
ከ 4 ሰአት በፊት
ሃማስ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነት በይፋ ውድቅ አድርጎ፣ ጦርነቱ እንዲያበቃ እና ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲፈቱ በምላሹ የተቀሩት እስራኤላውያን ታጋቾች ለመልቀቅ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ ብሏል።
የሃማስ ዋነኛ ተደራዳሪ ካሊል አል-ሀያ በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ “የኔታንያሁን [የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር] የፖለቲካ አጀንዳ የሚያገለግል ከፊል ስምምነቶችን አንቀበልም” ብለዋል።
59 እስራኤላውያን ታጋቾች አሁንም በሃማስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ የሚገለጽ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 24ቱ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
እስራኤል በቅርቡ ያቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት አስር ታጋቾችን ለማስለቀቅ ለ45 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁምን ማድረግ ያካተተ ነበር።
የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በሃማስ ላይ “የገሃነም በሮች የሚከፈቱበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ ዝተዋል።
በሳምንቱ መጀመርያ ላይ የሃማስ ባለስልጣናት እቅዱን እንደማይቀበሉት ለቢቢሲ ጠቁመው ነበር።
“ኔታንያሁ እና መንግሥታቸው ከፊል ስምምነቶችን ለፖለቲካ አጀንዳቸው መሸፈኛ አድርገው ይጠቀማሉ። ምንም እንኳን ሁሉንም እስረኞቹን [ታጋቾችን] መስዋዕትነት የሚያደርግ ቢሆን፣ይህም ፈጽሞ ከምድረ ገጽ የማጥፋት እና የረሃብ ጦርነታቸውን በማስቀጠል ላይ መሠረት ያደረገ ነው” ሲሉ የሃማስ ዋነኛ ተደራዳሪ ሀያ ተናግረዋል።
አክለውም ቡድኑ “በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጤማውያንን በእስራኤላውያን ታጋቾች ለመለዋወጥ እና ጦርነቱን ለማቆም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ነው” ብለዋል።
ሃማስ ቀደም ሲል ጦርነቱን ለማቆም አጠቃላይ ስምምነትን ከግምት እንደሚያስገባ ተናግሮ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች ያንን የሚያመጣ የትኛውም ዓይነት ስምምነት ላይ አልደረሱም።
እስራኤል ዓላማ ሃማስን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ማስፈታት እና ማጥፋት መሆኑን ይፋ አድርጋለች።
- የእስራኤል ወታደሮች ጦርነቱ ቢያበቃም በጋዛ “የፀጥታ ቀጠናዎች” እንደሚቆዩ ተገለፀ17 ሚያዚያ 2025
- የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምንድን ነው? አሜሪካስ ምን ትፈልጋለች?13 ሚያዚያ 2025
- ጋዛ ‘የግድያ ሜዳ ሆናለች’ ሲሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አሳሰቡ9 ሚያዚያ 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ፍልስጤማውያን በአየር ድብደባ በየቀኑ እየሞቱ ነው።
በጋዛ ሃማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ እንደገለጸው በቅርቡ የእስራኤል መከላከያ በፈጸመው ተከታታይ ጥቃቶች በትንሹ 37 ሰዎች ሞተዋል።
በአየር ጥቃቱ የደረሰን “ኃይለኛ” ፍንዳታ ተከትሎ፣ ስደተኞች የተጠለሉበት ድንኳኖች በእሳት ከተያያዙ በኋላ፣ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን በአል-ማዋሲ የሚገኙ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
አንድ ሰው ለቢቢሲ ጋዛ ላይፍላይን ፕሮግራም ሲናገር “ወደ ውጭ ሮጬ ስወጣ ከጎኔ ያለው ድንኳን በእሳት ተያይዞ አየሁ” ብሏል።
የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ላይ ወድያውኑ አስተያየቱን ባይሰጥም፣ ስለ ጥቃቱ የወጡ ሪፖርቶች እየተመለከትኩ ነው ብሏል።
እስራኤል ቀደም ሲል ፍልስጤማውያን ከሌሎች የጋዛ አካባቢዎች ወደ አል-ማዋሲ እንዲሄዱ አስጠንቅቃ ነበር።
የእስራኤል ጦር ባለፉት ሁለት ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች “የሽብር ህዋሶችን፣ ወታደራዊ መዋቅሮችን እና የመሠረተ ልማቶችን ጨምሮ “ከ100 በላይ የሽብር ዒላማዎች ተመትተዋል” ብሏል።
እስራኤል በጋዛ ምንም ዓይነት የእርዳታ እጥረት እንደሌለ በመግለጽ፣ ሃማስ ቀሪዎቹን ታጋቾች እንዲፈታ ግፊት ለማድረግ በሚል የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ አግዳለች።
ይሁን እንጂ የ12 ዋና ዋና የረድኤት ቡድኖች መሪዎች በጋዛ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ስርዓት “ጠቅላላ ውድቀት እየገጠመው ነው” ብለዋል።
እስራኤል ባለፈው መጋቢት ድጋሚ በጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት 1630 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ባለፉት 18 ወራት 51 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።