ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

ከ 1 ሰአት በፊት

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በታይም መጽሔት የዓመቱ የዓለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተካተቱ።

ታይም መጽሔት በየዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የሚላቸውን የ100 ሰዎች ስም ዝርዝርን ይዞ ይወጣል።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የአገራት እና የድርጅት መሪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አርቲስቶች እና ስፖርተኞች እንዲሁም ፀሐፊያን ይካተቱበታል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በታይም መጽሔት የ2025 ተጽእኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነታቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ሰዎች በእኩልነት የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ባበረከቱት አመራር የተነሳ የታይም መጽሔት የ100 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ አካትቷቸው ነበር።

ዶ/ር ቴድሮስ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “በዝርዝሩ ውስጥ መካተቴ በምሠራበት የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ ለሚሠሩ ባልደረቦቼም እውቅና ነው” ብለዋል።

በመጽሔቱ ላይ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ሃሳባቸውን ያጋሩት ዶ/ር ላሪ ብሪሊያንት በበኩላቸው “ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ከሆኑ በኋላ የዓለማችንን የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀይረውታል” ብለዋል።

የፈንጣጣ በሽታ ከዓለም ላይ አንዲጠፋ ቁልፍ አስተዋጽኦ ያደረጉት ዶ/ር ላሪ የዓለምጤና ድርጅት ኃላፊ ይህንን ማድረግ የቻሉት “በበሳል አመራር እና ሳይንሳዊ በሆነ የውሳኔ አሰጣጥ” በመታገዘ ነው ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ “ለዓለም ጤና ስጦታ ናቸው” ያሉት ዶ/ር ላሪ “የዓለም ጤና ድርጅትን ለመጀመሪያው ጊዜ የመሩ አፍሪካዊ መሪ፣ የመጀመርያው ሕክምና ያላጠኑ መሪ፣ ሚሊዮኖችን የገደለውን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የተጋፈጡ የመጀመሪያው መሪ፣ አሁን ደግሞ አሜሪካ ከመሠረተችው ተቋም ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ስትወጣ የተጋፈጡ መሪ ናቸው” ሲሉ በመጽሔቱ ላይ ጽፈዋል።

አክለውም በ194 አገራት የሚገኙ ሰዎችን ጤና የመጠበቅ ኃላፊነትን እየተወጡ የሚገኙ ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

“አመራሩ መርኅ ላይ የተመሠረተ ነው። ሀቀኛ ነው፤ ውጤት ተኮርም ነው። ዓለማችንን ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ጤነኛ እንድትሆን አድርጓል” በማለት ዶ/ር ላሪ ታይም መፅሔት ላይ ምስክርነታቸውን አስፍረዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት እአአ ከ2012 እስከ 2016 ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ሚንስትር ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና መሠረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋታቸው እና የሕጻናት እና የእናቶች ሞት መጠን መቀነሱ ይገለጻል።

ዋና ዳይሬክተሩ የዓለም ጤና ድርጅትን ለሁለተኛ ጊዜ በኃላፊነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

የህወሓት አባል የነበሩት ዶ/ር ቴድሮስ በመጀመሪያው ዙር የዓለም ጤና ድርጅት መሪነት ዘመናቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር ጦርነት በገጠመበት ወቅት ለቡድኑ ድጋፍ ይሰጣሉ በሚል ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ከስሰዋቸዋል።

ስለ ዶ/ር ቴድሮስ በአጭሩ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ቴድሮስ አድሃኖም የዓለማችንን ዋነኛ የጤና ተቋም ለመምራት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ሰው ሲሆኑ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ለውድድር ከቀረቡ ከበርካታ ዕጩዎች መካከል ተመርጠው ነው ለሁለት ዙር ድርጅቱን እየመሩ ያሉት።

በኤርትራ አሥመራ ውስጥ ተወልደው ያደጉት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባይሎጂ ከአሥመራ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል።

በተጨማሪም ከለንደን ዩኒቨርስቲ በኢንፌክሺየስ በሽታዎች ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በማኅበረሰብ ጤና ጥናት ከኖቲንግሃም ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ በኢትዮጵያ ውስጥ በሙያቸው በጤና አገለግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል። የወባ በሽታ ጥናት፣ የትግራይ ጤና ቢሮ ኃላፊ ከዚያም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ለረጅም ዓመታት አገለግለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የአገሪቱ የጤና ዘርፍ ላይ መጠነ ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን በማከናወን የጤና አገለግሎቶች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች እንዲደርሱ የሚያስችል መሠረት ጥለዋል።

በርካታ የጤና መሠረተልማቶች እንዲገነቡ፣ የጤናው ዘርፍ የገንዘብ ምንጮች እንዲሰፉ በማድረግ እንዲሁም የጤና ሠራተኞች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ይጠቀሳሉ።

በዚህም ምክንያት የመጀመሪያ የጤና ክብካቤ ማስፋፊያ ፕሮግራምን በመጀመር 40 ሺህ ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በመላው አገሪቱ ተሰማርተው አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋል።

በዚህም ምክንያት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የሚሞቱ እናቶች እና ሕጻናት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የዓለም ጤና ድርጅት አመልክቷል።

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ውስጥ በአመራርነት ቦታ ላይ ሰርተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነትን ከተረከቡ በኋላም ዶ/ር ቴድሮስ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ሥራ በመጀመር በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅሷል።