞችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ብቻ አያበቃም። አመራሩ፤ “ቢሮውን የከፈትነው በቀጣይ ወታደራዊ ማዕከሎች ሲከፈቱ ደግሞ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ሆኖ ሁሉንም እንዲያዝዝ ነው” በማለት ቢሮው ወደፊት በብርጌድ ንሓመዱ የትጥቅ ትግል የሚኖረውን ሚና አስረድተዋል።
አቶ በየነ፤ የብርጌድ ንሓመዱ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት የተከፈተው የእንቅስቃሴው አመራሮች ለኢትዮጵያ መንግሥት “ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት” መሆኑን ይናገራሉ።
በቀጣይም በአፋር ክልል ይህንን ዓይነት ጽህፈት ቤት የመክፈት ዕቅድ እንዳለም ጠቁመዋል።
የእንቅስቃሴው አመራሮች ወደ አፋር እና ትግራይ ክልሎች መሄዳቸውን የሚናገሩት አቶ በየነ፤ “እስከ አሁን የተፈቀደልን ነገር አድርገናል” ብለዋል።
“በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥመን ካለን የውስጥ የፀጥታ መዋቅር በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋስትና ይሰጠናል” በማለት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ታጣቂዎችን የመደገፍ ልምድ
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ ለአስርት ዓመታት በጠላትነት የቆዩት አዲስ አበባ እና አሥመራ፤ አንዳቸው የሌላኛቸውን መንግሥት ለመገልበጥ የሚሠሩ ታጣቂ ቡድኖችን የመደገፍ የቆየ ልምድ አላቸው።
ኤርትራ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ አርበኞች ግንቦት 7 እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴን ለዓመታት አስጠልላ ስትረዳ ቆይታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በተመሳሳይ በተለያዩ ጊዜያት የኤርትራ መንግሥትን ለመገልበጥ ዕቅድ ያላቸውን ተቃዋሚ ድርጅቶች አስተናግዷል።
ኤርትራዊው የሥነ ሰብ ፕሮፌሰር አብዱልቃድር ሳለህ መሐመድ እና በኖርዌይ የኦስሎ ኒው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የግጭት ጥናት ፕሮፌሰር ሸትል ትሮንቮል በ2007 ዓ.ም. ባሳተሙት የባለሙያ ትንተና መጣጥፍ ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ የሚገኙ ብሔረሰቦችን ጥያቄ ይዘው የተነሱ ተቃዋሚ ቡድኖች “እንዲመሠረቱ እገዛ ማድረጉን” ጽፈዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እገዛ ተመሥርተዋል ተብለው የተጠቀሱት ብሔር ተኮር ድርጅቶች፤ “የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” እና “የኤርትራ ኩናማ ነጻነት እንቅስቃሴ” የተባሉት ታጣቂ ቡድኖች ናቸው።
ከአስር ዓመት በፊት በወጣው ፅሁፍ ላይ የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 15 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ተጠቅሷል። ይህ ታጣቂ ቡድን አሁንም ድረስ መሠረቱን በአፋር ክልል አድርጎ ይንቀሳቀሳል።
“የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ኮንግረስ” የተባለው ተቃዋሚ ድርጅትም በተመሳሳይ በአፋር ክልል ውስጥ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። “የኤርትራ ወጣቶች አንድነት ለብሔራዊ ድኅነት (ስምረት)” የተባለው ተቃዋሚ ድርጅት ደግሞ በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ነበረው።
የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶችን የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከሚጠቀሱ ሁነቶች አንዱ በ2003 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው ኮንፈረንስ ነው።
ለአስር ቀናት የተካሄደው ይህ ኮንፈረንስ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ከ500 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የወጣቶች ተወካዮች የተሳተፉበት ነው።
የኤርትራ ዲያስፖራ ማኅበረሰብ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በ2015 ዓ.ም. የታተመ አንድ ጥናት፤ በሐዋሳው ኮንፈረንስ ላይ 21 የፖለቲካ ድርጅቶች መሳተፋቸውን አስፍሯል።
በጃፓን ቶኪዮ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በወቅቱ በድረ ገጹ ባወጣው ጽሁፍ ደግሞ ከ30 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮንፈረንሱ ላይ መሳተፋቸውን ገልጿል።

የኤርትራን “አምባገነን [መንግሥት] ለመገልበጥ የሚያስችል ዐቢይ ስልትን ለማጽደቅ” በተካሄደው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንደተገኙ የኤምባሲው ጽሁፍ ያስረዳል።
አምባሳደር ሬድዋን በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ኮንፈረሱ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነታቸውን እንዲፈቱ እና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ይረዳል” የሚል ዕምነት እንዳላቸው እንደገለጹም በጽሁፉ ላይ ሰፍሯል።
የኤምባሲው ጽሁፍ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በኤርትራ ሰላም እና ዴሞክራሲ ለማምጣት ለሚደረገው ትግል ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል” ሲል የአምባሳደር ሬድዋንን ንግግር ጠቅሷል።
ለሐዋሳው ኮንፈረስን ዝግጅት ለማድረግ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ የተሳተፈው ጋዜጠኛ ካሊድ አብዱ፤ የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶች በአዲስ አበባ እንዲሁም እንደ አዲግራት እና ሽረ ባሉ የትግራይ ክልል ከተሞች ጽህፈት ቤቶች እንደነበሯቸው ያስታውሳል።
በአሁኑ ወቅት ስዊዲን የሚገኘው ጋዜጠኛው፤ “ጽህፈት ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ በየወሩ [ከመንግሥት] የሚሰጣቸው የተወሰነ ገንዘብ ነበር። በተለይ ደግሞ መሳሪያ አንግበው የሚታገሉትን ይረዷቸው ነበር” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያገኙ የነበረው “ባላቸው እንቅስቃሴ እና የሰው ብዛት” ተሰልቶ እንደነበር የሚያስረዳው ካሊድ፤ በዚህ ምክንያት የአፋር እና የኩናማ ብሔረሰብ ታጣቂዎች ከሌሎቹ ድርጅቶች የበለጠ ድጋፍ ያገኙ እንደነበር ይገልጻል።
“አፋሮች እና ኩናማዎች በብዛት ሠራዊት ስለነበራቸው እነሱ የበለጠ ይረዱ ነበር። ይህ ደግሞ በብሔራቸው ምክንያት [እንደሆነ] ተደርጎ፤ ‘ኢህአዴግ የብሔር አቀንቃኝ ስለሆነ እነሱን የበለጠ እየደገፋቸው ነው’ የሚል ክስ ከሌላው አካል ይቀርብ ነበር” ሲል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
ከዚህም ባሻገር በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ማግኘትን በተመለከተ በተቃዋሚ ድርጅት እና እንቅስቃሴዎች መካከል ክርክሮች እና አለመግባባቶች ነበሩ።

“የባሕር በር ጥያቄን እኛ ልንመልሰው እንችላለን”
በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ድጋፍ ሲያገኙ የቆዩት የኤርትራ ተቃዋሚዎች፤ ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙት ለውጥ የታየበት፤ በ2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው።
አዲስ አበባ እና አሥመራ የሰላም ስምምነት መፈጸማቸውን ተከትሎ ሐምሌ 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የኤርትራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ማዘዙን”፤ ፖለቲካዊ ነጻነትን በተመለከተ ጥናቶችን የሚያደርገው የአሜሪካው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት “ፍሪደም ሐውስ” አስታውቆ ነበር።
