የአርሰናል ተጫዋቾች

ከ 2 ሰአት በፊት

አርሰናል አስደናቂ የሚባል ምሽት ባሳለፈበት ጨዋታ ሪያል ማድሪድን በሜዳው ቤርናባው 2 ለ 1 በድምር ውጤት ደግሞ 5 ለ 1 አሸንፎ ሻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ መድረሱን አረጋግጧል።

በዚህም መድፈኞቹ በታሪካቸው ለሦስተኛ ጊዜ በአውሮፓውያኑ ከ2009 በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩን ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ችለዋል።

በድራማ በተሞላው የረቡዕ ምሽት የመልስ ጨዋታ ቡካዮ ሳካ በመጀመሪያው አጋማሽ የፍጹም ቅጣት ሲስት ለሪያል ማድሪድ የተሰጠ ፍጹም ቅጣት ምት ደግሞ በቫር ከታየ በኋላ እንዲቀለበስ ተደርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሳካ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ ቻለ።

ዊሊያም ሳሊባ የፈጸመውን ስህተት ተጠቅሞ ቪኒሺየስ ጁኒየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ቢችልም ጋብርኤል ማርቲኔሊ ባስቆጠራት ግብ መድፈኞቹ 2 ለ 1 እንዲያሽነፉ ረድቷል።

አርሰናል የመጀመሪያው ጨዋታ 3 ለምንም ማሸነፉን ተከትሎ በድምር ውጤት 5 ለ 1 በማሸነፍ በሰፊ የግብ የበላይነት ወደ ግማሽ ፍጻሜው መቀላቀሉን አረጋግጧል።

አርሰናል በግማሽ ፍጻሜው ፒኤስጂን የሚገጥም ይሆናል።

“ይህ በእግር ኳስ ሕይወቴ ምርጡ ከምላቸው ምሽቶች አንደኛው ነው” ሲል አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ ተናግሯል።

“ትልቅ ታሪክ ካለው ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው። ይህ ውድድር ለሁላችንም መነሳሳትን የፈጠረ ነው።”

“በውድድሩ ያለን ታሪክ አጭር ነው። ይህን ታሪክ ስንሠራ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በጥሩ ሞራል ላይ ስለምንገኝ ይህንን አስጠብቀን መቀጠል ይኖርብናል” ብሏል።

የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ ቲዮ ዋልኮት በበኩሉ “እነዚህ የአርሰናል ተጫዋቾች ከሥነ ልቦና አንጻር ለታላላቅ ጨዋታዎች ዝግጁ ናቸው” ሲል ሃሳቡን ለቢቢሲ ስፖርት ገልጿል።

በሌላ የምሽቱ ጨዋታ ኢንተር ሚላን እና ባየር ሙኒክ 2 አቻ ተለያይተዋል።

ለኢንተር ላውታሮ ማርቲኔዝ እና ባጃሚን ፓቫርድ ሲያስቆጥሩ ለባየር ሚኒክ ደግሞ ሃሪ ኬን እና ኤሪክ ዳየር ኳስ እና መረብ አገናኝተዋል።

የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ 2 ለ 1 ያሸነፈው ኢንተር ሚላን በድምር ውጤት 4 ለ 3 በሆነ ውጤት አሸንፎ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚደረጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ኢንተር ሚላን በሜዳው ባርሴሎናን ሲያስተናግድ አርሰናል ደግሞ ወደ ፓሪስ አቀንቶ ፒኤስጂን ይገጥማል።