ነሐሴ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ ተቃዋሚዎች ሲሰጥ የነበረውን “የገንዘብ እና የምግብ” ድጋፍ ማቋረጡን በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚያቀርበው “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ድረ ገጽ ዘግቧል።
ጋዜጠኛው ካሊድ፤ ከስምምነቱ በኋላ “ከአዲስ አበባ ተጠልፈው ወደ ኤርትራ የተወሰዱ” ተቃዋሚዎች እንደነበሩ ይናገራል።
ከኢትዮጵያ “ከተወሰዱት” የኤርትራ ተቃዋሚዎች መካከል “የአውሮፓ ሀገራት ዜግነት ያላቸው” ጭምር እንደሚገኙበት የሚገልጸው ካሊድ፤ በዚህ ምክንያት “በጣም ብዙ” የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ለቅቀው መውጣታቸውን ያነሳል።
ከዚህ በመነሳት የአሁኑን የብርጌድ ንሓመዱ እና የኢትዮጵያ መንግሥትን ግንኙነት በጥንቃቄ የሚያየው ካሊድ፤ “አሁንስ ነገ ጠዋት ይህ [ግንኙነት] እንደማይገለበጥ ዋስትናው ምንድነው?” ሲል ይጠይቃል።

በ2010 ዓ.ም. ወደ ወዳጅነት ተቀይሮ የነበረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት፤ የትግራይ ጦርነትን ካስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ ዳግም ሻክሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ እያነሳው ያለው በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ እና በቀጣናው እየታየ ያለው የአሰላለፍ ለውጥም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን መካረር ጨምሮታል።
የኤርትራው ተቃዋሚ ብርጌድ ንሓመዱ፤ በኢትዮጵያ እንስቃሴውን ለማስጀመር የተንቀሳቀሰው በአዲስ አበባ እና በአሥመራ መንግሥታት መካከል የነበረው “ግንኙነት መቋረጡ” እና “ልዩነታቸው [መስፋቱ] በተረጋገጠበት” ጊዜ እንደሆነ የእንቅስቃሴው አመራር አቶ በየነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አመራሩ፤ “ወደ ኢትዮጵያ የሄድነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢሳይያስ [መንግሥት] ጋር የነበረው ግንኙነት በተቋረጠበት ወይም ልዩነታቸውን ባረጋገጥንበት ጊዜ እንደገና ወደ ሌላ ጦርነት እና ችግር እንዳንገባ እንደ አማራጭ እንድንሆን ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ብርጌድ ንሓመዱ በኤርትራ ሊያደርግ ባቀደው “ስር ነቀል ለውጥ ላይ” ኢትዮጵያ መንግሥት “የድርሻውን እንዲወጣ” የሚጠይቁት አቶ በየነ፤ ይህ ከሆነ መንግሥት የሚያነሳውን “የባሕር በር እና ሌሎች ጥያቄዎች እኛ ልንመልሳቸው እንችላለን” ይላሉ።
“መጀመሪያ የኤርትራ ሕዝብ በግዛቱ በሕገ መንግሥት እንዲተዳደር እናድርግ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ ያግዘን። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ በሚቀርባት አሰብ ተጠቃሚ እንድትሆን እና ይህንን እንድታስተዳድር [ለማድረግ] ችግር የለብንም” ሲሉ የእንቅስቃሴውን አቋም አብራርተዋል።
አቶ በየነ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት ወደ ጦርነት ያመራል የሚል እምነት እንደላለቸው ተናግረዋል።
“‘ሻዕብያ ከኢትዮጵያ’ ይውጣ የሚል ጥያቄ አለ። ‘ኤርትራን እንወርራለን’ የሚል ነገር ግን አላየሁም” የሚሉት አመራሩ፤ ጦርነት የሚነሳ ከሆነ ብርጌድ ንሓመዱ “በራሱ አወቃቀር፣ ቅርፅ እና አመራር” በኩል ጉዳዩን “እንደሚወያይበት” ገልጸዋል።
ቢቢሲ የብርጌድ ንሓመዱን የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት በኢሜይል ያቀረበው ጥያቄ እና ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አላገኙም።